አዲስ አበባ እና የሜትር ታክሲዎቿ | ኤኮኖሚ | DW | 30.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አዲስ አበባ እና የሜትር ታክሲዎቿ

የአዲስ አበባን የታክሲ አገልግሎት ለማዘመን አዳዲስ የአገልግሎት አቅራቢዎች ወደ ገበያው ብቅ ብለዋል። መንገደኞች ከአሽከርካሪዎች ጋር የሚያደርጉት ድርድር ቀርቶ በተጓዙት ርቀት የሚያስከፍሉት ኩባንያዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ለመሆኑ አዲስ አበባ ለአገልግሎቱ ምን ያክል ዝግጁ ነ?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:29
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:29 ደቂቃ

አዲስ አበባ ለሜትር ታክሲዎች ዝግጁ ናት?

ቢጫዎቹ የአዲካ ታክሲ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሞላቸው። የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቀላጠፍ እና ለማዘመን ካቀዱት መካከል አንዱ የሆነው ኩባንያ የተቋቋመው በጎርጎሳዊው ጥቅምት 2013 ዓ.ም. ነው። ዘርፉን በውጭ ባስገባቸው 25 ተሽከርካሪዎች በቀዳሚነት የተቀላቀለው ሸገር ሜትር ታክሲ የተሰኘ ኩባንያ ከዘመን ባንክ የተበደረውን ገንዘብ መመለስ ተስኖት ለኪሳራ ተዳርጓል። የአዲካ አስጎብኚ እና የጉዞ ወኪል እህት ኩባንያ የሆነው አዲካ ታክሲ አገልግሎት ሥራውን የጀመረው ዘመን ባንክ በጨረታ የሸጣቸውን የሸገር ሜትር ተሽከርካሪዎች  ገዝቶ ነበር።  አቶ ብዙአየሁ ታደሰ የአዲካ ታክሲ አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።  


የመንገድ ጭንቅንቅ በሚበዛባት አዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዘመን ዘርፉን በአዲስ ቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች የተቀላቀለው ግን አዲካ የታክሲ አገልግሎት ብቻ አይደለም። በዩናይትድ ስቴትስ የቦስተን ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሐብታሙ ታደሰ የመሰረቱት ዛይ ራይድ የተሰኘ አገልግሎት በምዕራባውያኑ ዘንድ ከተለመደው ኡበር ጋር ተመሳሳይነት አለው። አቶ ሐብታሙ የኢንተርኔት አገልግሎትን በመጠቀም ደንበኛ እና ተሽከርካሪዎችን የማገናኘት ስራን ከመጀመራቸው በፊት ነባሩ የታክሲ አገልግሎት ቋሚ የዋጋ ተመን እንዳልነበረው ታዝበዋል። እውነትም አዲስ አበባ መሸትሸት ሲል አልያም ዝናብ ሲጥል የ80 ብሩ ጉዞ እስከ 300 ብር ያሻቅባል። ክፍያው የሚወሰነው በድርድር ከመሆኑም ባሻገር መንገደኞች በፈለጉት ጊዜ እና ቦታ ተሽከርካሪዎች የማግኘት እድላቸው ጠባብ ነው። የአቶ ሐብታሙ ዛይ ራይድ መንገደኞች የሚያጉዝበት የራሱ ተሽከርካሪዎች የሉትም። አቶ ሐብታሙ እንደሚሉት ኩባንያው ያዘጋጀው የቅንጡ ስልኮች አፕሊኬሽን ደንበኞች እና አገልግሎት አቅራቢዎች ያገናኛል። 


ከአዲካ እና ዛይ ራይድ በተጨማሪ 18 ማህበራት የመሰረቱት ዘ-ሉሲ የተሰኘ ኩባንያም በቻይና ሰራሾቹ የሊፋን ተሽከርካሪዎች ገበያውን ተቀላቅሏል። አዲካ የታክሲ አገልግሎት አሽከርካሪዎቹ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛን መሰል ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ከደንበኞቻቸው መግባባት እንዲችሉ ሥልጠና መስጠቱን አቶ ብዙአየሁ ታደሰ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

 

 

Audios and videos on the topic