አዲሱ ካቢኔ የምሁራንና የባለሞያዎች መንግሥት ነዉን? | ኢትዮጵያ | DW | 02.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

አዲሱ ካቢኔ የምሁራንና የባለሞያዎች መንግሥት ነዉን?

የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ ካቢኔ ማወቀሩን ተከትሎ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው እየጎረፉ ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አዲስ የሚያዋቅሩት ካቢኔ የፓርቲ አባላት ያልሆኑ የምሁራን እና የባለሙያዎች (ቴክኖክራቶች) ስብስብ እንደሚይዝ ጥቆማ ሰጥተው ነበር፡፡ የሚኒስትሮቹን ሹመት ከቃላቸው አንጻር የሚመዝኑ ጥያቄዎችን ማንሳት ጀምረዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:34
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:34 ደቂቃ

ኃይለማርያም ቴክኖክራቶችን ሾመዋልን?

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የካቢኔ መዋቅር ካሉ 30 ሚኒስትሮች መካከል ሲሶው ያህል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምርምር ማዕከላት የመጡ ናቸው፡፡ በህዝብ ዘንድ እምብዛም ከማይታወቁት ከእነዚህ ተሿሚዎች ውስጥ የተወሰኑት ከሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር የተያያዘ የትምህርት እና የስራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከዚህ ቀደም በተቋሞቻቸው ያካበቱት የስራ ልምድ እንደ መመዘኛ መስፈርት ተወስዶላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ሲናገሩ “እውቀት እና ክህሎት” ያላቸውን እነዚህን ተሿሚዎች ለማግኘት ብዙ አፈላልገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈልጌ አገኘኋቸው ያሏቸው ሚኒስትሮችም ቢሆኑ ግን ከትችት አላመለጡም፡፡ ከተቃዋሚዎች እስከ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ተሳታፊዎች የሚኒስትሮቹን “አዲስነት እና ብቃት” ጥያቄ ውስጥ ከትተዋል፡፡

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ከሚኒስትሮቹ ውስጥ ሁለቱን በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡ ምሁራን ናቸው ቢባሉም በተቋሞቻቸው ውስጥ እያሉ ይፈጽሙት የነበረው ተማሪዎችን ለጉዳት የሚያጋልጥ ነበር ሲሉ ይከሳሉ፡፡

“እነዚህ ምሁራን የሚባሉት ለኢህአዴግ ሲሰሩ የነበረ ሲያገልግሉ የነበሩ ናቸው፡፡ የምሰማቸው ስሞች አዲስ አይደሉም፡፡ ኢህአዴግን በማገልገል የታወቁ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ የምናውቃቸው ወለጋ ዩኒቨርስቲ፣ ሃሮማያ ዩኒቨርስቲ የነበሩ ሰዎች የኦሮሞ ወጣቶች ያሳስሩን ነበር ሲሉ ሲከሷቸው የነበሩ ናቸው” ይላሉ ዶ/ር መረራ፡፡

   ሌሎች ተቺዎች ደግሞ በዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔቶች ላይ ጽሁፎችን ማሳተም እንዴት የሚኒስትር መምረጫ መስፈርት ውስጥ እንደገባ ይጠይቃሉ፡፡ ካቢኔው “የዩኒቨርስቲ ሴኔት መሰለ” ያሉም አሉ፡፡እንዳንዶች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሌሎች መስሪያ ቤቶች ውስጥ ኃላፊ ሆኖ መስራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ከመምራት የተለየ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡

በትናትናው የካቢኔ ምስረታ ሹመት ያገኙት አዲሱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ግን ሚኒስትሮቹ “አቅም አላቸው” የሚል ምልከታ አላቸው፡፡ “የተሻለ የሚናገረው ውጤት” እንደሆነ እና ጊዜውን ጠብቆ ያንን መመልከት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

“እኔ በአዎንታዊ ጎኑ ነው የማየው፡፡ ደግሞ ውጤት ነው የተሻለ የሚናገረው፡፡ ብዙ ጊዜ እንግዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ የተሻለ ተናጋሪዎች እና ብዙ የሚናገሩ ሰዎች የተሻለ ፖለቲከኞች የሆኑ አድርጎ መገመት አለ፡፡ አሁን ግን ይህ መሰረታዊ ለውጥ ይመስለኛል፡፡ የተሻለ ስራ የሚሰሩ፣ ሰርተው የሚያሰሩ፣ በስራ የሚያምኑ፣ በሀገር በዜጋ ተጠቃሚነት የሚያምኑ ሰዎች ስራ ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ የሚበዙት ጥያቄዎች እንደዚህ ይቀጥላሉ ብዬ አላምንም፡፡ ዜጎችን አሳትፈው ሀገሪቷን ወደ ተሻለ መምራት ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡   

 “አዲሱ ካቢኔ በእርግጥ የቴክኖክራቶች ስብስብ ነው?” የሚለው ጥያቄ ማከራከሩን ቀጥሏል፡፡ የተሿሚዎችን የትምህርት እና የስራ ልምድ ቃኝተው በምሁርነታቸው እና ባለሙያነታቸው የተስማሙ እንዳሉ ሁሉ “የእነርሱ በካቢኔው መካተት ብቻ የጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያምን አስተዳደር የቴክ ኖክራት መንግስት አያስብለውም” የሚሉ አሉ፡፡

ለመሆኑ የቴክኖክራት መንግሰት ማለት ምን ማለት ነው? በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር ለሆኑት ጆሽዋ ተከር የቴክኖክራት መንግስት ማለት የሙሉ ጊዜ ፖለቲከኞች ያልሆኑ ሚኒስትሮችን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡እነዚህ ሚኒስትሮች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይጠበቅባቸው ነገር ግን በተሰማሩበት ዘርፍ ባለሙያ መሆን ግድ እንደሚላቸው ይተነትናሉ፡፡

“በብያኔው መሰረት  የቴክኖክራት መንግስት ማለት የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ ምክትላቸው እና በመንግስት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ሰዎች መንግስት ከመሰረተው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ከአጋሮቹ ሳይሆኑ ሲቀር ነው፡፡ ቴክኖክራት መንግስት የምንልበት ምክንያት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለመምራት የሚያስፈልግ ክህሎት ያላቸው ነገር ግን ራሳቸው ፖለቲከኛ ያልሆኑትን ስለሚያካትት ነው፡፡ የቴክኖክራት መንግስት የሚለውን ቃል ከፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ተወካዮች ጋር ንኪኪ የሌለላቸውን ሰዎች ለመግለጽ ነው፡፡ ሰዎቹ ባለሙያ መሆን ይኖርባቸዋል” ብለዋል ፕሮፌሰሩ፡፡    

ዶ/ር ነገሪ የአዲሱ ካቢኔ አባላት ቴክኖክራቶች መሆናቸውን በልበ ሙሉነት ይመሰክራሉ፡፡   

“እነዚህ ምሁራን በእውነትም ቴክኖክራት ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንዳንዶቹን [ብናይ] እንደ ተባበሩት መንግስታት ባሉ ዓለም አቀፍ ትልልቅ ተቋማት አልፈው በአህጉር ደረጃም ከዚያም በሀገር ውስጥም ትልልቅ ድርጅቶችን የመሩ ነገር ግን በፖለቲካ ቅርበት የማያምኑ እና የሀገር ፍቅር ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ኃላፊነቱ ከተሰጣቸው በኋላ ዝም ብለው የተሰጣቸውን የሚቀበሉ ይሆናሉ ብዬ አላምንም”  ሲሉ እምነታቸውን  ይገልጻሉ   

የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም በብዙዎች ዘንድ ግን ሹመቱ ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎችን እንደደቀነ ነው፡፡

 

ተስፋለም ወልደስ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic