አዲሱ የቱርክ ፓርቲ ሊቀመንበርና ጠ/ሚኒስትር | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 29.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

አዲሱ የቱርክ ፓርቲ ሊቀመንበርና ጠ/ሚኒስትር

አህምት ዳቩቶግሉ ቱርክን የሚያሥተዳድረዉ የፍትሕ እና የልማት ፓርቲ በቱርክኛ አፅሮቱ የ «AKP» ዋና ሊቀመንበር ሆነዉ ተሾሙ። እስከ ዛሬ የቱርክ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ ያገለገሉት አህሜት ዳቩቱግሉ በተጨማሪ፤ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት በመሆን በአዲስ የተመረጡትን የሬሴፕ ተይፕ ኤርዶኻንን የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ስልጣንንም ተረክበዋል።

ቱርክን የሚያስተዳድረዉ የፍትሕ እና የልማት ፓርቲ በቱርክኛ አፅሮቱ የ «AKP» ፓርቲ ዋና ሊቀመንበር ሆነዉ የተሾሙት፤ አህምት ዳቩቶግሉ፤ ባሳለፍነዉ ረቡዕ ፓርቲዉ ባካሄደዉ ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፤ እንደ ቀድሞዉ የፓርቲ ሊቀመንበር እንደ የሬሴፕ ተይፕ ኤርዶኻን ሁሉ ፓርቲያቸዉ እስከ ዛሬ የተቀዳጃቸዉን ድሎች ሞቅ ባለ ንግግራቸዉ አጉልተዉ አሳይተዋል። አህምት ዳቩቶግሉ፤ በንግግራቸዉ የቱርክን ልማት ለማደናቀፍና ሃገሬቱን ለማዳከም የተቃዉሞ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን አካሎችም አስጠንቅቀዋል። ይህ የዳቩቶግሉ ማስጠንቀቅያ፤ በተለይ ፊቱላህ ጉለን፤ በተባሉት ሃይማኖተኛ መሪነት፤ መንግሥትን ለመገርሰስ በሚደረገዉን እንቅስቃሴ ላይ ያነጣጠረ ነበር።

አዲስ ተመራጩ የ «AKP» ፓርቲ ሊቀመንበርና የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር አህምት ዳቩቶግሉ፤ በጉባኤዉ ላይ እስካሁን ኤርዶኻን ሲያራምዱት የነበረዉን ፖለቲካ መቀጠል ፍላጎታቸዉ እንደሆነም ገልፀዋል ፤

"የተከበሩ ፕሬዚዳንት፤ እርሶ ያስጀመሩትን በቀጣይ ለመምራት እና እስከዘላቂዉ ለመጠበቅ ሃላፊነትን መቀበል ለኛ ትልቅ ክብር ነዉ። እኛ የፓርቲዉ አባላት በሙሉ፤ የርሶ የተዉልን ስራዎች በታማኝነት እንጠብቃለን። ይህን ታሪካዊ ሃላፊነት በቀጣይ መምራት ዓላማችንም ነዉ።"

በአደባባይ የሞቀ ንግግር ሲያደርጉ ታይተወ የማይታወቁት፤ የቀድሞዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት አህምት ዳቩቶግሉ፤ የፓርቲዉን የመሪነት ሥልጣን እንደተረከቡ እንደቀድሞዉ የፓርቲዉ ሊቀመንበር እንደ የሬሴፕ ተይፕ ኤርዶኻንን ሁሉ ፤ መድረክ ላይ ቀስቃሽ ንግግር ነበር ያሰሙት። አዲስ ተመራጩ የቱርክ ፕሬዚዳንት የሬሴፕ ተይፕ ኤርዶኻን በበኩላቸዉ ፤ AKP ፓርቲ ፖለቲካዉን እንደማይቀይር አስረግጠዉ ተናግረዋል፤

"ይህ የመጨረሻ ሳይሆን መጀመርያችን ነዉ። የፓርቲያችን ዓላማም ከዛሬ ጀምሮ አይቀየርም። ሃሳባችን እና ዓላማችንም አይቀየርም። ከዛሬ ጀምሮ የሚቀየረዉ ሥም ብቻ ነዉ።"

ሬሴፕ ተይፕ ኤርዶኻን፤ ሃገራቸዉ የእስልምና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ፤ እንደ ኦስማን ግዛት ጥንካራ የሆነች አዲቷ ቱርክን በመገንባት፤ ለኅብረተሰቡ ብልፅግናን ማምጣት ነዉ የሚፈልጉት። ባለፈዉ ረቡዕ የተካሄደዉ ልዩ ጠቅላላ ጉባኤም ያለምንም ጥርጥር የሚያመክተዉ ኤርዶኻን የዚች የአዲቱ ቱርክ ገንቢ መሃንዲስ እንደነበሩ እና በቀጣይ በምህንድስናቸዉን እንደሚገፉበት ነዉ። አንካራ ቱርክ ዉስጥ በሚታተመዉ ዕለታዊ ጋዜጣ ላይ የሚሰራዉ ጋዜጠኛ ሙራት ያኪንም ይህን ነዉ የታዘበዉ፤ " ከኤርዶኻን ንግግር የምንረዳዉ ፓርቲዉን ለቀዉ መሄዳቸዉን ሳይሆን ፓርቲዉ ዉስጥ መቆየታቸዉን ነዉ።

ኤርዶጋን በንግግራቸዉ፤ ፕሬዚዳንት ሆኜ ሳገለግል ሁሉን ቦታ የሚቃኙ አይኖች አሉኝ ብለዉ ነዉ፤ ፓርቲያቸዉን ፤ ለማረጋጋት የሞከሩት። ዳቩቱግሉ፤ በአዲስ ሥራዉን ለማሟላት የተቀመጡ አይደሉም። ሁሉም ነገር የሚያሳየን የቀድሞዉ መሪ በቀጣይም መሪ ሆነዉ እንደሚቀጥሉ ነዉ፤ የተለወጠዉ የፓርቲዉ መሪ ሥም ብቻ ነዉ።"

እንደ ቱርክ ህገ- መንግሥት፤ የሃገሬቱ ፕሬዚዳንት በማንኛዉም ፓርቲ ዉስጥ አባል መሆን አይችልም። ለዚህም ነዉ የAKP ፓርቲ ከተመሠረተ ከ 13 ዓመት ጀምሮ በሊቀመንበርነት የመሩት የአሁኑ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሴፕ ተይፕ ኤርዶኻን የፓርቲ ሊቀመንበርነቱን ሥልጣን ለማስረከብ የተገደዱት። ኤርዶኻን ትናንት 270814 ሃሙስ፤ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን ተቀብለዉ ቃለ-ማሃላ ፈፅመዋል፤ በቀጣይ አህምት ዳቩቶግሉም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታም ይረከባሉ። ኤርዶኻን እና ዳቩቶግሉ የእስካሁኑን የቱርክ የፖለቲካ ሂደትን ለማስቀጠል እንዲያስችላቸዉ፤ በመንግሥቱ ካቢኔ ዉስጥ ማን ማን የሚኒስቴር ሥልጣንን እንደሚወስድ መስማማታቸዉም ተመልክቶአል።

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic