አዲስ ሳንካ- በደቡብ ሱዳን | አፍሪቃ | DW | 20.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አዲስ ሳንካ- በደቡብ ሱዳን

የደቡብ ሱዳን አማጺ ቃል አቀባይ ጄኔራል ሉል ሯይ ኩአንግ ከሪየክ ማቻር አፈነገጡ። ቃል አቀባዩ በደቡብ ሱዳን የኑዌር መንግስት የማቋቋም ሃሳብ አላቸው ተብሏል። ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በበኩላቸው የስልጣን ዘመናቸውን ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት የማራዘም ሃሳብ ይዘው ብቅ ብለዋል።

አስራ አራት ወራት ለዘለቀው የደቡብ ስዳን ቀውስ መፍትሄ ፍለጋ በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ተቀናቃኝ ሃይሎችን የማደራደር ጥረት በባለሙያዎች ደረጃ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ይጀመራል። ካሁን ቀደም የተደረጉ ስምምነቶችን ተፈጻሚነት ለመገምገም እና ቀጣይ አፈጻጸም ላይ ለመወያየት ቀጠሮ የተያዘለት ድርድር እንደታሰበው የሚሄድ አይመስልም። በሰላም ድርድሩ እና በተደራዳሪዎቹ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አዳዲስ ጉዳዮች ተከስተዋል። በኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም ዓቀፍ ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አቤል አባተ የሪየክ ማቻር ጦር ቃል አቀባይ የነበሩት ጄኔራል ሉል ሯይ ኩአንግ በጆንጊሌ ግዛት የኑዌር መንግስት የመመስረት አዲስ ሃሳብ ይዘው ብቅ እንዳሉ ይናገራሉ።

«ሰውየው ከኢትዮጵያ ቀጥታ ወደ ጁባ መሄዳቸውን አንዳንድ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። በመንግስት በኩልም ከፍተኛ አቀባበል እንደተደረገላቸው እየተወራ ነው።ኬንያ ውስጥ መግለጫ ሲሰጡ የዶ/ር ሪየክ ማቻር አካሄድ የሳቸውን ስልጣን ከማስጠበቅ ውጪ ምንም የዘለለ ትርጉም ስለሌለው በአሁን ሰዓት መውጣታቸውን አሳውቀዋል።ጆንግሌን ነጻ ግዛት በማድረግ የኑዌሮች መንግስት መመስረት እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል።»

የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ በበላይነት የሚመራው ድርድር ሐምሌ2 ፣2007የሽግግር መንግስት የመመሥረት ሃሳብ ሰንዝሮ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቷል ተብሎ ነበር። ካሁን ቀደም በተካሄደው ድርድር መሠረት ከሽግግር መንግስቱ በኋላ ምርጫ ለማስከተል የተያዘው እቅድ አሁን ተግባራዊ መሆን የሚችል አይመስልም። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የስልጣን ዘመናቸውን ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ለማራዘም ያቀረቡት ሃሳብ በመንግስታቸው ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ አቤል አባተ ይናገራሉ።

«የደቡብ ሱዳን ካቢኔ ተሰብስቦ የፕሬዝዳንቱን የስልጣን ጊዜ እስከ ሐምሌ 2017 ማራዘሙን አሳውቋል። አሁን በጁባ ያለው መንግስት ሙሉ በሙሉ የሚወከለው በሳልቫ ኪር ወገን እንደመሆኑ መጠን በህግ አውጪዎቹም በቀላሉ እንደሚያልፍ ይጠበቃል።»

ካሁን ቀደም ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና የተቃውሞ ጎራው መሪ ሪየክ ማቻር በዋናነት እና ገለልተኛ የሚባሉትን የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት በተጨማሪ ሲያሸማግል የቆየው የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ጄኔራል ሉል ሯይ ኩአንግ ተጨማሪ የቤት ሥራ ጨምረውበታል። የተኩስ አቁም ስምምነት፤ የመንግሥት የስልጣን ክፍፍል እና ምርጫን እያነሳ ሲጥል የከረመው የደቡብ ሱዳናውያን አተካሮ አሁን ያለበት ደረጃ ለአደራዳሪው መልካም ዜና አይመስልም። አቶ አቤል አባተ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚቀያየረው የደቡብ ሱዳን ሱዳን ተቀናቃኞች አቋም እና ግትርነት በድርድሩ እምነት እንዲያጡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። አቶ አቤል ካሁን ቀደም የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት አደራዳሪዎች ቀውሱን ለመፍታት ያቀረቧቸው ሃሳቦች እየተጣሱ እንደሆነ ይናገራሉ።

«አሁን በፕሬዝዳንቱ በኩል የታሰበው በመጪው ሐምሌ ምርጫ ለማካሄድ የያዘውን እቅድ የሚቃረን ነው። በተበታተኑ ቁጥር እያንዳንዱ ወገን የራሱን ፍላጎት ይዞ ስለሚመጣ ማደራደሩን ውስብስብ ያደርገዋል።»

ካርተር ማዕከል ተብሎ ለሚጠራው የዩ.ኤስ. አሜሪካ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተቀጣሪ እንግሊዛዊ በጁባ ከተማ በዚህ ሳምንት ከታጣቂ በተተኮሰ ጥይት መገደል ለደቡብ ሱዳን ሌላ መርዶ መሆኑን አቶ አቤል አባተ ተናግረዋል። እንግሊዛዊውን ጨምሮ በደቡብ ሱዳን በዚህ ዓመት ብቻ 14 የበጎ አድራጎት ድርጅት ሠራተኞች ተገድለዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic