አዲሱ የደመወዝ ጭማሪ መዘግየት ያስከተለው ቅሬታ
ረቡዕ፣ ኅዳር 18 2017
መንግሥት የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ባለፈው ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ገልጧል። ያን ተከትሎም በማኅበራዊ መገናኛ ተለቀቀ የተባለውን የጭማሪ ሰንጠረዥ እየተመለከተ የደመወዝ መጠኑ የት ላይ እንዳለ ጭምር እያየና እየመዘነ «መቼ ይሆን ኪሴ የሚገባው» እያለ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረው ሠራተኛ ቁጠር ቀላል አልነበረም።
«ጭማሪው እንዲያውም ያለንን ወስዶብናል» ሠራተኞች
«ጥቅምት ወር ላይ ክፍያ እንደሚፈፀም ጠብቀን ነበር» የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የደመወዝ ይጨመራል ዜና ክፍያው ሳይፈፀም መነገሩ በሽቀጦች ላይ ዋጋ እንዲንር ምክንያት ሆኗል፣ «እንዲያውም ያለንን ወስዶብናል» ይላሉ። ይህን አስተያየት ከሰጡን ሠራተኞች መካክል በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደብረወርቅ ከተማ ነዋሪ አንዱ ናቸው። እንደ አስተያየት ሰጪው፣ የደመወዝ ጭማሪውን የሚያሳየው ደብዳቤ ወደ ወረዳው ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት አልደረሰም፣ የሚታሰብም አይደለም። ለኑሮ ውድነት ግገን ዳርጎናል ይላሉ።
ጭማሪ የተባለው መንግሥት በአገልግሎት ዘርፉ ለጨመረው ዋጋ ማካካሻ ይመስላል ተብሏል
የሰሜን ወሎ የመንግሥት ሠራተኛ በበኩላቸው፣ መንግሥት በውሀ፣ በኤሌክትሪክ በቴሌፎንና በሌሎች አገልግሎቶች ላይ ጭማሪ አድርጎ ደመወዝ ጨመርኩ ማለቱ እንደማካካሻ የሚታይ ነው የሚሉት ወገኖች፤ እንደውም ተጨምሯል የተባለው ደመወዝ በእጅ ባለመግባቱ ኑሯቸውን እንዳመሰቃቀለባቸው አብራርተዋል። ጭማሪውን በጉጉት ሲጠብቁ ቢቆዩም መዘግየቱ፣ ለዋጋ መጨመር ምክንያት መሆኑ ተስፋ አስቆርጦናልም ነው ያሉት።
የደመወዝ ጭማሪ ዜና ቀድሞ መነገሩ ለዋጋ መጨመር ምክንያት ሆኗል
ያሉበት አካባቢ እንዳይገለጽ የፈለጉ ሌላ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኛ ክፍያው መዘግየቱን ጠቅሰው፣ ሠራተኛውን የሚጠቅመው ከደመወዙ ይልቅ የግብር ቅነሳ ነበር ብለዋል። ደመወዝ ይጨመራል ተብሎ ቀድሞ መነገሩም ትክክል እንዳልነበር ነው ያስረዱት። ሌላው የምዕራብ ጎጃም አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የመንግሥት ሠራተኛው፣ በኑሮ መማረሩንና የሚጠብቀው ደመወዝም በእጁ ሊገባ አልቻለም ነው ያሉት።
ጭማሪው ቀርቶ ብዙዎቹ የነበረውን ደመወዝ በአግባቡ እያገኙ እንዳልሆነና ወደ የመንግሥት ሠራተኛው ይልቁንም ወደ ሌሎቸ አማራጮች እየሄደና የመንግሥት ሥራ የመጨረሻ አማራጭ እየሆነ መጥቷልም ብለዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጡን ለአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ ደውለን ጉዳዩ ቢሮውን እንደማይመለከት አንድ የቢሮው ከፍተኛ ባለሥልጣን ነግረውናል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ኃላፊ ወ/ሮ ባንቺአምላክ ገ/ማሪያም በበኩላቸው ስብሰባ ላይ በመሆናቸው አስተያየት ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጠዋል።
ጭማሪው በክልል ምክርቤት ከፀደቀ በኋላ በቅርቡ ይከፈላል
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ታደለ ልይለት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ክፍያውን ማዘግየቱን አመልክተው አሁን ግን ሥራዎች እየተጠናቀቁ በመሆኑ ክፍያ በቅርቡ ይከናወናል ብለዋል።c
መረጃ አደራጅተው ለሚመለከተው አካል ማስረከባቸውን የተናገሩት አቶ ታደለ፣ ገንዘቡ ተፈቅዶ ወደ ክልሉ ሲመጣ በክልሉ መንግሥት ከፀደቀ በኋል ለተፈቀደላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ክፍያው ይፈፀማልም ብለዋል።
በአማራ ክልል የመንግሥት ተሿሚዎችን ጨምሮ 520 ሺህ የመንግሥት ሠራተኞች እንደሚገኙ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ፀሐይ ጫኔ