1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የህወሓት ጥቃት በአፋር

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2014

የአፋር ክልላዊ መንግስት ረዳት ተጠሪ ከባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከትግራይ ክልል መዲና መቀለ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የአፋር ክልል ዓብዓላ ከተማ ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት መፈፀሙን ተናገሩ። በጥቃቱ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተነግሮአል። ዜናዉን ትግራይ በኩል ለማጣራት ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።

https://p.dw.com/p/44sab
Äthiopien Konflikte
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

«ዓብዓላ ከተማ ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ፈጽሟል» የአፋር ባለሥልጣን

ባለፈው ሳምንት ከአፋር እና ከምስራቅ አማራ ክልሎች ሙሉ በሙሉ መውጣታቸው የተነገረው የህወኃት ታጣቂዎች በአፋር ሰሜናዊ ዞን አብዓላ በኩል አዲስ ጥቃት መጀመሩን ባለስልጣናት ገለፁ፡፡ የአፋር ክልላዊ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ መሃመድ አህመድ ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት ህወሓት ከባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከትግራይ ክልል መዲና መቀለ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የአፋር ክልል ዓብዓላ ከተማ ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ ንጹሃንን ዓላማ ያደረገ ነው ባሉት በጥቃቱ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንም አመልክተዋል፡፡

የአፋር ክልል መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ መሃመድ አህመድ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት በህወሓት በኩል በተተኩሰው የከባድ ማሳሪያ ጥቃት የእምነት ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የማህበራዊ መገልገያ እና የነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች እላማ ውስጥ ገብተው የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡ በዚህም ለጊዜው ቁጥራቸው ያልተለየው የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የሞትና መፈናቀል አደጋ ተከስቷል፡፡  

ይህቺ ከተማ በትኩረት ውስጥ የገባችበትን ወታደራዊ ጠቀሜታ እና የጥቃቱ ዓለማ ምን ይሆን በሚል የተጠየቁት ኃላፊው በጭፍራ እና አሳግታ በኩል ወደ ሚሌ እንዳይጓዝ ጠላት ያሉት የህወሓት ኃይል መከልከሉን ተከትሎ የወሰደው የበቀል እርምጃ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው ግምታቸውን የገለጹት፡፡  

ጥቃቱ የእምነት ተቋማትን ጨምሮ የነዋሪዎችን ቤትም ያልለየ ነው የሚሉት አቶ መሃመድ፤ ለሰላም ጀርባውን የሰጠ ያሉት ህወሓት ለሰላም ዝግጁ ይሆናል ብለው እንደማይጠብቁትም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሓሙስ በአፋር እና ምስራቅ አማራ የሚገኙ የሰራዊት አባላት ባሉበት ፀንተው እንዲቆዩ ያስተላለፈው የውሳኔ ኃሳብ ዓመትን ለተሻገረው ጦርነት ምናልባትም የሰላም እልባት ያመጣ ይሆናል በሚል በበርካቶች መሞካሸቱ ይታወሳል፡፡

 

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ