አዲሱ የጀርመን የተገን አሰጣጥ ሕግ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 20.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

አዲሱ የጀርመን የተገን አሰጣጥ ሕግ

የጀርመን የህዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ባለፈው ሳምንት አዲስ የተገን አሰጣጥ ሕግ አፅድቀዋል። አዲሱ ሕግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም ከልዩ ልዩ የስደተኞች መርጃ ድርጅቶች ትችቶች ተሰንዝሮበታል። ጀርመን የሚገባው ስደተኛ ቁጥር እየጨመረ ከሄደ በኋላ ጀርመን ያወጣችው ጥብቅ የተባለው አዲስ የተገን አሰጣጥ ሕግ እያነጋገረ ነው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:31

የጀርመን የተገን አሰጣጥ ሕግ

ከዚህ ሕግ ዓላማዎች ውስጥ የተገን አሰጣጥ ሂደትን ማፋጠንና ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን በአስቸኳይ ወደ ሃገራቸው ማባረር በዋነኛነት ይጠቀሳሉ ። በሌላ በኩል አዲሱ ሕግ ስደተኞች ከህብረተሰቡ ጋር በተቻለ ፍጥነት ተቀራርበውና ተዋህደው እንዲኖሩም ያግዛሉ የተባሉ ማሻሻያዎችንም አካቷል ። አዲሱ ሕግ ከቀድሞው በምን ይለያል? ማሻሻያዎቹስ ምንድን ናቸው ? ። የሕግ ባለሞያውና ና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ አዲሱን ሕግ ከቀደመው ጋር በማነፃፀር ያስረዱናል ።አዲሱ ሕግ የስደተኞች የተገን ጥያቄ ቶሎ ውሳኔ እንዲያገኝ ከማድረጉም በተጨማሪ ለዜጎቻቸው አያሰጉም ወይም የሕግ የበላይነት ይከበርባቸዋል ያላቸውን ሃገራትንም ለይቶ ዘርዝሯል።የፌደራል ጀርመን መንግሥት አሁን ወደ ጀርመን በጎረፈው ስደተኛ ምክንያት በጎርጎሮሳውያኑ 2015 ና 2016 ለሚያስፈልገው ወጪ የሚውል ለፌደራል ክፍላተ ሃገራት የሚሰጥ 6 ቢሊዮን ዩሮ መድቧል ። ለስደተኞች ገንዘብ ወጪ የሚደረግበት መንገድና የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ በአዲሱ ሕግ ከተለወጡት ውስጥ ይካተታሉ። አዲሱ ሕግ ከ631 የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የ475ቱን አባላት ድምፅ አግኝቶ በፀደቀው በአዲሱ ሕግ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ውስጥ የቋንቋ ትምህርት አሰጣጥም ይገኝበታል ።

ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ጀርመን የገባውና ፣ እስከ ዛሬ 2 ወር ተኩል ግድም ድረስ ጀርመን ይይመጣልል ተብሎ የሚጠበቀው ስደተኛ ቁጥር ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል ። ከመካከላቸው ጀርመን አገር መቆየት ይችላሉ ተብሎ የሚወሰንላቸው ተገን ጠያቂዎች ወዲያውኑ የቋንቋ ትምህርት እንዲያገኙ ከመፈቀዱ በተጨማሪ አዲሱ ሕግ የመሥራት መብትም ይሰጣቸዋል ።እነዚህን የመሳሰሉ ለውጦች የተደረጉበት አዲሱ የተገን አሰጣጥ ሕግ የተገን ጠያቂዎችን መብት በመጣስ በጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲዎችና በስደተኞች መብት ተሟጋቾች እየተቸቸ ነው ። እነዚህ ወገኖች ስደተኞች እስከ 6 ወር ለሚጠጋ ጊዜ በአንድ ማዕከል እንዲቆዩ መደረጉን ፣ለተገን ጠያቂዎች ጥሬ ገንዘብ መስጠት መቅረቱን ፣የተገን ጥያቄያቸው ውድቅ የሆነ ስደተኞች ደግሞ ጀርመንን ለቀው ካልወጡ ምንም ዓይነት ጥቅማ ጥቅሞች እንዳያገኙ መደንገጉን ህገ መንግሥቱን የሚቃረን ሲሉ ተቃውመውታል ።ዶክተር ለማ ደግሞ ሕጉ ሳይሠራ ገንዘብ ለማግኘት አልሞ ለሚመጣው ስደተኛ ቅስም ሰባሪ ፣ ሠርቶ ለማደግ ለሚፈልግ ግን ጥሩ አጋጣሚ ነው ይላሉ ።አዲሱ የጀርመን የተገን አሳጣጥ ሕግ ከ11 ቀናት በኋላ ሥራ ላይ ይውላል ።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic