አደንዛዡ ዕፅና ምዕ/አፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 10.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አደንዛዡ ዕፅና ምዕ/አፍሪቃ

የተመድ የአደንዛዡ ዕፅ ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት ባወጣው ዘገባ መሠረት፡ አደንዛዡ ዕፅ የኮኬይን ንግድ ከደቡብ አሜሪካ በህገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮጳ በሚገባበት ጉዞ ላይ ምዕራብ አፍሪቃ መሸጋገሪያ በመሆን ዋነኛ ሚና ይጫወታል።

default

በኬፕ ቬርዴ የተወረሰ ኮኬይን

እርግጥ፡ አደንዣዡ ዕፅ በምዕራብ አፍሪቃ በኩል የሚያልፍበት ድርጊት ለደቡብ አሜሪካውያኑ ህገ ወጥ አደንዛዥ ዕፅ ንግድ አራማጅ ድርጅቶች ብዙ ወጪ ይቀንስላቸዋል። በአካባቢው ሕዝብ ላይ ግን አሳሳቢ መዘዝ አስከትሎዋል።

በአሁኑ ጊዜ አንድ በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ቢኖር ሴኔጋል፡ ላይቤርያ፡ ጊኒ ቢሳው፡ ባጠቃላይ ማዕከላይ እና ምዕራብ አፍሪቃ ለህገ ወጡ የአደንዛዡ ዕፅ ኮኬይን ንግድ ዋነኛ መናኸሪያ እየሆኑ መጥተዋል። የተመድ የዕፀ ሱስ ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው፡ በያመቱ በምዕራብ አፍሪቃ በኩል ወደ አውሮጳ ከሚያልፈው የኮኬይን ንግድ የሚገኘው ገቢ ስድስት መቶ ሰማንያ ሚለን ዩሮ መሆኑ ተመልክቶዋል። ምንም እንኳን የየመንግሥታቱ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች በ 2009 ዓም የወረሱት የኮኬይን መጠን በ 2006 ዓም ከነበረው ቢቀንስም፡ ይህ ህገ ወጡ ንግድ ቀንሶዋል ማለት አለመሆኑን የተመድ የዕፀ ሱስ ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት የማዕከላይና የምዕራብ አፍሪቃ ተጠሪ አይሰር አል ሀፊድ ገልጸዋል።
« በ 2009 ዓም በምዕራብ አፍሪቃ በኩል ወደ አውሮጳ ሲያልፍ የተወረሰው የኮኬይን መጠን ሀያ አንድ ቶን እንደነበር መዝግበናል። ከሁለት ዓመት በፊት በ 2007 ዓም አርባ ሰባት ቶን ኮኬይን ለመውረስ ተችሎ ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የወንጀለኞቹ መረብ የአስራር ሥልታቸውን በመቀየራቸው ነው። እና ችግሩ የሚመለከታቸው የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት ከተቀየረው ሁኔታ ጋ የሚስማማ ዘዴ ማውጣት ይኖርባቸዋል። »

** TO GO WITH COCAINA AFRICA ** People gather around a speedboat of a type believed to be used by drug traffickers, as it unloads cargo at a quay in Bissau, Guinea-Bissau, July 17, 2007. Geography is only part of the West African nation's appeal for traffickers trying to get cocaine to Europe. They also need a population that is largely unaware of their business and a weak, easily corruptible government. (ddp images/AP Photo/Rebecca Blackwell)

በጊኒ ቢሳው ለኮኬይን ማጓጋዣ ያገለግላሉ የሚባሉ ፈጣኖቹ ጀልባ


የወንጀለኞቹ ህገ ወጥ መረቦች ለምሳሌ አደንዛዡን ዕፅ ኮኬይን ለማጓጓዝ የሚጠቀሙበት ዘዴ እጅግ ዘመናይና የተራቀቀ ነው። ዕአደንዛዡ ዕፅ ኮኬይን በአይሮፕላን፡ በመርከብ ወይም ባህር ሠርጓጅ መርከቦች ራቅ ብለው በሚገኙት ኬፕ ቬርዴን በመሳሰሉት ደሴቶች ይራገፋል። ከዚያ ጥቂት በጥቂት ወደሚፈልጉት ሀገር ይላካል። በሲየራ ልዮን እና በላይቤሪያ፡ እንዲሁም፡ ሴኔጋልን በመሳሰሉት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገሮች የሚታየው ያልተረጋጋው የፀጥታ ሁኔታ እና ያልተጠናከረው የድንበር ቁጥጥር ህገ ወጡ የኮኬይን ንግድ በቀላሉ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኖዋል።
ህገ ወጡን ንግድ ተቆጣጥሮ ለማከላከሉ ተግባር በ ጊኒ ቢሳው የባህር ኃይል፡ የግምሩክ እና የጦር ኃይል ላይ ጥገኛ ለመሆን ባለመቻሉ ይህቺው ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ባለፉት ዓመታት ኮኬይን ወደ አውሮጳ የሚተላለፍባት ዋነኛ መናኸሪያ ሆናለች። ምክንያቱም እነዚሁ ወገኖች ራሳቸውን ከህገ ወጡ የኮኬይን ንግድ ተጠቃሚ እንዳደረጉ በጊኒ ቢሳው በአደንዛዡ ዕፅ ኮኬይን አንጻር የሚታገለው የስዊድናውያኑ ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ፕሪስካ ሀውዘር ሼረር አመልክተዋል።
« የዕፀ ሱሱ ንግድ አደገኛ በመሆኑ ሁኔታውን በጣም አሳሳቢ አድርጎታል። የራስን ሕይወት አደጋ ላይ ሳይጥሉ አንድን የአደንዛዡ ዕፅ ኮኬይን ነጋዴን ለማስቆም አይቻልም። ሕገ ወጡን ንግድ ለማስቆም የሚደረገው ትግል ውጤታማ እንዲሆን በማድረጉ ጥረት ላይ በአንድም የመንግሥት አካል መተማመን ያልተቻለበት እውነታ ለአንድ ሀገር ትልቅ ሸክም ነው። »
በሴኔጋልም ሁኔታው ከጊኒ ቢሳው ብዙም አይለይም። በደቡባዊው ሴኔጋል በሚገኘው የካዛሞንስ ክፍለ ሀገር እአአ ከ 1980 ዓም ወዲህ በመንግሥቱ ጦር ኃይላት እና ለክፍለ ሀገሩ ነፃነት በሚታገሉ ቡድኖች መካካል የቀጠለው ውጊያ ያካባቢውን ፀጥታ ያናጋ ሲሆን፡ ይህ ያልተረጋጋ ሁኔታ ባካባቢው የህገ ወጦቹ የአደንዛዡ ዕፅ ኮኬይን ነጋዴዎች ተፅዕኖ ከፍ እንዲል አድርጓል። ምክንያቱም፡ በሴኔጋል መዲና ዳካር የሚገኘው የጀርመናውያኑ የኮንራድ አድናወር ተቋም መርሀግብር ዋና ስራ አስኪያጅ ፋቱማታ ሲ ጌይ እንዳስረዱት፤ ባካባቢው የሚኖረው ድሀው ሕዝብ የዕፀ ሱሱን ንግድ አማላይ የገቢ ምንጭ ሆኖ አግኝቶዋል።

Mauretanien Kokainschmuggel

በሞሪታንያ የተያዘ ኮኬይን የጫነ አውሮፕላን


« በተለይ የኤኮኖሚው ቀውስ እና የተበላሸው የፀጥታ ሁኔታ በካዛሞንስ አካባቢ የአደንዛዡ ዕፅ ኮኬይን ንግድ እንዲስፋፋ አድርጓል። በሌሎች የሴኔጋል አካባቢዎችም የአደንዛዡ ዕፅ ኮኬይን ንግድ በቀላሉ ገንዘብ የሚገኝበት አማራጭ ሆኖ ስለተገኘ ትርጓሜው እያደገ መጥቶዋል። »
ሴኔጋል ምንም እንኳን በምዕራብ አፍሪቃ ትልቅ መሻሻል ካሳዩት ሀገሮች መካከል አንዷ ብትሆንም፡ በሀገሪቱ አሁንም ግዙፍ ኤኮኖሚያዊ ችግር አለ። የምግቡ ዋጋ እየተወደደ ከመሄዱ ጎን፡ ግማሽ የሚሆነው የሴኔጋል ዜጋ ሥራ የለውም። ፋጡማ ሲ ጌይ እንደገለጹት፡ በተለይ የወጣቱን ትውልድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ብሩሕ ለማድረግ ከተፈለገ አዳዲስ የስራ ቦታዎች ሊፈጠሩለት ይገባል። ሕዝቡም በዕለታዊ ኑሮው የሚያጋጥሙትን ፈታኝ ሁኔታዎች ማሸነፍ እንዲችል አማራጭ ዕድሎች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ምዕራብ አፍሪቃ ከደቡብ አሜሪካ ወደ አውሮጳ የሚላከው የህገ ወጡ የኮኬይን ንግድ መሸጋገሪያ መሆኑ እስከቀጠለ ድረስ፡ በዚሁ የአህጉሩ አካባቢ ውስጥ ቀርቶ ለገበያ የሚቀርበው፡ በሌላ አነጋገር ያካባቢውን ሕዝብ ለሱሰኝነት የሚዳርገው የኮኬይን መጠንም ከፍ ማለቱ አይቀርም።ተመድ ዘገባ አክሎ እንዳስረዳው፡ ደቡብ አሜሪካውያኑን ህገ ወጥ የኮኬይን ነጋዴዎችን ዕፀ ሱሱን ወደ አውሮጳ በማሸጋገሩ ስራቸው የሚተባበሩዋቸው የምዕራብ አፍሪቃውያኑ አቻዎቻቸው ለዚሁ ትብብራቸው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በኮኬይንም ይከፈላሉ። በዚህም የተነሳ በቀላሉ የማይገመት የኮኬይን መጠን በዚያው በምዕራብ አፍሪቃ በህቡዕ ለሽያጭ ይቀርባል። በ 2009 ዓም ሀያ አንድ ቶን ኮኬይን በምዕራብ አፍሪቃ በኩል ወደ አውሮጳ ሲያልፍ፡ በዚሁ ጊዜ እዚያው ምዕራብ አፍሪቃ የቀረው ዕፀ ሱሱ ኮኬይን መጠን አሥራ ሦስት ቶን እንደነበረ ታውቋል።

አርያም ተክሌ/ክላውዲያ ዛይስል

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 10.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14ISr
 • ቀን 10.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14ISr