አዲሱ የጀርመን ጥምር መንግሥት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 17.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

አዲሱ የጀርመን ጥምር መንግሥት

የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምርጫ አሸናፊ የክርስቲያን ዲሞክራት ሕብረት ፓርቲ መሪ አንጌላ ሜርክልም ዛሬ ቃለ መሃላ በመፈፀም የመራሄ መንግሥትነቱን መንበር ለ3ተኛ የስልጣን ዘመን በይፋ ተረክበዋል ። የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ፣ በሰጠው ድምፅ የመረጣቸው ሜርክል ትልቁን ተጣማሪ መንግሥት ለሚቀጥሉት አራት አመታት ይመራሉ ።

ተጣምረው መንግሥት የመሰረቱት ትላልቆቹ የክርስቲያን ዲሞክራት ህብረትና የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት እንዲሁም የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፖርቲዎች ከመንግሥት ምስረታው ድርድር ያገኙትና ያጡት እንዲሁም የአዲሱ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ይዘት የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ያስቃኘናል ። በጀርመን የዲሞክራሲ ታሪክ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትላልቆቹ ፓርቲዎች የተጣመሩበት መንግሥት ሲመሰረት የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው ። የክርስቲያን ዲሞክራቶች ህብረት በምህፃሩ CDU ና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት CSU ፓርቲዎች እንዲሁም የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ በምህፃሩ SPD ለመጨረሻ ጊዜ ሃገሪቱን ተጣምረው ያስተዳደሩት በሜርክል መራሂተ መንግሥትነት በጎርጎሮሳውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ2005 እስከ 2009 ዓም ነበር ።

የመጀመሪያው ትልቁ የጀርመን ጥምር መንግሥት ደግሞ በጎርጎሮሳውያኑ 1966 ተመሥርቶ እስከ 1969 የዘለቀውና በCDU ው ኩርት ጌኦርግ ኪሲንገር የተመራው መንግሥት ነው ። የአሁኑ ትልቅ መንግሥት መሥረታ እውን የሆነው 3 ወራት ከወሰደ ድርድር በኋላ ነበር ። የመስከረሙን የምክር ቤት ምርጫ እህትማማቾቹ CDU እና CSU አብላጫ ድምፅ አግኝተው ቢያሸንፉም በምክር ቤቱ የበላይነቱን ለመያዝ የሚያስችላቸው 5 መቀመጫዎች በመጉደላቸው ተጣማሪ ከመፈለግ ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም ። ባለፈው መንግሥት ከእህትማማቾቹ ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ ያስተዳደረው የነፃ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ በምህፃሩ FDP በመስከረሙ ምርጫ ምክር ቤት ውስጥ መግባት የሚያስችለውን 5 በመቶ ድምፅ ባለማግኘቱ ፣ CDU እና CSU በምርጫ ሁለተኛ ደረጃን ካገኘው ከSPD ጋር ለመጣመር ሃሳብ አቀርቡ ። SPD ሃሳቡን ቢቀበልም ጥምር መንግሥት ከመመስረቱ በፊት ወደ 475 ሺህ የሚጠጉትን የፓርቲውን አባላት ይሁንታ እንደ ቅድመ ግዴታ አስቀምጦ ድርድሩ ተጀመረ ። ሶስት ወራት ከዘለቀ ንግግር በኋላ ባለፈው ቅዳሜ የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ አባላት በሰጡት ድምፅ ስምምነታቸውን ከተረጋገጠ በኋላ ትናንት የጥምር መንግሥቱ ውል ፀድቋል ። እነሆ ዛሬም የክርስቲያን ዲሞክራቶች ፓርቲ መሪ አንጌላ ሜርክል ከጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት በ462ቱ የድጋፍ ድምፅ ከተመረጡ በኋላ የመራሄ መንግሥትነቱን መንበር ለ 3ተኛ ጊዜ ተረክበዋል ። አዲሱ ጥምር መንግሥትም እንደተጠበቀው በጎርጎሮሳውያኑ 2013 መገባደጃ ተመስርቷል ። በጥምር መንግሥት ምሥረታ ድርድር ስምምነት የተደረሰባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ምን እንደሆኑና የተደራደሩት ፓርቲዎች ያጡትና ያገኙትን ፍራንክፈርት ጀርመን ነዋሪ የሆኑት የፖለቲካ ሳይንስ ና የህግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ይገልጹልናል ።

ሁለቱ ፓርቲዎች ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ቢስማሙም በተለይ ለሃብታሞች ቀረጥ እንዳይጨመር የደረሱበት መግባቢያ መንግሥትን ለተጨማሪ ወጭ መደረጉ አይቀርም ይህ ደግሞ ዶክተር ለማ እንደሚሉት መንግሥትን ችግር ውስጥ ሊጥል ይችል ይሆናል።በአዲሱ የጀርመን ትልቅ ጥምር መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነባርና አዳዲስ ሚኒስትሮች ይገኙበታል ። ከቀደመው የሚኒስትርነት ኃላፊነታቸው ወደ ሌላ የተዛወሩም አሉ ። የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሁም መሠረታቸው ቱርክ የሆነ የመጀመሪያዋ ሚኒስትርም ተሹመዋል ። በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ተመርጠው ቃለ መሃላ የፈፀሙት አንጌላ ሜርክል በቀደሙት ሁለት ዘመነ ሥልጣናቸው ያተኮሩት በዓለም ዓቀፉ የፋይናንስ ቀውስና መፍትሔዎቹ ላይ ነበር ። አሁን ግን ፊታቸውን ይበልጡን ወደ ሃገር ውስጥ ጉዳዮች ያዞራሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው ። በአዲሱ ምክር ቤት CDU/CSU እና SPD ከጀርመን ምክር ቤት መቀመጫ 80 በመቶውን ይይዛሉ ። ሆኖም በምክር ቤቱ ግራ ዘመም አቋም ያላቸው ማለትም SPD የአረንጓዴዎቹ ፓርቲና ግራዎቹ ከምክር ቤቱ 631 መቀመጫዎች 320 ውን መያዛቸው ምናልባት አሁን ሥልጣን በሚይዘው በሜርክል አስተዳደር ላይ ጫና መፍጠር ያስችላቸዋል የሚል ስጋት አለ ። ዶክተር ለማ ግን ሜርክል እንደ ከዚህ ቀደሙ ችግር ሳይገጥማቸው መጪውን 4 ዓመት ሊወጡ ይችላሉ ይላሉአንጌላ ሜርክል ከ1949 እስከ 1963 የጀርመን መራሄ መንግሥት ከነበሩት ከCDU ው ከኮናርድ አደናወር እና እጎአ ከ 1982 - እስከ 1998 ሥልጣን ላይ ከቆዩት ከCDU ው ከሄልሙት ኮል ቀጥሎ በጀርመን ታሪክ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን በመመረጥ ሶስተኛዋ መራሂተ መንግሥት ናቸው ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic