አዲሱ የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት ም/ፕሬዚደንት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 15.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አዲሱ የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት ም/ፕሬዚደንት

ዶክተር ሶሎሞን በላይ በ1996 ዓ/ም ከሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበረሰብን ፤ቆይተውም የእንጦጦ የስፔስ ሳይንስ ምልከታ እና ምርምር ማዕከልን መስርተዋል።ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ባመጠቀችው ሳተላይትም ጉልህ ድርሻ ያበረከቱ የሀዋ ሳይንስ ተመራማሪ ናቸወ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:47

አዲሱ የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት ም/ፕሬዚደንት

ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት በቅርቡ ኢትዮጵያዊውን የስፔስ ሳይንስ ባለሙያ ዶክተር ሶሎሞን በላይን በምክትል ፕሬዚዳንትነት መርጧል።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም  በአዲሱ ሀላፊነታቸውና በዘርፉ  ባበረከቱት አስተዋፅኦ እና ልምድ ላይ ያተኩራል።  
ዶክተር ሰለሞን በላይ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማኅበረሰብ ፣የእንጦጦ የምልከታና እና የምርምር ማዕከል ፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም፣ አስትሮኖሚ እና አስትሮፊዚክስ ምርምርና ልማት እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ የሥነ ፈለክ ማኅበር መስራች ናቸው።የኢትዮጵያ የአስትሮኖሚ ብሔራዊ ኮሚቴን ጨምሮ  አብዛኛዎቹን ተቋማት በፕሬዝዳንትነት  መርተዋል።የዩንቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪም ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ የቴክኖሎጂ አማካሪ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ ደግሞ ለዓለም አቀፉ አስትሮኖሚያዊ  ህብረት ም/ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጠዋል።ከ100 በላይ ሀገራት እና ከ12000 በላይ ባለሞያዎችን  በአባላትነት  የያዘው  ይህ ተቋም እሳቸውን በም/ፕሬዝዳንትነት የመረጠው  በኢትዮጵያ ብሎም  በአፍሪካ በአስትሮኖሚ እና በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።ዶክተር ሶሎሞን እንደሚሉት አዲሱ ሀላፊነት ለሚቀጥሉት ሶስት አመታት የሚዘልቅ ሲሆን አመራረጡም ለዚህ ተብሎ በተሰየመ ኮሚቴ የተከናወነ ነው።


ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት ሳይንስና ቴክኖሎጅ ምርምሮችን በተመለከተ የመጨራሻ ውሳኔዎችን የሚሰጥ ቁልፍ ተቋም ነው።ተቋሙ አስትሮኖሚ ላይ ተመስርቶ በትምህርት፣በልማት ፣በዘላቂ እድገት፣ ወጣቶችን በማሰልጠን እንዲሁም ማኅበረሰቡን በማንቃት ላይ  ይሰራል።በጎርጎሪያኑ 2012 ዓ/ም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የዚህ ተቋም አባል ስትሆን፤ ዶክተር ሶሎሞንም በዘርፉ ባደረጉት ምርምር በተመሳሳይ ዓመት የዚህ ተቋም አባል ሆነዋል።ከ10 ዓመታት የአባልነት ቆይታ በኋላ ደግሞ ይህንን ትልቅ ተቋም በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ መመረጣቸው እንደ ዶክተር ሶሎሞን በግለሰብም ይሁን በሀገር ደረጃ የሚያስደስት ነው።
ዶክተር ሶሎሞን በላይ ትውልድና እድገታቸው በቀድሞው አጠራር  ጎጃም ክፍለ ሀገር መተከል አውራጃ  በአሁኑ አማራ ክልል በአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ ስጋዲ ገጠር ቀበሌ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ  ትምህርታቸውን ስጋዲ አንደኛ ደረጃ ፤የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ከትውልድ ቀያቸው አቅራቢያ ከምትገኘው ቻግኒ ከተማ  በእግራቸው ተመላልሰው ተምረዋል።


የመምህሮቻቸው እና የእናታቸው የሞራል ድጋፍ በልጅነታቸው ለሂሳብ ትምህርት የተለዬ ፍቅር እንዲኖራቸው  አስተዋፅኦ ማድረጉን የሚገልፁት ዶክተር  ሶሎሞን፤ የአስትሮኖሚ እና የስፔስ ሳይንስ ህልማቸው የተጠነሰሰው  የ11 ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ነው።  
በዚህ ሁኔታ ህልማቸውን ለማሳካት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፊዚክስ በመመረቅ በሁለተኛ ደረጃ መምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፤ ትንሽ ቆይተውም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን  በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በማጠናቀቅ በጅማ  እና  በኮተቤ ዩንቨርሲቲዎች  በፊዚክስ የትምህርት ክፍል በመምህርነት አገልግለዋል።ከዚያም ሶስተኛ ዲግሪያቸውን  አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ  ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ልምድ ያለው አማካሪ ባለማግኘታቸው ወደ ሲዊድን ስቶኮልም በማምራት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተከታትለዋል።ከዚያም በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ የወጠኑትን ስራ በማጠናከር ሀገራቸውን ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

Ausstellung Vatikan Astronomie 2009


ዶክተር ሶሎሞን በ1996 ዓ/ም ከሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን  የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበረሰብን ፤ቆይተውም የእንጦጦ የስፔስ ሳይንስ ምልከታና ምርምር ማዕከልን መስርተዋል። ያም ሆኖ በወቅቱ  የነበረው  ተግዳሮት  ቀላል አልነበረም። በመንግስት በኩል ለዘርፉ ፍላጎት ማጣት፤ በህብረተሰቡ በኩል የመንግስት የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ የማየት፣ የገንዘብ ችግርና በእነርሱ ዘንድም የልምድ እጥረት ፈተናዎች ነበሩ።
ያም ሆኖ እውቀታቸውን፣ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን በነፃ በማበርከት ችግሮቹን ተቋቁመው በዘርፉ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ እሳቸው ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረጉበትና ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ያመጠቀችው ሳተላይት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች መረጃዎችን  በማቅረብ ጥሩ ውጤት እየታዬ መሆኑን አስረድተዋል።በሰው ሀይል ስልጠና ፣ ትምህርቱ በዩንቨርሲቲዎች እንዲስፋፉ እና የህዋ ሳይንስ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲገባ በማድረግ እንዲሁም ኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ፖሊሲ ያላት ሀገር እንድትሆን በማድረግ ረገድም  የተሳካ ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።


በሌላ በኩል ስለ ስፔስ ሳይንስ ሲታሰብ ለታዳጊ ሀገራት ምን ይፈይዳል? የሚል ጥያቄ ተደጋግሞ እንደሚቀርብ የሚገልፁት ዶክተር ሶሎሞን ፤ጥያቄው በሁለት ምክንያቶች እንደሚነሳ ያስረዳሉ።አንድም ታዳጊ ሀገራትን ከውድድር ውጭ ለማድረግ በሌላ በኩል ከግንዛቤ እጥረት።ይሁን እንጅ  ስፔስ ሳይንስ  ለእርሻ፣ለንግድ ስራ ፣ ለመሰረተ ልማት ግንባታ እና ሌሎች መሰረታዊና  ለሀገር ዕድገት የሚጠቅሙ ነገሮችን ለመስራት ወሳኝ ነው ብለዋል።

«አጠቃቀማችንን ለታዳጊ ሃገራት ደረጃዎች አሉት። እርሻ አለ፣« ኮኔክቲቪቲ» አለ፣ መንገዱ አለ ። ከተሞቻችን እየተበላሹ ያሉት እኮ ከተሞችን ፕላን የሚያደርግ  ስፔስ ቴክኖሎጂ ስለሌለን ነው ። ከተማዎቻችን እየተበላሹ ያሉት። ስንት ነገር አለ። እርሻችንን  ለማዘመን፣ የገጠሩን የመሬት አስተዳደር ስርዓት ለማዘመን  ከ«ኮራፕሽንም» ነፃ ያደርጋል ። «ኢ ኮሜርስ» የምንለውም ከሌላ ከየትም የመጣ አይደለም። ስፔስ የሌለበት ነገር የለም። በእርግጥ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ፣ አፍሪካን የመሳሰሉ በዘርፉ ባደጉ ቁጥር  የሌሎች  ሀገራት ገበያ ይቀንሳል ልክ ነው።ግን እስከ መቼ?  የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማምጣት የሚቻለው ሲሰራ ነው። የቴክኖሎጂ ቅኝ-ግዛት በጣም ከባድ ነው። ከፖለቲካ ቅኝ-ግዛት በለጠ አደገኛው የቴክኖሎጂ ቅኝ-ግዛት ነው። በቴክኖሎጂ የበለጠ ጠንካራ ካልሆን ለዘላለም ምንም ነን።»

 


ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

  

Audios and videos on the topic