አዲስ እስራት ተከሰተ ያለዉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ | የጋዜጦች አምድ | DW | 06.02.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

አዲስ እስራት ተከሰተ ያለዉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ

መቀመጫዉን ብሪታንያ ሎንዶን ያደረገዉ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግስት በተቃዉሞ ፓርቲ ደጋፊዎች ላይ አዲስ የማዋከብና የማሰር ዘመቻ መጀመሩን የተመለከተ ዘገባ ይፋ አድርጓል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አርማ

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አርማ

አምነስቲ አዲስ የማዋከብና የእስር ድርጊት ያለዉን ዘገባ ይፋ ያደረገዉ ባለፈዉ ዓርብ ዕለት ሲሆን በፖሊስ ተይዘዉ የማሰቃየት ድርጊት ሳይፈፀምባቸዉ አይቀርም ያላቸዉንም የተወሰኑ ሰዎች የስም ዝርዝር በዘገባዉ ላይ አስፍሯል።

ሰዎቹ ከሰዉ እንዳይገናኙ በስዉር ነዉ የታሰሩት የሚለዉ የአምነስቲ ዘገባ በቅድሚ ማዕከላዊ በሚባለዉ ስፍራ ይህ ተፈፅሞባቸዋል ይላል። ሎንዶን የሚገኘዉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ የሆኑት ማርቲን ሂል ድርጅታቸዉ በቅርቡ በኢትዮጵያ አገረሸ ስላለዉ በተቃዉሞ ድርጅት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በእንግሊዝኛዉ ምህፃሩ CUD አባላትና ደጋፊዎች ላይ የማዋከብና የእስራት ዘመቻዉ መካሄዱን አስመልክቶ ያወታዉን ዘገባ ምንነት እንዲያስረዱን ጠይቄያቸዉ ነበር

«አዎ! አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ አስደንጋጭ ዘገባ ደርሶታል። ይህም በCUD ላይ ደጋፊዎች ወይም የፓርቲ አባላት አዲስ አበባ እስራት መጀመሩን ያመለክታል። እነዚህ ሰዎች የታሰሩት በታህሳስ ወር መገባደጃ ገደማ ነዉ። የታሰሩት ሰዎችም ሰዎች አያገኟቸዉም በመጀመሪያ በፖሊስ ማዕከላዊ ምርመራ ቢሮ ማዕከላዊ በመባል በሚታወቀዉ ስፍራ ማለት ነዉ ታስረዉ ነበር። አሁን ግን እንደሚገባን ከዚያ አዉጥተዋቸዋል።»

ይህ የሚሉን አሁን በቅርቡ ባለፈዉ ታህሳስ ወር የተፈፀመ ነዉ?

«አዎ ነዉ!፡በእርግጥ በ2005ዓ.ም በህዳር ወር የተካሄደዉን የተቃዉሞ ሰልፍ ተከትሎ በገፍ የታሰሩት የቅንጅት ደጋፊዎች አሁን በአብዛኛዉ ተለቀዉ ይሆናል ብለን እናስባለን። ሌሎቹ ደግሞ አሁንም የክስ ሂደታቸዉ እየታየ ነዉ በአገር ክህደትና በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸዉ። ሆኖም በርካታ በገጠር አካባቢ የሚገኙ ደጋፊዎችና በአዲስ አበባም ያሉት እየታሰሩ ነዉ። ይህም በቅርቡ የተፈፀመ ነዉ። ከCUD ጋ በተገናኘ እንቅስቃሴ 50 ወይም 40 የሚደርሱ ናቸዉ በቡድን የታሰሩት።»

አጃንስ ፍራንስ ፕረስ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል አቶ በረከት ስምዖንን ስለጉዳዩ ሲጠይቅ መሰረተ ቢስ ዉንጀላ ነዉ ማለታቸዉን ዘግቧል። የተባለዉን ለማጣራት ወደኢትዮጵያ ደዉዬ ነበር በተደጋጋሚ ባደረጉት ሙከራም አቶ በረከት ስምዖንን ትናንት ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ቢነግሩኝም ዛሬ ደግሞ ስልካቸዉ ቢጠራም አይነሳም። ቢሯቸዉም ብደዉል አለመኖራቸዉ ነዉ የተነገረኝ። አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ያለዉን በመጥቀስ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ምን ይላል ብያቸዉ ነበር

«ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ቀጥተኛ ምላሽ እኛ ገና አላገኘንም። እነሱ ዝርዝሩን ለማወቅ ፍላጎት አላቸዉ ማስተባበያ ሲሰጡ እኛ ደግሞ ይህ አለን ብለን በጥሩ መረጃዎች ነዉ የምናምነዉ። የእኛ ዘገባ የመቀስቀስና የመቆርቆር ዓይነት ነዉ። እነሱም ከበርካታ የአምነስቲ ፅህፈት ቤቶች የተለያዩ ማመልከቻዎች ሲቀርቡላቸዉ ከመንግስትም ሆነ ከኤምባሲዎቻቸዉ ዝርዝሩን መረጃ ለማወቅ መሻታቸዉ አይቀርም። እናም ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለጋዜጠኞች የሚሰጠዉ ፈጣን ምላሽ የሚረዳ አይመስለኝም።»

የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ተመራማሪ እንደመሆናቸዉ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ በኢትዮጵያ ዉስጥ ምን እንደሚመስል ተጠይቀዉ ሲያብራሩ

«በርካታ ነገሮች አሉ ትኩረት ሰጥተን የምንከታተላቸዉ። አንዱ በእርግጥ የCUD መሪዎች፤ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የተከሰሱበትን የፍርድ ሂደት መከታተል ነዉ። ሂደቱ ረዥም ጊዜ ወስዷል። እስካሁን አልተቋጨም። እኛ እነዚህ የCUD መሪዎችና ጋዜጠኞች እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች የታሰሩት ከአመፅ በራቀ ድርጊት ነዉና የህሊና እስረኞች ነዉ የምንላቸዉ። ሌላዉ ጉዳይ አሁንም ያልተጠናቀቀዉ የሜጫና ቱለማ ማህበር የኦሮሞ መሪዎች የሆኑትን ሰዎች ጉዳይ ነዉ። በደርግ ዘመን ያገለገሉ ሰዎችና በእስር ላይ የሚገኙትንም ሰዎች ጉዳይ እየተከታተል ነዉ። አብዛኛዎቹ እንደተፈራዉ የሞት ፍርድ አልተበየነባቸዉም። መንግስት እዚህ ጋ አዎንታዊ አካሄድ ተከትሏል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሞት ቅጣትን አይደግፍም።»

ይህ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት በተደጋጋሚ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዙሪያ ኢትዮጵያን የተመለከተ ዘገባዎችን ሲያቀርብና ለዓለም ማህበሰብ አቤቱታዉን ሲያሰማ መሰንበቱ ይታወሳል። ዛሬም ቀጥሏል። ለመሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል አዎንታዊ ምላሽአግኝቶ ይሆን? ሂል ይህን ይላሉ
«ለተወሰኑ አቤቱታዎች ምላሾችን አግኝተናል። ምላሹም እኛ ካልነዉ እጅግ የተለየ ነዉ ማለት እችላለሁ። በእኛ በሉል ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ዝግጁነን። በተጨማሪም ሊስተካከሉ የሚገባቸዉን የሰብዓዊ መብቶች ችግሮች በዝርዝር ልናቀርብ እንችላለን። ሆኖም እስከ ዛሬ አዎንታዊ ሊባሉ የሚችሉ ምላሾችን አላገኘንም። ወደፊት በዚህ ሁኔታ ይቀጥላል ብለን አናስብም።»

ተዛማጅ ዘገባዎች