አደጋ፤ ሐዘንና ቁጣ በቱርክ | ዓለም | DW | 15.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

አደጋ፤ ሐዘንና ቁጣ በቱርክ

ቱርክ ውስጥ ከኢስታንቡል በስተደቡብ ምዕራብ ፣ ሶማ በተባለችው ቦታ በሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማውጫ ጉድጓድ ከትናንት በስቲያ በደረሰ የፍንዳታ አደጋ ሳቢያ ፤ 282 የማዕድን ሠራተኞች መሞታቸው በዛሬው ዕለት ተረጋግጧል።

አሁንም በትኅተ-ምድር ያስጨነቀው፣ መፈናፈኛ ያጡ ሠራተኞች ይዞታ ፤ የአገሪቱ ህዝብ ዐቢይ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል። ሁኔታው ያናደዳቸው ያገሪቱ 4 ታላላቅ የሠራተኞች ማሕበራት ዛሬ የአንድ ቀን የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል። የማዕድን ሠራተኞቹ አሟሟት ያስቆጣቸው ቁጥራቸው ከ 3,000 እስከ 4,000 የሚገመት ዜጎች አንካራ ውስጥ ትናንት ቅጽበታዊ የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄድ ፤ ከፖሊስ ጋር ተጋፍጠው እንደነበረ ታውቋል።በግዙፏ ከተማ በኢስታንቡልም በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው ነበር።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሪቸፕ ጣይብ ኤርዶጋን፤ አደጋ የደረሰበትን ቦታ እዚያው ድረስ ሄደው ቢመለከቱም፤ እጅግ አሳዛኙን ዕልቂት አስመልክተው በእኛ ሀገር ብቻ አልተጀመረም ፤ ይህን መሰል አደጋ በሌሎችም አገሮች ያጋጥማል ማለታቸው አልተወደደላቸውም።

« እንዲህ ዓይነቱ በማዕድን ማውጫ ቦታ የሚያጋጥም አደጋ በቱርክ ብቻ የሚደርስ አይደለም። በብዙ አገሮች፤ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ቻይና ፤ ፈረንሳይ፤ ሕንድና ቤልጅግም አጋጥሞ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በድንጋይ ከሰል ማውጫ ጉድጓዶች ብዙ ሰዎች የሞቱበትን ዝርዝር አኀዝ ማቅረብ እችላለሁ። ሃገራችን በተሻለ ሁኔታ ላይ ነው የምትገኘው።»

በቱርክ ፤ ከ 280 በላይ የማዕድን ሠራተኞች ሕይወት መቀጠፉን መንስዔ በማድረግ፤ ሕዝቡ ሐዘኑንና ቁጣውን በመግለጽ ላይ ሲሆን፤ ጠ/ሚንስትሩ፣ አደጋውን አቅልለው በማየት፣ በ 19ኛው ክፍለ ዘመን በሌላ ሀገር እዚህም ላይ በእንግሊዝ ሀገር፣ እ ጎ አ በ 1862 ዓ ም 204 የማዕድን ሠራተኞች በ 1864 ደግሞ 361 መሞታቸውን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ አያሌ ዓመታት ተመልሰው በሌላ ሀገር የደረሰ አደጋ ከመጥቀስ፤ በራሳቸው ሀገር የቅርብ ታሪክ ያጋጠመውን ማውሳት በቻሉ ነበር ። እ ጎ አ በ 1992 በቱርክ ፤ ዞንጉልዳክ በተባለ ቦታ በሚገኝ ማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ውስጥ በጋዝ ሳቢያ በደረሰ ፍንዳታ፤ 263 የማዕድን ሠራተኞች ሕይወታቸውን ማጣታቸው የሚታወስ ነው። የአሁኑ አደጋ የደረሰበት ክፍለ ሀገር የማኒሳ የህዝብ እንደራሴ፤ ኦዝጉር ኦዜል፤ በየጊዜው ሶማ ላይ ከሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማውጫ ጉድጓድ ሠራተኞች፤ በትኅተ- ምድር የሚከናወነው ተግባር ለደኅነነት እከዚህም አስተማማኝ አይደለም በማለት ሥጋታቸውን ይገልጹላቸው እንደነበረ ጠቁመዋል።

በኢስታንቡል ፣ የቢልጊ ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር ፣ ኢልተር ቱራን ፣

«በማዕድን ማውጫው ጉድጓድ የደኅንነት ጥያቄ ችላ ተብሎ ስለመቆየቱ አስተማማኝ መረጃ ከቀረበ፤ የፖለቲካ ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል። የኤርዶጋን አስተዳደር በሙስና ተዘፍቋልና ምርመራ ይካሄድበት ለሚሉትም በቂ ምልክት የሚሰጥ ነው » ማለታቸው ተጠቅሷል።

ጠ/ሚንስትር ኤርዶጋን በበኩላቸው የተለየ መረጃ እንዳላቸው ነበረ የተናገሩት።

«በመጋቢት ወር ማለቂያ ( እ ጎ አ በ 2010 ዓ ም) ይህ ማዕድን ማውጫ ቦታ፤ ለሠራተኞች ጤንነት ጠንቅ እንደሌለበት፤ ለደኅንነታቸው አስተማማኝ መሆኑ በምርመራ ተራጋግጦ ነበር።»

ከ 280 በላይ የሚሆኑ የማዕድን ሠራተኞች ሕይወት በመቀጠፉ፣ የቱርክ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር አዝኗል። በሀገሪቱ በመላ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል። አንካራ ውስጥ ከፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጋር ግጭት ተፈጥሯል። ብዙዎች በአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናደዋል። በኢስታንቡል አጥሮች ፣ «ነፍስ ገዳዮች » የሚል ብርቱ ዘለፋም ሠፍሯል። የሃገሪቱ ሠራተኞች ማሕበራት እንዲያውም የሕዝብ ጭፍጨፋ ተካሂዷል ነው ያሉት። ኩባንያዎቹ የሚያስቡት ትርፍ ስለመዛቃቸው እንጂ፤ ለማዕድን ሠራተኞች ደኅንነት ደንታም የላቸው። መንግሥት ደግሞ ይህን አቋማቸውን ይደግፍላቸዋል። ሰው ኖረ ሞተ፤ ጉዳያቸው አይደለም፤ ስንጥቅ ትርፍ ማግኘታቸውን ብቻ ነው የሚያሰላስሉት። ከተቃውሞ ሠልፈኞች መካከል አንዱ እንዲህ ነው ያለው።

«የማዕድን ማውጫው ጣቢያ በግል ይዞታ እንዲውል ወሰኑ። የሚነገረው ታሪክ የተሳኩ ድርጊቶችን የሚያወሳ ሆነ።ይኽኛው የማዕድን ኩባንያም፤ ስለኩባንያው ስኬታማነት ነው የሚያወራው። ከዚያስ ምንድን ነው የሆነው? ከፍንዳታው ጋር ተያይዞ፤ የቅድሚያ ጥንቃቄ አለመደረጉን ለማስተዋል ችለናል። የሠራተኞቹ ኅልውና ዋጋ አልተሰጠውም። ለላቀ ትርፍ ሲባል ሕይወታቸው ለአደጋ እንዲጋለጥ ነው የተደረገው።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic