1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በቀበሌ ደረጃ ያዋቀረው አዲስ መዋቅር

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28 2016

” እኔ አሁን እስካሁን ከየትኛውም ፖለቲካ ገለልተኛ ነኝ፡፡ በሙያተኝነት ነው ሳገለግል የቆየሁት፡፡ የአመራር ክህሎትም የለኝም፡፡ የውትድርና ስልጠናም አልተሰጠኝም፡፡ እንዴት ነው አስቸጋሪ የጸጥታ ሁኔታ ባለበት ላይ የአንድ ቀበሌ አስተተዳዳሪ ሁን የሚል ግዴታ የሚሰጠኝ” አንድ አስተያየት ሰጪ

https://p.dw.com/p/4kEFT
ጨፌ ኦሮሚያ
ጨፌ ኦሮሚያምስል Seyoum Hailu/DW

የኦሮሚያ ክልል አዲስ መዋቅር

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ መልክ በቀበሌ ደረጃ አዋቀርኩ ያለው አዲስ የቀበሌ መዋቅር ገቢራዊ መሆን መጀመሩ  ገልጿል።
በርካታ የወረዳ  ሰራተኞችን ወደ ቀበሌ በማሸጋሸግ ለህብረተሰቡ ቀረብ ብለው አገልግሎት በመስጠት እንዲያገለግሉ የሚል ዓላማን ያነገበ ነው የተባለው ይህ ውሳኔ ከወዲሁ በጎም ሆነ አሉታዊ ምላሾችን እያስተናገደም ነው፡፡
አሁን በቀበሌዎች ደረጃ ከከተማ ውጪ ያለው የጸጥታ ይዞታ ወደ ቀበሌ ደረጃ ወርደው አገልግሎት እንዲሰጡ የተባሉትን የመንግስት ሰራተኞች ቢያሰጋም፤ መንግስታዊ አገልግሎቶች በቀበሌ ደረጃ ወርዶ ለህብረተሰቡ እንዲሰጡ የተዘረጋው አሰራር ግን  ውጤት ሊኖረው እንደሚችል በክልሉ መንግስት በኩል ታምኗል፡፡
አዲስ የቀበሌ ደረጃ መዋቅር ለምን? 
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቀደም ሲል በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ  “መንግስታችን ትኩረቱ ቀበሌ ላይ ነው፡፡ በገጠርም ይሁን በከተማ ህዝባችን ያለው በቀበሌ ስለሆነ ያለውን አቅም በሙሉ ወደ ቀበሌ አውርደን የምንሰራ ይሆናል፡፡ ህዝባችን፣ አመራሩና ሲቪል ሰራተኛው በዚህ ላይ የላቀ ትኩረት ይስጥ”፡፡ ብለው ነበር።
ርዕሰ መስተዳድሩ ትናንት አመሻሹን በተረጋገጠው ይፋዊ ማህበራዊ ገጻቻው ላይ “የቀበሌ መንግስት ህዝባዊ መንግስት” የሚል ርዕስ ሰጥተው በለቀቁት ዘለግ ባለው ጽሁፍም አዲስ ወደ ቀበሌ ደረጃ የወረደው የመንግስት መዋቅር፤ ትልቅ ስርዓታዊ ለውጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ጠንካራ ስርዓት፣ በምጣኔሃብት የዳበረ ማህበረሰብ ለመገንባት እና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ይረዳል ያሉትን ይህን ስርዓት ያለ ምንም ማንገራገር ተፈጻሚ እንዲሆንም ርዕሰ መስተዳድሩ በአጽእኖት አስቀምጠዋል፡፡ 


“መተዳደርም፤ ማስተዳደርም ቀበሌ ነው” 
“መተዳደርም፤ ማስተዳደርም ቀበሌ ነው” የሚል መፈከር የተሰጠው ይህ የቀበሌ ደረጃ መንግስታዊ አደረጃጀት በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች ወደ ገቢራዊነት እየገባ መሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡ በትናንትናው እለት የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ሽፋን የሰጠውና በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በተገኙበት በምስራቅ ሀራርጌ ዞን ሀሮማያ ወረዳ “ኢዶ በሊና” በሚል በአዲስ መልክ የተዋቀረ ቀበሌ ላይ በተገኙበት ወቅት የአዲሱ የቀበሌ መዋቅር አስፈላጊነት አብራርተዋል፡፡ “ዲሞክራሲ መሬት የሚይዘው፤ እውነተኛ ዲሞክራሲ የሚረጋገጠው መንግስት ለህዝቡ ቀረብ ብሎ መስራት ሲችል ነው” ያሉት አቶ አዲሱ መንግስታቸው የቀበሌ መዋቅር ማጠናከርን “የአዲስ ምዕራፍ ድል” አድርጎ እንደሚወስደው አንስተዋል፡፡ ዲግሪና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ላይ ሆነው የአመራር ልምድ ያላቸው ወጣቶች ህዝባቸውጋ ተጠግተው እንዲሰሩ የሚያስቻል አዲስ ምእራፍ ነውም ብለውታል፡፡ 


በቀበሌ ደረጃ መዋቅሩ የተዘጋጀው ሰነድ ስላስነሳው ስጋት
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የወረዳዎች እና ቀበሌዎች ሪፎርም በሚል ያዘጋጀው ሰነድ በሶስተኛ አንቀጹ ላይ የዚህ መዋቅር ዓላማ በቀበሌ ደረጃ ጠንካራ መንግስት በማዋቀር የህብረተሰቡን የመልማት፣ የሰላምና ጸጥታ ብሎም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት ነው ይላል፡፡ “ህገመንግስትን መሰረት ያደረገ ነው” የተባለው አደረጃጀቱ ሶስቱ የመንግስት መዋቅሮችም እንደሚኖሩትና የቀበሌ አስተዳዳሪን ጨምሮ ብያንስ ሰባት የአመራር እርከኖች ያሉት እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
አደረጃጀቱን ተከትሎ እየተፈጸሙ ባሉ የመንግስት ሰረተኞች አመዳደብ ላይ ግን ከወዲሁ ጥያቄ መነሳት ጀምሯል፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው ስጋታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ አንድ የሰሜን ሸዋ ዞን የመንግስት ሰራተኛ፤ ባሁን ወቅት ወደ ቀበሌ ለመሄድ አንዱ ስጋት ጸጥታ ሲሆን አመዳደብ ላይ የሚታይ ያሉት “አድሎ”  ስጋትን አጭሯል፡፡ 
አስተያየት ሰጪው አዲሱ የቀበሌ መዋቅር  “ማንም ተቀብሎ ሊሰራበት የሚገባው መመሪያ እንደሆነም ነው የማምነው” ይላሉ፡፡ ነገር ግን ቅሬታው ያለው ከወዲህ ነው ይላሉ አሰርተያየት ሰጪው፤ “በሰዎች አመራረጥና አመዳደብ ላይ ፖለቲካውን እንዳሻቸው የሚዘውሩ ሰዎች በአቀራረብ ሁኔታ የሚፈልጉትን ቀረብ ወዳለ ቀበሌ የማይፈልጉትን ወደ ሩቅ ቦታዎች እየመደቡ መሆኑ ነው ቅሬታ የሚያስነሳው፡፡ ሌላው የጸጥታው ሁኔታ በብዙ ቀበሌ ከባድ ነው፡፡ እኔ አሁን እስካሁን ከየትኛውም ፖለቲካ ገለልተኛ ነኝ፡፡ በሙያተኝነት ነው ሳገለግል የቆየሁት፡፡ የአመራር ክህሎትም የለኝም፡፡ የውትድርና ስልጠናም አልተሰጠኝም፡፡ እንዴት ነው አስቸጋሪ የጸጥታ ሁኔታ ባለበት ላይ የአንድ ቀበሌ አስተተዳዳሪ ሁን የሚል ግዴታ የሚሰጠኝ” ሲሉ አስተያየት አዘል ጥያቄ አንስቷል፡፡
ስለ አዲሱ የቀበሌ መዋቅር ላይ ስለሚነሱ ጥያቄዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ለክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ እና ምክትላቸው በመደወልና መልእክትም በመላክ ጥረት ብናደርግም ለዛሬ አልሰመረልንም፡፡ 
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ