አዲሱ የሚሌኒየም ግድብ እና ግብጽ፤ | ኢትዮጵያ | DW | 05.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

አዲሱ የሚሌኒየም ግድብ እና ግብጽ፤

ኢትዮዽያ ይፋ ያደረገችው አዲሱ የሚሌኒየም ግድብ ማንንም የሚጎዳ አይደለም ትላለች። ግብጽ የግድቡ ፕሮጀክት ጥናት እንዲሰጣት ኢትዮድያን ጠይቃለች። ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል በአዲሱ ግድብ ላይ ዘመቻ አልከፈትኩም ሲል አስታውቋል።

default

ከ70 ሚሊዮን እስከ 80 ሚሊዮን ብር በጀት ይጠይቃል- አዲሱ የሚሌኒየም ግድብ። ጉዳዩ ኢትዮዽያንና ግብጽን ፍጥጫ ውስጥ ሊከታቸው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል። አልሚስሪ አል አልዮም የተሰኘ አንድ የግብጽ ጋዜጣ የኢትዮዽያን እቅድ «በእሳት የመጫወት ያህል ነው» በማለት ዘግቦታል። ኢትዮዽያ መብቴ ነው፤ ግብጽን ሊጎዳ የሚችል አይደለም ትላለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የግብጽን ህዝብ የመጉዳት እቅድ ኢትዮዽያ የላትም ይላሉ።

ኢትዮዽያ አዲሱን የሚሌኒየም ግድብ በተመለከተ ግብጽና ሱዳን የሚጎዱበት ሁኔታ የለም ብትልም ግብጻውያን ግን ስጋቱ እንዳላቸው ይገልጻሉ። የቀድሞ የግብጽ የውሃ ሀብት ሚኒስትር፤ አሁን የአረብ ሀገራት የውሃ ጉባኤ ዳይሬክተር የሆኑት መሀሙድ አቡ ዘይድ እንደሚሉት፤ በእርግጥ ስጋት አለ።

«ታዛቢ ሰዎች፤ ይህ ግድብ የግብጽን ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ነው ብለው ፍርሃታቸውን ይገልጻሉ። በእርግጥ ኢትዮዽያ አንድ ግድብ አይደለም በአባይ ላይ እያቀደች ያለችው። አራት ግድቦችን ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እነዚህ ግድቦች ወደ ግብጽና ሱዳን የሚገባውን የውሃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ የሚያደርጉ ናቸው»

የኢትዮዽያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ኢትዮዽያ በአባይ ላይ የምታከናውናቸው ፕሮጀክቶች በጥናት የተካሄዱ፤ የጋራ ተጠቃሚነትንም የሚያጠናክሩ ናቸው ይላሉ።

የሆነ ሆኖ ሁለቱ ሀገራትን ፍጥጫ ውስጥ ይከታል የተባለው አዲሱ የሚሌኒየም ግድብ በግብጽ በኩል የፕሮጀክቱን ዝርዝር ጉዳይ የተመለከተ መረጃ ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ ቀርቧል። የቀድሞ የግብጽ የውሃ ሀብት ሚኒስትር መሀሙድ አቡ ዘይድ መረጃውን ከኢትዮዽያ እየጠበቅን ነው ይላሉ።

ከዚሁ ከሚሌኒየም ግድብ ጋር በተያያዘ ከአከባቢና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሊነሳ የሚችለው ተቃውሞ ይጠበቃል። የጊቤ ግድብን በመቃወም 400 ያህል ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፊርማ እያሰባሰቡ ሲሆን ይህንንም ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል የተሰኘ ለጎሳ ህዝቦች የሚሟገተው ድርጅት በፊት አውራሪነት እየመራው ይገኛል። ሊንሲ ዳስሎግ በድርጅቱ የጊቤ ዘመቻ አባል ናቸው።

«ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል በአዲሱ የሚሌኒየም ግድብ ላይ የከፈተው ዘመቻ የለም። የግድቡ ሥራ ድርጅቱ ከሚሟገትላቸው ህዝቦች ጉዳይ ጋር የሚገናኝ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ በጊቤ ግድብ ምክንያት መብቱ አደጋ ላይ ስለወደቀው የኦሞ አከባቢ ህዝብ ነው ድርጅታችን ተቃውሞ የሚያሰማው። ይህ ዘመቻ ኢትዮዽያ ይፋ ካደረገችው የሚሌኒየም ግድብ ፕሮጀክት የተለየ ነው።» መሳይ መኮንን ሂሩት መለሰ