አዲሱ ዓመትና የሶርያ ቀዉስ | ዓለም | DW | 01.01.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

አዲሱ ዓመትና የሶርያ ቀዉስ

ሶርያዉንያ የጎርጎሮሳዊዉን አዲስ ዓመት በሰላም አልተቀበሉትም፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በአዉሮፕላን ድብደባ ሲካሄድ የመንግስት ኃይሎችና አማፅያንም ዉጊያዉን አጠናክረዉ ቀጥለዋል። በዋዜማዉ ትናንት ደግሞ የሶርያ ሰብዓዊ መብት ተመልካች ደማስቆ ዉስጥ ቁም ስቅል የተፈመባቸዉ እና ህይወታቸዉ ያለፈ ሰዎችን በአንድ ስፍራ ማግኘቱን አመልክቷል።

«የሶርያን ችግር ለመፍታት እና የሶርያን ህዝብ ለማስደሰት እና ለሶርያ ህዝብ ህጋዊ መብቱን ለመስጠት የፖለቲካ መፍትሄ አስፈላጊ ነዉ፤ ይህ ካልሆነ ግን ሶርያ ወደሲኦልነት ትለወጣለች።»

የሶርያ የተመድ እና የአረብ ሊግ የሰላም ልዑክ ላክዳር ብራሂሚ ዓመቱ ከመጠናቀቁ ከሶስት ቀናት በፊት ካይሮ ላይ የሶርያን ጉዳይ አስመልክተዉ የሰጡት መግለጫ ነዉ።

ሶርያ በመንግስት እና በተቃዋሚዎች ፍጥጫና ጦርነት ከገባችበት ቀዉስ ሳትላቀቅ እንደሌላዉ ዓለም ሁሉ የጎርጎሮሳዊዉን 2013ዓ,ም ዛሬ አንድ ብላለች። በአዲሱ ዓመት መባቻም የተሰማዉ ከመሰንበቻዉ የሚለይ አይደለም። አማፅያን ፕሬዝደንት ባሺር አልአሰድን ከስልጣን ገልብጠዉ በአዲሱ ዓመት የደማስቆ ቤተመንግስትን ለመቆጣጠር እንዳለሙ፤ ፕሬዝደንቱም ከነደጋፊዎቻቸዉ የያዙትን ላለመልቀቅ የምድርም የአየርም ጥቃትና ድብደባቸዉን አጠናክረዉ ታይተዋል። አሌፖ በተሰኘችዉ ከተማ የአማፅያን የተጠናከረ ጥቃት የአዉሮፕላን ማረፊያዉ ለጊዜዉ እንዲዘጋ አስገድዷል። አዉሮፕላን ማረፊያዉ የተዘጋዉ የመንግስት የጦር ጀቶች በከተማዉ አቅራቢያ የሚገኙ አካባቢዎችን በሚደበድቡበት ወቅት መሆኑንም የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል። መንግስት ምክንያቱን ሲገልፅ፤ አማፅያን በተደጋጋሚ የመንገደኞች አዉሮፕላንን መትተዉ ለመጣል በመሞከራቸዉ ነዉ ብሏል። ይህንንም የሶርያ የሰብዓዊ መብቶች ተመልካች በዘገባዉ አረጋግጧል።

UN-Gesandter Brahimi in Kairo

ላህዳር ብራሂሚ ካይሮ

ባለፈዉ ቅዳሜ ዕለት ከአማጽያን የተተኮሰ መሆኑ የተገመተ አዳፍኔ አንድ የመንገደኞች አዉሮፕላንን መምታቱን የጠቆመዉ የቡድኑ ዘገባ ግን ስለደረሱዉ ጉዳት የሰጠዉ ዝርዝር መረጃ የለም። የሚዘጋዉም ጦሩ አካባቢዉን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር ማድረጉ እስኪረጋገጥ መሆኑንም አንድ የመንግስት ባለስልጣን ገልጸዋል። ግጭት ጦርነት ብሎም አመፅ ባናወጣት ሶርያ ትናንትናም በሚግ ጀቶች ከደማስቆ በስተሰሜን ምስራቅ የሚገኙ ትናንሽ መንደሮችን፤ እንዲሁም ዳራያ እና ሞዳሚየት አልሻም የተባሉ ከተሞችን መደብደባቸዉ ተገልጿል። የመንግስት እግረኛ ጦርም፤ የሶርያ ነፃ አዉጭ ከተባለዉ አማፂ ቡድን ጋ ሲዋጉ መዋላቸዉ ተገልጿል። አማፅያን ድጋፍ ካሳዩዋቸዉ የዉጭ መንግስታት የጠበቁትን የጦር መሳሪያ ባለማግኘታቸዉ ቅሬታ እያሰሙ ነዉ። ያም ሆኖ እዚያዉ ባገኟቸዉ ስብርባሪ ብረታብረቶችና ንጥረነገሮች በመጠቀም ከኢንተርኔት ያገኙትን መረጃ ተጠቅመዉ ባዘጋጇቸዉ ጓዳ ሰራሽ መሳሪያዎች የፕሬዝደንት በሽር አልአሰድን መንግስት ለመጣል ፍልሚያ መቀጠላቸዉን ሮይተርስ አመልክቷል።

ትናንት የሶርያ መብት ተመልካች ቡድን በቪዲዮ አስደግፎ ይፋ ያደረገዉ ዘገባ በሀገሪቱ ዉስጥ እየተፈጸመ የሚገኘዉን የጭካኔ ድርጊት አጉልቶ እንደሚያሳይ አመልክቷል። ደማስቆ ባርዛህ በተባለዉ ክፍለ ከተማ የተገኘዉ 50 የሚሆኑ ሰዎች አስከሬን አንገትና ሌሎች አካሎች በመቆረጡ ማንነታቸዉን መለየት እንዳልተቻለም ተገልጿል። ደማስቆ ዉስጥ የተገኘዉ ቁም ስቅል ተፈጽሞባቸዉ ህይወታቸዉ ያለፈ የበርካቶች አስከሬን ይፋ መሆንም የሶርያ ቀዉስ እልባት እንዲያገኝ በተመድ በአረብ ሊግ የሰላም ልዑክ ላክዳር ብራሂሚ የተጀመረዉ ጥረት እንዳያሰናክል ስጋት አስከትሏል። ሶርያ የምትገኝበት ሁኔታ ያሳሰባቸዉ ብራሂሚ በቅርበት የሚከታተሉትን እንዲህ ነዉ የገለፁት፤

«ሶርያ ዉስጥ ሁኔታዉ በጣም መጥፎ፤ በጣም በጣም መጥፎ ነዉ። ልዩነቱም እንዲሁ እጅግ ከፍ ብሏል።»

ፕሬዝደንት አልአሰድም የብራሂሚን የሰላም እቅድ በመቀበል በሀገሪቱ የሚታየዉን የደም መፋሰስ ለማብቃት ለዉይይት ዝግጁ መሆናቸዉን መግለፃቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። ዘገባዎች እንደሚሉት 21 ወራትን ባስቆጠረዉ የሶርያ ግጭት ጦርነቱ 45 ሺህዎችን ፈጅቷል። ከዚህ መካከል ዘጠና በመቶ የሚሆነዉ ባለፉት 12 ወራት ዉስጥ የተፈፀመ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic