አዲስ አበባ ደርሶ መልስ -ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ | ኢትዮጵያ | DW | 27.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ ደርሶ መልስ -ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ

ባራክ ኦባማ ከዘጠኝ አመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የመጀመሪያው በስልጣን ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ባራክ ኦባማ ካሁን ቀደም በሴናተርነት የስልጣን ዘመናቸው አገሪቱን ጎብኝተው ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:03 ደቂቃ

አዲስ አበባ ደርሶ መልስ -ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ

ከስድስት አመታት በፊት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በምዕራብ አፍሪቃዊቷ አገር ጋና ነበሩ። በዚያ ጉብኝታቸው የጋናን ምርጫና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አሞግሰው «አፍሪቃ ጠንካራ ሰው አትፈልግም። አፍሪቃ የምትፈልገው ጠንካራ ተቋማትን ነው።» ሲሉ ተናገሩ።

ያ ንግግራቸው ግን ለአንድ አፍሪቃዊ መሪ አልተዋጠላቸውም። የቀድሞው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ለነበሩት ዶናልድ ያማማቶ በባራክ ኦባማ ሃሳብ ላይ ተቃውሞ አሰምተው እንደነበር ቆይቶ ዊኪሊክስ ይፋ ያደረገው የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶች ምስጢር ያስረዳል። የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ መስፍን ነጋሽ አሁን ዋዜማ የተሰኘ የኢንተርኔት ሬዲዮ አዘጋጅና ሲቪል መብቶች ተከላካይ (Civil Rights Defenders) በተሰኘ የስዊድን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአፍሪቃ ቀንድና የምሥራቅ አፍሪቃ ክፍል ኃላፊ ነው። መስፍን ነጋሽ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከባራክ ኦባማ ንግግር መካከል « ለልማት ዴሞክራሲ ያስፈልጋል፤ለመረጋጋት ዴሞክራሲ ያስፈልጋል የሚባለውን ነገር።» እንዳልተቀበሉት ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸውም ምስጢሮች መነሻ በማድረግ ይናገራል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ «አፍሪቃ የምትፈልገው ጠንካራ ተቋማትን ነው።» ያሉት የልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ ናቸው።

ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአዲስ አበባ

አዲስ አበባ መንገዶቿን አጥባ፤ ሰንደቅ አላማ አውለብልባ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማን በደመናማው የእለተ እሁድ አመሻሽ ስትቀበል ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃና ፍተሻ ውስጥ ነበረች። የፕሬዝዳንቱ ጉዞ 122 ዓመታት በዘለቀው የኢትዮጵያና አሜሪካን ወዳጅነት በስልጣን ላይ እያሉ የምሥራቅ አፍሪቃዋን አገር የጎበኙ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ናቸውና ታሪካዊ ነው።

ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አዲስ አበባ ሲደርሱ ላለፉት 24 ዓመታት አገሪቱን ሲመራ የቆየው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ.) አምስተኛውን አገራዊ ምርጫ 100 % አሸንፏል። ተቃዋሚዎች በምርጫው ዴሞክራሲያዊነት፤ ነጻና ፍትሐዊነት የመረረ ቅሬታ አላቸው። ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሬስ ነጻነት እና የሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴን በማፈን ይተቻል። እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ተመጋቾች እነዚህን ሁነቶች እያጣቀሱ የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት ያጠይቃሉ። በሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ክፍል ምክትል ሃላፊ ለሆኑት ሌስሊ ሌፍኮ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን የሚጎበኙበት ጊዜ አጓጉል ነው።

«ዩናይትድ ስቴትስ የዴሞክራሲያዊ፤ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ደጋፊ ነች። ኢትዮጵያ ዉስጥ በግንቦት በተካሄደው ምርጫ ገዢው ፓርቲ በመቶ የተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮችን አሸንፏል። ስለዚህ ምርጫን አስመልክቶ አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮች አሉ። ይህ በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የጭቆና ሁኔታ የሚያሳይ ይመስለኛል። ጥያቄው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ምን ያገኛሉ? የሚለው ይሆናል። ኢትዮጵያ አጥብቃ በምትፈልገው የሰብዓዊ መብት አያያዝ መሻሻል ላይ ፈቃደኝነት ያገኛሉ?»

የሌስሊ ሌፍኮን ጥያቄ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ምህዳር የሚከታተሉ መንግስቱን የሚተቹ ሁሉ ይጋሩታል። የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በውጭ ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትችት ቢሰነዘርበትም ለኢትዮጵያ መንግስት እና ደጋፊዎቹ ግን ትርጉሙ ሌላ ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችው እድገትና በክፍለ አህጉሩ የምትጫወተን ሚና በቀዳሚነት ይጠቅሳሉ። የአፍሪቃ የጸጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ የሆኑት አቶ ሃሌሉያ ሉሌ «አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የጠበቀ የደህንነት(Security) ግንኙነትና ኢትዮጵያ በአህጉሩ እና ክፍለ አህጉሩ ያላት ሚና» ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት መነሻ ሊሆኑ ከሚችሉ ሶስት ጉዳዮች ቀዳሚው ሊሆን እንደሚችል ለዶይቼ ቨሌ ተናግረዋል። «ኢትዮጵያ ባለፉት አስር አመታት ያስመዘገበችው እድገት እና የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ መሆኗ» ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።

የሶማልያው አሸባብ ታጣቂ ቡድን ስጋት ከተጫናቸውና ለመፍትሄውም ደፋ ቀና ከሚሉ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች። ካሁን ቀደም በአሜሪካ እርዳታ የያኔውን እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኃይል የበታተነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አሁንም በሶማልያ ይገኛል። እንደ መስፍን ነጋሽ እምነት የፕሬዝዳንቱ ጉዞ «ኢትዮጵያ ደህንነቷ የተጠበቀ ነው።» የሚል መልዕክት ሊያስተላልፍ ይችላል።

ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዙ ለአገራቸው፤ ኢትዮጵያና ምሥራቅ አፍሪቃ አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሽብርተኝነት፤ ልማትና መዋዕለ ንዋይ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለ ስልጣናትና የአፍሪቃ ህብረት ጋር ከሚወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። በውጭ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግን በመወያያ ጠረጴዛው ላይ ምንም ይነሳ ምንም ጉብኝታቸው አያስፈልግም። እንዲያውም የጉብኝቱ ተቃዋሚዎች‘አምባገነን’ ላሉት የኢትዮጵያ መንግስት ቅቡልነትን (Legitmacy) የሚሰጥ ይሆናል ሲሉ ይተቻሉ። በአፍሪቃ የጸጥታ ጥናት ተቋም የአስተዳደርና ሰብዓዊ መብት አጥኚው ሴባስቲያን ጋቲሙ ግን «በኢትዮጵያ ያለው የዴሞክራሲ ሁኔታና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት በጣም ውስን ነው። ቢሆንም ከቀጣናው አኳያ በተለይም በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ኢትዮጵያ የምትጫወተውን ሚና ልንመለከት ይገባል።» ሲሉ ይከራከራሉ። «ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡባቸው ጉዳዮች መካከል ጸጥታ ዋንኛው ነው። ለውይይት ከሚቀርቡባቸው ጉዳዮች መካከል ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያን እንዴት ማረጋጋት ይቻላል? የኢትዮጵያስ ሚና ምን ይሆናል? የሚሉት ናቸው። በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት( ኢጋድ )አማካኝነት የሚካሄደው የደቡብ ሱዳን ድርድር አዲስ አበባ ላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።»

ባራክ ኦባማ ጓዛቸውን ሸክፈው በኤርፎርስ ዋን ወደ አፍሪቃ መንገድ ከመግባታቸው በፊት ሂዩማን ራይትስ ዎችና ፍሪደም ሃውስን ጨምሮ አስራ አራት የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኬንያና ኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ልብ ቢሏቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ያሰፈሩበትን ደብዳቤ ጽፈው ነበር። በደብዳቤው ሁለቱ የምሥራቅ አፍሪቃ አገራት በብሄራዊ ደህንነት ስም መሠረታዊ ነጻነቶችን ነፍገዋል፤ ይህ ደግሞ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ከመጣስ ባሻገር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እንቅፋት ይሆናል ሲሉ ተችተዋል። ሌስሊ ሌፍኮ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በሚያደርጓቸው ውይይቶች አስራ አራቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ያነሷቸውን ትችቶች እንደሚመክሩባቸው ይጠብቃሉ።

«ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በስብሰባዎቹ የተለየ አቋም ያንጸባርቃሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ግልጽ መሆን ያለበት የኦባማ አመራር ብቻ ሳይሆን ከእሳቸው በፊት የነበሩትም ትኩረታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የጸጥታ እና የልማት ትብብር ነበር። የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በዲፕሎማሲ የሚታይ ይሆናል ብለው ያስቡ ነበር። እውነታው ግን ባለፉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ይዞታ በአሳሳቢ ሁኔታ ሲያሽቆለቁል ተመልክተናል። በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታና የፖለቲካ ምህዳር በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ እርስ በርስ ተቆላልፈዋል። እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ያለ የመናገርና የመሰብሰብ ነጻነትን በመከልከል ሰላማዊ፤ ሃብታምና የተረጋጋች ኢትዮጵያን እፈጥራለሁ የሚል ሌላ መንግስት ሊኖር አይችልም። እጅግ በጣም ውስን አቀራረብ ነው።»

ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት የእርዳታና ብድር ስምምነቶች፤ ጸረ-አሸባብና ሽብርተኝነት የሁለትዮሽ ዘመቻዎች ብቅ ሊሉ ይችላሉ። በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ይዞታ በተመከተ የሚያደርጉት ንግግር ወዲያው ለውጥ ባያመጣም ከፍ ያለ ትርጉም ይኖረዋል። «የአሜሪካን መሪ በአንተው አገር ላይ ሆኖ አንተኑ የሚተችም የሚያሞግስም ነገር ሲናገር ትልቅ ትርጉም ይሰጠዋል።» የሚለው መስፍን ነጋሽ እንደ ሌስሊ ሌፍኮሁሉ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ጠንከር ያለ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠብቃል። «ኦባማ አዲስ አበባ መጥቶ በኢትዮጵያ የሚታየውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የሚናገረው ነገር ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየተካሄደ እንደሆነ እውቅና እንደሚሰጥ የሚገልጽበት ንግግር ነው የሚሆነው።»

ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ቀን ውሏቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንቱ «ሁሉም ድምጾች ሲደመጡ፤ሰዎች በፖለቲካዊ ሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን ሲያውቁ አገር የበለጠ ስኬታማ ትሆናለች።» ሲሉ የገደምዳሜ ትችት ሰንዝረዋል። የፕሬዝዳንቱ አስተያየት ለብዙ ታዛቢዎች የሚያጠግብ አልሆነም። ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመከላከል ሞክረዋል።

በጉብኝታቸዉ መርሃግብር መሠረት ፕሬዝዳንቱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን በተናጠል ባያናግሩም የማህበረሰቡ ተወካዮች የተባሉ ሰዎች ያገኛሉ ተብሏል። በፕሬዝዳንትነት የስልጣን ዘመናቸው አራተኛውን ምናልባትም የመጨረሻውን የአፍሪቃ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአፍሪቃ ህብረት ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ። በጉባኤው በስልጣን ወዳድነት፤ ሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚታሙት መሪዎች መታደማቸው አይቀርም። አገራቸውም ለህብረቱ የሰጠችው ትኩረት አነስተኛ እና እጅጉን የዘገየ እየተባለ ይተቻል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic