አዲሱ የማሊ ፕሬዚደንት፣ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ | አፍሪቃ | DW | 13.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አዲሱ የማሊ ፕሬዚደንት፣ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ የማሊ 2ኛ ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ ሆኑ። ምንም እንኳን የምርጫው ውጤት በይፋ ባይወጣም በኬይታ አንፃር ለከፍተኛው የሀገሪቱ ሥልጣን የተወዳደሩት የቀድሞው የገንዘብ ሚንስትር ሱማይላ ሲሴ ትናንት ባልተለመደ ሁኔታ ሽንፈታቸውን በመቀበል

default

ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ


ሱማይላ ሲሴ ትናንት ባልተለመደ ሁኔታ ሽንፈታቸውን በመቀበል ከተፎካካሪያቸው ኬይታ ጋ በመገናኘት የእንኳን ደስ ያልዎት ምኞታቸውን መግለጻቸው ተሰምቶዋል።

ቀደም ሲል የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ከመዲናይቱ ባማኮ እንዳስታወቁት፣ በከፊል በወጣው ውጤት ላይ ኬይታ ሱማይላ ሲሴን በጉልህ የድምፅ ብልጫ በመምራት ላይ ነበሩ። በዚህም መሠረት የማሊ ፕሬዚደንት የመሆን ጽኑ ፍላጎት የነበራቸው የ68 ዓመቱ በአህፅሮት ኢ ቤ ካ በመባል የሚጠሩት ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ፣ ያስቀመጡት ዓላማ ላይ መድረሱ ተሳክቶላቸዋል።
ምርጫውን የሚታዘብ ቡድን ወደ ማሊ የላከው የአውሮጳ ህብረት ተጠሪ ልዊ ሚሸል በምርጫው ሂደት መደሰታቸውን ገልጸዋል።


« የምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሂደት የተሳካ ይመስለኛል። አሁን ሀገሪቱ የጀመረችውን ዴሞክራሲያዊ ሂደት፣ ማለትም፣ ወደ ሥርዓተ ዴሞክራሲ የመመለሱን ተግባር ልትቀጥልበት ትችላላለች። »

ኢ ቤ ካ በተለይ በደቡብ ማሊ ተወዳጅ ናቸው። በዚሁ የሀገሪቱ አካባባ ገና በመጀመሪያው የምርጫ ዙር ነበር አብላጫውን ድምፅ ያገኙት። በተለይ ኢሳ ኮናቴን የመሳሰሉ ወጣቶች ነበሩ ፍትሓዊ ናቸው ላላቸው ለኬይታ ድምፁን የሰጠው።
« አዎ ኢ ቤ ካ ነው የመረጥኩት። ኢ ቤ ካ ሰፊ ተሞክሮ ያላቸው ፖለቲከኛ ናቸው። በርግጥም፣ ማሊን ወደፊት ለማራመድ ይሰራሉ ብየ እተማመንባቸዋለሁ። »
ኬይታ ለሀገራቸው ጠንክረው የሚሰሩ ግለስብ መሆናቸውን እአአ ከ 1994 እስከ 2000 ዓም ጠቅላይ ሚንስትር፣ በኋላም ከ 2002 እስከ 2007 ዓም የምክር ቤት ፕሬዚደንት ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት ማስመስከራቸውን በባማኮ የሚገኘው የራድዮ ጃማና ኃላፊ እና ጋዜጠኛ ሀሚዱ ኮናቴ ገልጸዋል።
« ቀውስን በቁጥጥር ማድረግ የሚችሉ ግለሰብ ናቸው። ቁመናቸው እንኳን ሕዝቡን የሚያረጋጋ ነው፣ ይህ በኛ ባህል ወሳኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በአስተዳደሩ ዘርፍ ስራቸውን በሚገባ የሚያውቁ መሆናቸውም እንዲህ በቀውስ ጊዜ እንደትተማመንባቸው ያደርግሀል። »
በዳካር ሴኔጋል እና በፓሪስ ፈረንሣይ የታሪክ፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት እና ለሀገራቸው የፖለቲካ መድረክ አዲስ ያልሆኑት ኢ ቤ ካ ግን በሀገራቸው የፖለቲካ ተሀድሶ ያነቃቃሉ ተብሎ አይጠበቁም። እንደሚታወሰው፣ ኢ ቤ ካ ሁለቴ ነበር ካሁን ቀደም ፕሬዚደንት ለመሆን የተወዳደሩት።


ኢ ቤ ካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠሩት ጥሩ ግንኙነት ለሀገራቸው ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል በባማኮ የአውሮጳ ህብረት የልዑካን ቡድን መሪ ሪቻርድ ሲንክ ገልጸዋል። እንደሚታወሰው የአውሮጳ ህብረት ባለፈው ግንቦት 2013 ዓም ለማሊ በ2013 እና በ 2014 ዓም የሚሰጥ 520 ሚልዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብቶዋል።
« በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ታዋቂ ናቸው። ከኛ ጋ ሁሌ፣ የፖለቲካ ሥልጣና ባልያዙበትም ጊዜ ግንኙነት ነበራቸው። ጥሩ የግንኙነት መረብ አላቸው። እንግዲህ አሁን ትክክለኛውን ቡድን በማቋቋም ማሊ እንደገና በሁለት እግሯ እንድትቆም ማድረግ፣ ሕገ መንግሥቱን እና የመንግሥቱን መዋቅር ማስተካከል እና አስፈላጊ ውሳኔዎችን ባፋጣኝ በተግባር መተርጎም ይጠበቀባቸዋል።
የማሊን ኤኮኖሚ ማነቃቃት፣ ስራ አጥነትን እና ድህነትን መታገል ኢ ቤ ካን ከሚጠብቃቸው ተግባር መካከል አንዱ ሲሆን፣ ትልቁ ሀገሪቱን ማረጋጋት ይሆናል። ምክንያቱም ለተወሰነ ጊዜ በእሥላማውያን ዓማፅያን ቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ሰሜናዊ ማሊ ሙሉ ለሙሉ አልተረጋጋምና። የሀገሪቱን ፀጥታ ለማስጠበቅ አዲሱ ፕሬዚደንት ከሌሎች ጋ ባንድነት በመሆን የጦር ኃይሉን ማጠናከር እንደሚኖርባቸው ጋዜጠኛው ሀሚዱ ኮናቴ ጠቁመዋል።
« እርግጥ ኢ ቤካ ከጦሩ ጋ ቅርበት አላቸው ግን እኛም ለጦሩ ቅርብ ነን። አዎ የጦር ኃይሉ ስላካሄደው የመፈንቅለ መንግሥት ግልጽ አስተያየት አልሰጡም፤ መፈንቅለ መንግሥቱን እንዳወገዙ ይናገራሉ። ግን፣ መፈንቅለ መንግሥቱን ያካሄዱትን የጦር መኮንኖችን ሄደው መጎብኘታቸውም የሚታወቅ ነው። »
በዚሁ ጉብኝታቸው በመጨረሻዎቹ የሥልጣን ዘመናቸው አንዳችም ለውጥ ባለማስገኘታቸው ሀገሪቱን እውድቀት አፋፍ አድርሰዋል በሚል በማሊ ዜጎች ይወቀሱ ከነበሩት ከሥልጣን ከተወገዱት አማዱ ቱማኒ ቱሬ መራቃቸውን አሳይተዋል፣ ይኸው ርምጃቸውም በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ለድል እንዳበቃቸው ብዙዎች ይገምታሉ።

.

ካትሪን ጌንስለር/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic