አዲሱ የ«ዩ ቲዩብ» አፕልኬሽን | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 02.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አዲሱ የ«ዩ ቲዩብ» አፕልኬሽን

ጉግል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪካ ተኮር የሆኑ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ይገኛል፡፡ የጉግል ዋና ስራ አስፈጻሚ ባለፈው ሳምንት ወደ ናይጄሪያ ብቅ ብለው ኩባንያው ለአፍሪካ ያሰባቸውን እቅዶች እና አገልግሎቶች ይፋ አድርገዋል፡፡ ከአገልግሎቶቹ ውስጥ ለአፍሪካ የኢንተርኔት ፍጥነት እና የተስማማ የዩ ቲዩብ መተግበሪያ (አፕልኬሽን) አንዱ ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:05

አፕልኬሽኑ ለአፍሪካ የኢንተርኔት ፍጥነት የተስማማ ነው

አሊባባ የተሰኘው የቻይናው የኢንተርኔት ግብይት ኩባንያ መስራች ጃክ ማ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በኬንያ መዲና ናይሮቢ በአንድ መድረክ ላይ በተገኙበት ወቅት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ የመጡት የኩባንያው ስራ አስፈጻሚ ሊቀመንበር ወደ ሩዋንዳም ተሻግረው ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የሰውየው ጉብኝት ዜና ሳይደበዝዝ የሌላኛው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጉግል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሱንዳር ፒቻይ ወደ ናይጄሪያ መጓዛቸው ተነገረ፡፡ 

ሁለቱ የግዙፍ ኩባንያ ሃላፊዎች በየሀገራቱ በነበራቸው ቆይታ ደጋግመው ሲያነሱ የነበረው በርካታ ሚሊዮን የአፍሪካ ወጣቶች ከቴክኖሎጂ ጋር የሚተሳሰሩበትን እቅድ እና ሊያደርጓቸው ስላሰቧቸው ድጋፎች ነው፡፡ የአሊባባው ጃክ ማ ለወጣት የስራ ፈጣሪዎች የሚሆን 10 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደመደቡ አሳውቀዋል፡፡ የጉግሉ ፒቻይ በበኩላቸው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 10 ሚሊዮን አፍሪካውያንን የዲጂታል ክህሎቶች ባለቤት እንዲሆኑ ስልጠና ለመስጠት ማቀዳቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ በመላው አህጉሪቱ መቶ ሺህ የሶፍት ዌር ሰሪዎችን ለማፍራትም ሀሳብ አላቸው፡፡ 

ጉግል እቅድ ብቻ ሳይሆን በተግባር የጀመራቸውን አፍሪካ ተኮር ምርቶቹን እና አገልግሎቶቹን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ፣ ሐምሌ 20፣ በሌጎስ ከተማ በተካሄደ ስነስርዓት ይፋ አድርጓል፡፡ አርባ ዶላር ገደማ ዋጋ ያለው ለናይጄሪያ ገበያ ተብሎ በጃፓን እየተመረተ ያለው የጉግል ስልክ አንዱ ነው፡፡ ጉግል የሌጎስ መንገዶችን በጉግል ካርታ ላይ በዝርዝር እንዲታዩ ማድረጉ ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከሁሉም በላቀ ግን የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የአፍሪካን ዘገም ያለ የኢንተርኔት ፍጥነት ታሳቢ ያደረገ አዲሱ የዩ ቲዩብ መተግበሪያ (አፕልኬሽን) ነው፡፡ ከጎርጎሮሳዊው 2006 ጀምሮ የጉግል ንብረት የሆነው ዩ ቲዩብ ለናይጄሪያ ገበያ ምን ይዞ እንደመጣ የድርጅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዮሃና ራይት እንዲህ ነበር የገለጹት፡፡ 

“በቀጣዩ ትውልድ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ንሻጤ (inspiration) አዲስ አፕልኬሽን እየሰራን መሆናችንን ሳሳውቅ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ዩ ቲዩብ ጎ ብለነዋል፡፡ አፕልኬሽኑን ለግብረ መልስ ፍለጋ በህንድ ለቅቀነው ነበር፡፡ ብዙ እየተማርንበት ነው፡፡ በናይጄሪያም ከሰኔ ወር ጀምሮ ሙከራ እያደረግን መሆናችንን ሳሳውቅ በደስታ ነው፡፡ እንደዚህ በተከታታይ ሙከራ ስናደርግ ይህ ሁለተኛው ቦታችን ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሙከራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው” ብለዋል ዮሃና፡፡ 

ምክትል ፕሬዝዳንቷ በሌጎሱ ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት አሁን በናይጄሪያ የጀመሩትን ሙከራ ማስፋት ይሻሉ፡፡ ከተጠቃሚዎች ግብረ መልስ ለመሰብሰብ እንዲረዳቸው አፕልኬሽኑን ከጎርጎሮሳዊው 2017 መጨረሻ በፊት ተጠቃሚዎች ዘንድ የማድረስ ዓላማ አላቸው፡፡

“ዩ ቲዩብ ጎ” እንደ ናይጄሪያ ዝቅተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት ላለባቸው ሀገራት የተሰራ ነው፡፡ ይህ አፕልኬሽን ከመደበኛው ዩ ቲዩብ ከሚለየው ባህሪያት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ተጠቃሚዎች አንድን ቪዲዮ በፈለጉት የጥራት ልክ ወደ ኮምፒውተራቸው ወይም ስልካቸው እንዲገለብጡ ማስቻሉ ነው፡፡ በመደበኛው ዩ ቲዩብ ተጠቃሚዎች እንደ ኢንተርኔታቸው ፍጥነት አንድን የቪዲዮ ጥራት መጠን እየለዋወጡ መመልከት ብቻ ነው የሚችሉት፡፡ ሁለተኛው የ“ዩ ቲዩብ ጎ” ጠቀሜታ ደግሞ አንድን ቪዲዩ መመልከት ከመጀመራቸው አሊያም ከመገልበጣቸው በፊት በthumbnail ደረጃ ቅድመ ዕይታን መፍቀዱ ነው፡፡ “ዩ ቲዩብ ጎ” ተጠቃሚዎች አንዴ የተመለከቱትን ቪዲዮ ያለ ኢንተርኔት ግንኙነት ድጋሚ አንደሚለከቱ ያስችላቸዋል፡፡ ለጓደኞቻቸውም እንዲያጋሩ እድል ይሰጣል፡፡ 

ጉግል ለአፍሪካ ዘገምተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት መፍትሄ ያለውን ይዞ ቢመጣም እንዲህ አይነት ተነሳሽነት በመውሰድ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ እንደ ማይክሮሶፍት እና ፌስ ቡክ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ለአፍሪካ ይሆናል ያሉትን የአገልግሎት ማሻሻያዎች ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ጉዳዮች አማካሪው ነቢዩ ይርጋ ከቀርፋፋ ኢንተርኔት ጋር በተያያዘ ፌስ ቡክ በኢትዮጵያ ያከናወነውን እንዲህ ያስታውሳል፡፡ 

“ሰው ኢንተርኔት በደንብ እንዲጠቀም ዕድሉን ለመስጠት እንደ እርሱ ዓይነት ትልልቅ ኩባንያዎች ሀሳብ አላቸው፡፡ ፌስ ቡክም የዛሬ ሁለት ዓመት መጥቶ ይሄን ሰርቶ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ የሰሩት ነገር ምንድነው? እዚህ መጥተው የሞባይል ኢንተርኔት ሲጠቀሙ፣ በጣም ብዙ ሲቆጥርባቸው ያለውን ነገር ወደ ኋላ ተመልሰው ማየት ጀመሩ፡፡  ያሉት የፋይል ፎርማቶች በጣም ትልልቅ ስለሆኑባቸው፣ ስለተቸገሩ እርሱን ቀናንሰው መስራት ጀምረው ነበር፡፡ አዳዲስ የፈጠሯቸው የፋይል አይነቶች (ፎርማቶች) የምስል፣ ድምጽን፣ ቪዲዮን ድሮ ከነበራቸው አሳንሰውት አሁን በደንብ ለመጠቀም እንዲያመች አድርገውታል፡፡ የማየው ነገር ትልቅ ከሆነ ወጪ ያስወጣኛል፡፡ ስለዚህ ያንን ነገር ከመጠቀም ወደ አለመጠቀም የመሄድ ዕድሌ በጣም የበዛ ነው፡፡ እነዚህን ፎርማቶች ማስተካከል እንግዲህ አፍሪካ መጥተህ ስትጠቀም ላለው ችግር እንዲሆን ነው” ይላል ነቢዩ፡፡  

በዘገምተኛ ኢንተርኔትም ቢሆን አፍሪካውያን የማህበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየጨመረ መምጣት እንደ ፌስ ቡክ እና ዩ ቲዩብ/ጉግል ያሉ ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ ለመሳባቸው እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ እንደ ጉግል ኩባንያ መረጃ ከሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአፍሪካ አህጉር የተጫኑ የቪዲዮ ይዘቶች በእጥፍ ጨምረዋል፡፡ በአህጉሪቱ ተንቃሳቃሽ ስልኮች የሚታዩ ቪዲዮዎች የዕይታ ጊዜም በአንድ ዓመት ውስጥ በ120 ፐርሰንት አሻቅቧል፡፡ በኢትዮጵያም በዩ ቲዩብ የሚጫኑ ይዘቶች በየጊዜው እየጨመሩ እንደመጡ የቴክኖሎጂ አማካሪው ነቢዩ ይናገራል፡፡ ምክንያቶቹን እንዲህ ይዘረዝራል፡፡ 

“በፊት ብዙውን ጊዜ ኢንተርኔት ላይ የምንጠቀማቸው ነገሮች ለምሳሌ ፎቶ እና ጽሁፍ መላላክ ወይም መቀባበል፣ በእርሱ ላይ መወያየት ነበር፡፡ የቪዲዮ እና የእዚህ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ በደንብ እየሰፋ ሲመጣ ለሁሉ ሰው በደንብ ለማድረስ በተለይ ደግሞ ከሀገር ውጭ ላሉ ሰዎች [ተመራጭ ሆኗል]፡፡ በቴሌቪዥን ቢታይ በሀገር ውስጥ ነው የምታየው፡፡ ሀገር ውስጥ የሚታዩትን ውጭ ላሉ ሰዎች ማሳየት አትችልም፡፡ ለምሳሌ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ (አረብ ሀገራት) ያሉ ሰዎች ማየት ቢፈልጉ ኢንተርኔት ላይ ገብተው ነው የሚያዩት፡፡ ስለዚህ ኢንተርኔት ላይ የምታየው ከሆነ አነዚያን የምታያቸውን ነገሮች ዩ ቲዩብ ላይ ባስቀምጥልህ በደንብ ታያዋለህ፣ ከሰው ጋር አንደፈለግህ መላላክ ትችላለህ፡፡ ውጭ ከሆንህም ከእኛ ሀገር ካለው ኢንተርኔቱ የፈጠነ ስለሆነ በደንብ ዘና ብለህ፣ ጥራቱ በጨመረ መልኩ ታየዋለህ፡፡ ድሮ እንግዲህ መገናኛ ብዙሃን የምንለው (ቴሌቪዥን እና ሬድዮ) አንዴ ነው የምታየው፣ የምትሰማው፡፡ መድገም ከፈለግህ የሆነ ሰዓት መጠበቅ አለብህ፡፡ ኢንተርኔት የሚሰጠህ መብት ወይም ጥቅሙ ምንድነው? ለምሳሌ ወደ ፈለገኸው ደቂቃ መመለስ፣ አቋርጠህ ካቆምክበት መቀጠል፣ ለፈለግኸው ሰው ማቀበል ትችላለህ፡፡ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ዩ ቲዩብን በደንብ ለመጠቀም አቅልለውታል፡፡ ጥሩ አድርገውታል” ይላል የቴክኖሎጂ ጉዳዮች አማካሪው፡፡         

አንድ የዩ ቲዩብ ቻናል በደንብ ተመልካች ካለው ዩ ቲዩብ ራሱ በየቪዲዮዎቹ ማስታወቂያ እያደረገ በተመልካች ልክ መክፈሉም ሌላው ማበረታቻ እንደሆነ ነቢዩ ያነሳል፡፡ ቪዲዮዎቹን የሚያቀርቡት ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ይህን አውቀው ከድርጅቱ ጋር የሚስተካክሉት ነገር በአግባቡ መፈጸም ከቻሉ በደንብ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ባይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ቪዲዮዎች በዩ ቲዩብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾች እያገኙ መምጣታቸውን በማንሳትም የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት እንዴት ነገሮች እየተመቻቹ እንደመጡ ያብራራል፡፡ 

ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ከሚሆኑ የዩቲዩብ ገጾች መካከል አንዱ “ሆፕ ሙዚቃ” የተሰኘው ገጽ ነው፡፡ መቀመጫውን ፊንላንድ ባደረገው ሆፕ ኢንተርቴይመንት ስር ያለው ይህ ገጽ አዳዲስ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን በመጫን ይታወቃል፡፡ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ኃላፊ ብሩክ ተከስተ እንደሚናገሩት ድርጅታቸው ከዘፋኞች ጋር በመጣመር የቪዲዮ ክሊፖችን ያዘጋጃል እና ተሰርተው የመጡለትንም ይገዛል፡፡ በዚህም መሰረት በየቀኑ አዳዲስ ሙዚቃዎችን በዩቲዩብ ቻናሉ ላይ ያቀርባል፡፡ 

ሆፕ ሙዚቃ ኢትዮጵያ ቻናል 231 ሺህ ገደማ የተመዘገቡ ተመልካቾች ቢኖሩትም በርካታዎቹ ቪዲዮዎቹን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾች አይተዋቸዋል፡፡ የአንድ ወቅት መነጋገሪያ የነበረው እና የዛሬ ዓመት ገደማ ለዕይታ የበቃው የጌትሽ ማሞ “ተቀበል” የቪዲዮ ክሊፕ ብቻ 11 ሚሊዮን ገደማ ተመልካቾች አይተውታል፡፡ አቶ ብሩክ “የኢትዮጵያ ዩ ቲዩብ ተመልካቾች ቁጥር እየጨመረ ነው” በሚለው ይስማማሉ፡፡ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ቁጥር ጠቅሰው ያስረዳሉ፡፡    

“አንድ ጥሩ ቪዲዮ ከተለቀቀ በአንድ ቀን ውስጥ፣ 24 ሰዓት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከ100 ሺህ እስከ 150 ሺህ ጊዜ የሚታይበት አለ፡፡ ሃምሳ በመቶው በሚሊዮኖች የታዩ ናቸው፡፡ ከዚያ በታች ያሉት አዳዲስ ልጆች ናቸው፡፡ ዕውቅና ለማግኘት እየሰሩ ያሉ ናቸው” ይላሉ አቶ ብሩክ፡፡     

የኢትዮጵያ የኢንተርኔት ፍጥነት በአፍሪካ ካሉት ሀገራት እንኳ ሲነጻጸር ዘገምተኛ እንደሆነ በዘርፉ ዙሪያ የሚወጡ ዓመታዊ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ የሆፕ ሙዚቃ አይነት የቀን ስራቸው ከኢንተርኔት ጋር የተያያዙ ድርጅቶች ችግሩን ለመፍታት በሀገሪቱ ላይ አሉ የተባሉ መፍትሔዎችን ይጠቀማሉ፡፡ እንደ አቶ ብሩክ ገለጻ የእርሳቸው ድርጅት በሀገሪቱ ፈጣን የተባለው የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት በመጠቀም ስራቸውን ያከናውናሉ፡፡ እንደ ናይጄሪያ ካሉ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ልቀው ከሄዱ ሀገራት ጋር ለመወዳደር ግን እነ “ዩ ቲዩብ ጎ” ወደ ኢትዮጵያ እስኪዘልቁ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ 

Audios and videos on the topic