አዲሱ የዩጋንዳ ህግና የምዕራባውያን ተቃውሞ | አፍሪቃ | DW | 28.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አዲሱ የዩጋንዳ ህግና የምዕራባውያን ተቃውሞ

ዩጋንዳ በቅርቡ ያፀደቀችው ግብረ ሰዶማዊነትን የሚቃወም ህግ ዓለም ዓቀፍ ትችት አስከትሏል ። አንዳንድ ምዕራባውያን ሃገራት ለዩጋንዳ የሚሰጡትን እርዳታ እያገዱ ነው ። የጀርመን የልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በበኩሉ የበርሊን መንግሥት ፣ የልማት እርዳታ ቅነሳ ከማድረጉ በፊት ጥንቃቄ የተሞላበት ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቋል ።

በዩጋንዳ ግብረ ሰደሞውያንን ላይ የሚካሄደው ጥቃት ቀጥሏል ። የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ህጉን በፊርማቸው ባፀደቁ በማግስቱ ማክሰኞ Red Pepper የተባለው ጋዜጣ ቀንደኛ ግብረ ሰዶማውያን ያላቸውን የ 200 ሰዎች ስም ዝርዝር ካወጣ በኋላ በዩጋንዳ ግበረ ሰዶማውያን እየታደኑ ነው ። የዩጋንዳ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች እንዳስታወቁት ትናንት ማታ ከባድ ድብደባ ከተፈፀመባቸው ግብረሰዶማውያን ጥንዶች መካከል አንዱ የሞተ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለህክምና ሆስፒታል ተወስዷል ።አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ከ3 ዓመት በፊት የቀድሞው የግብረሰዶማውያን መብት ተከራካሪ ዴቬድ ካቶ ባልታወቁ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወቱ ያለፈበትን ግድያ ያስታውሳል ። ካቶ ከመገደሉ በፊት አንድ ጋዜጣ «ስቀሏቸው »በሚል ርዕሰ ስር ፎቶውን በመጀመሪያ ገጹ ላይ አውጥቶ ነበር ። ከዚያ ቀደም ሲል ካቶ ጋዜጦች የግብረ ሰዶማውያንን ስም እንዳያጠፉ በህግ አስወስኖ ነበር ። ዩጋንዳ ውስጥ ግብረሰዶማውያን አሁን መዋከባቸው አስገራሚ አይደለም ። ባለፈው ሰኞ የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ሰዶማዊነትንና ግብረ ሰዶማዊነትን ማበረታታትን የሚቃወም ህግ በፊርማቸው አፅደቀዋል ። በአዲሱ ህግ በድርጊቱ የተያዙ ሰዎች የእድሜ ልክ እሥራት የሚደርስ ቅጣት ሊበየንባቸው እንደሚችል ተደንግጓል ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች እርምጃው የዩጋንዳ ግብረሰዶማውያንን የከፋ አደጋ ውስጥ ሊጥል እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር ።

Uganda Mord an David Kato

ዴቪድ ካቶ

ህጉ ከዓለም ዙሪያ ትችቶች ቀርበውበታል ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን ዩጋንዳ ሰዎችን በሙሉ ከአመፅና ከአድልዎ እንድትጠብቅ ጥሪ አስተላልፈዋል ። ባን ህጉ ወደፊት ይሻሻላል ወይም ይነሳል የሚል ተስፋቸው እንዳላቸው ተናግረዋል ። ዴንማርክ ኖርዊይና ኔዘርላንድስ ለዩጋንዳ መንግሥት የልማት እርዳታ መስጠት እንደሚያቋርጡ አስታውቀዋል ። ስዊድንና ዩናይትድ ስቴትስም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እያሰቡ ነው ። የጀርመን ፖለቲከኞችም ህጉን አልተቀበሉም ። የጀርመን መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተጠሪ ሶሻል ዲሞክራቱ ክሪሽቶፍ ሽትሬሰር
« በህጉ የተቀመጠው ከፍተኛው ቅጣት ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው ለኛ ግልፅ ነው ። ዩጋንዳ ራሷ ያፀደቀቻቸውን ዓለም ዓቀፋዊ ደንቦችንና ዓለም ዓቀፋዊ ውሎችን የሚጥስ ነው ። »
ሽትራሰር የዩጋንዳ መንግሥት ህጉን እንዲሰርዝም ጠይቀዋል ። በሽትሬሰር እምነት በአሁኑ ጊዜ የልማት እርዳታን ማቋረጥ አስፈላጊ የሆነ ትክክለኛ እርምጃ አይደለም ። ሃገሪቱ በምታራምደው መርህ ተጠያቂ ያልሆኑ ሰዎችን ይጎዳልና ።
« የልማት ተራድኦው ትብብር እንዲቋረጥ ጥያቄ አለ ። እኔ ግን ይሄን በአሁኑ ጊዜ አከራካሪ አድርጌ ነው የማየው ። በዩጋንዳ የሚገኙ ድርጅቶችም ቢሆኑ ይህን ዓይነቱ እርምጃ ይህን ውሳኔ ያስተላለፉትን ፖለቲከኞች እንደማይነካቸው አስጠንቅቀዋል ። »

Uganda President Yoweri Museveni unterzeichnet Anti-Homosexuellen-Gesetz

ሙሴቬኒ ህጉን በፊርማቸው ሲያፀድቁ

እጎአ በ 2013 የቀድሞው የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ዲርክ ኒብል ሰዶማውያንን በሚቃወው የዩጋንዳ የፖለቲካ መርህ ምክንያት ጀርመን ለዩጋንዳ የምትሰጠውን የበጀት ድጋፍ አግደው ነበር ። ያኔ ዩጋንዳ ውስጥ ሲያነጋግር የነበረው ረቂቅ ህግ የሶዶማዊነት ባህርይ በሚያሳዩ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት የሚያስፈርድ ነበር ። የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብርና የልማት ሚኒስቴር ስለ አዲሱ የዩጋንዳ ህግ ለዶቼቬለ በላከው መግለጫ ከመንግሥታት መሪዎች ጋር የልማት ፖሊስ ውይይት ሲያደረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ እንደሚጠይቅ ገልጾ እርዳታን በተመለከተም ገንዘቡ ለሌላ ተግባር እንዲውል ማድረግ እንደሚቻል ሆኖም መቀነሱ ግን በጥሞና መመርመር እንዳለበት አመልክቷል ። ህጉ የሰብዓዊ መብትን የሚጋፋ ነው ሲሉ ከተቃወሙት መካከል የአውሮፓ ህብረትም ይገኝበታል ። ምዕራባውያኑ ህጉን በመቃወም የልማት እርዳታ እንደሚያቋርጡ ቢያስጠነቅቁም ሙሴቬኒ በሰጡት መግለጫ ግን ማሳሰቢያቸውን ከቁብም አልቆጠሩትም ።
« የውጭ ሰዎች ከኛ ጋር መኖር መቻል አለባቸው ። ያን ማድረግ ካልፈለጉ ግን እርዳታቸውን ይዘው መሄድ ይችላሉ ። ዩጋንዳ በጣም ሃብታም ሃገር ናት ። እርዳታ አያስፈልገንም ። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እርዳታ የችግሩ አካል ነው ።»

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic