አዝማሪ ከየት ወደ የት | ባህል | DW | 30.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

አዝማሪ ከየት ወደ የት

«ኧረ እናንተ ሰዎች ከታሪክ ተማሩ፤ እንደ አባቶቻችን ምን እንደነበሩ፤ አዝማሪ ይሉናል አዝማሪ ክሳቸዉ፤ የተበላሸዉን ስላደስልናቸዉ» ሲሉ አዚመዋል፤ አዝማሪ ከየት ወዴት » በተሰኘ ርዕስ የአዝማሪን ሥራ ለማኅበረሰቡ የሚሠጠዉን ጠቀሚታ በተመለከተ በባሕር ዳር ዩንቨርስቲ የሁለት ቀናት አዉደ ጥናት ላይ ተሳታፊ የነበሩት አዝማሪዎች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 17:10
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
17:10 ደቂቃ

አዝማሪ ከየት ወደ የት

«በትግራይም ዋጣ፤ ወሎ ላሊበላ፣ በጎንደር አዝማሪ፤ የተናቀዉ ፈላ፤ ታሪክ መርማሪዎች፤ ተፈላሳፊዎች፤ በኮንፈረንስ ዋሉ መሰንቆዎቻችን፣ ጀርመን ተከበረ በኢትዮጽያ ልጆች» ሲል አዚሞ ነበር እዉቁ አዝማሪ ደጀን ማንችሎት በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም ጀርመን ሂልደስሃይም ላይ በተካሄደዉ የመጀመርያዉ ዓለም አቀፍ የአዝማሪ ጉባዔ ላይ። ከሁለት ሳምንት በፊት ሃንቡርግ ጀርመን ላይ ስለ አዝማሪ የሚያጠናዉ ቡድን በዩኤስ አሜሪካ የሚገኘዉን አሜሪካዊ ምሁር ይዞ ከእስራኤል ታዋቂዉን አዝማሪ አስከትሎ ባህር ዳር ዩንቨርስቲ ሁለተኛ አዉደ ጥናት አካሂዶአል። በዓዉደ ጥናቱ አዝማሪዎች ምሑራንና ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ተካፋይ ነበሩ። ከጉባኤዉ አዘጋጆች መካከል በጀርመን ሃገር የሦለተኛ ዲግሪያቸዉን ያገኙትና በዩንቨርስቲዉ የአባይ የባህልና ልማት ጥናት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን አንዷለም፤ የአዝመሪ ሞያ በቂ ጥናት ስላልተደረገበት ባለሞያዎችንና ምሁራን በጋራ የሚመክሩበት መድረክ መጀመር በማስፈለጉ ጉባዔዉ መካሄዱን ገልፀዋል።

Äthiopien Internationale Azmari Konferenz

2ኛዉ የዓለም አቀፍ የአዝማሪ ጉባዔ በባሕር ዳር ዩንቨርስቲ« ኢትዮጵያ ዉስጥ አዝማሪ ብዙ ትኩረት ያልተሰጠዉ የተነፈገ ሆኖ ነዉ ለረጅም ጊዜ የቆየዉ። በአገሪቱ ዉስጥ ብዙ ባለሞያዎች አሉ። በተለይ በሰሜኑ አካባቢ ሰፊ የሆኑ ባለሞያዎች አሉ ግን ማኅበረሰቡ በሞያቸዉ እየተጠቀመ ሞያዉን ንቆት ሰዎችንም አቃሎ የሚኖርበት አጋጣሚ ስለነበረ፤ ይህንን ነገር ለምን ትኩረት አንሰጠዉም ፤ አዝማሪና ሞያዉ ማለት ልክ ባህላዊ ባንድ ማለት ነዉ፤ ድምፃዊዉም እሱ ራሱ ነዉ ግን ደራሲዉም እሱ ራሱ ነዉ፤ ተጫዋቹም እሱ ራሱ ነዉ፤ መሳሪያዉንም የሚጫወተዉ እሱ ራሱ ስለሆነ እንደ አንድ ባንድ ማለት ነዉ። ስለዚህ እንዲህ አይነት ሞያ ያለዉ ሆኖ ሳለ ትኩረት የተነፈገበት ምክንያት ምንድን ነዉ ብለን ነዉ፤ ባለሞያዎቹ የሚኖሩት ኢትዮጵያ ዉስጥ ስለሆነ በሚል ነዉ እዚህ የተደረገዉ። የዘማሪ ጥቅም እንደሙዚቃዉ ሁሉ፤ የሕብረተሰብን አንድነት ወይም ደግሞ የሕብረተሰብን ሁኔታ መያዝ የሚችል ነዉ። የሕብረተሰብን ስሜት ይቆጣጠራል፤ ብዙ ጠቀሜታ ነዉ ያለዉ።


በጎርጎረሳዊ 2012 ዓ,ም ሂልደስ ሃይም ጀርመን ላይ የተካሄደዉ የመጀመርያዉ የአዝማሪ ጉባዔ ሁለት አዝማሪዎችንና ከ 20 በላይ ኢትዮጵያዉያን የሙዚቃን የሚያጠኑና ምዕራባዉያን ምሁራንና ኢትዮጵያዉያን ተሳታፊ ነበሩ። ባሕር ዳር ዩንቨርስቲ የተካሄደዉን ሁለተኛዉን ዓዉደ ጥናት በማዘጋጀት ተሳታፊ የሆኑት በሀንቡርግ ዩንቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ ስለዓዉደ ጥናቱ ገልፀዋል።

Äthiopien Internationale Azmari Konferenz

2ኛዉ የዓለም አቀፍ የአዝማሪ ጉባዔ በባሕር ዳር ዩንቨርስቲ ፤ አዝማሪዎች ተሳታፊ ነበሩ« ሁለተኛዉ የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ አዝማሪ ጉባዔ በተለይ የባሕር ዳር ዩንቨርስቲ ባለሥልጣናትና ኃላፊዎችን ፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን፤ የዩንቨርስቲዉን ምሁራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም ራሳቸዉ ባለሞያዎቹ አዝማሪዎችን ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሮላቸዋል። በጣም በጣም ከመጠን በላይ እጅግ ደስ ብሎአቸዉ ፤ሞያቸዉ ጥበባቸዉ የፈጠራ ችሎታቸዉ ሥራቸዉ ለኛ ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የሚያበረክቱት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ፤ በዓለም አቀፍ ጉባዔ ደረጃ መከበሩና መታወቁ እጅግ ደስ አስኝቶአቸዋል። አዘጋጆቹም ምስጋና ይገባቸዋል። በተጨማሪም ከአሜሪካን አገር ፕሮፊሰር ዴቪድ ኤቫንስ የሚባሉ ከሜንፊስ ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ እሳቸዉም ተገኝተዉ የአዝማሪን እና የአሜሪካ የብሉዝ ሙዚቃን በማነፃፀር እጅግ ግሩም የሆነ ጥናት አቅርበዉ ነበር። በሌላ በኩል አዝማሪ ደጀን ማንችሎት ከቴላቪቭ እስራኤል አገር ተገኝቶ በኢትዮጵያና እስራኤል ጥንታዊ ግንኙነት በጥበቡ በሙዚቃዉ በግጥሙ በዜማዉ በመሰንቆ ተጫዉቶ እጅግ እድምተኛዉን የጉባዔ ተሳታፊዎች አስደምሞአል።»

እንደ ዶክተር ጌቲ ገላዬ በጉባዔዉ ላይ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ አዝማሪዎች ተገኝተዋል ፤ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል ሙዚቃዎቻቸዉንም አቅርበዋል። በመሰናዶዉ መጀመርያ ላይ ስንኝ የቋጠሩልን አዝማሪ ነጋ ሙሉዓለም አደገና ባለቤታቸዉ ምግብን በስልክ ከባሕር ዳር አግኝተን ስለአዉደ ጥናቱ እንዴትነት ጠይቀናቸዉ ነበር።

Äthiopien Internationale Azmari Konferenz

አዝማሪ ደጀን ማንችሎት« እዝራ በመሰንቆ ዳዊት በበገና እያጫወታት ሳታየዉ አለፈች ያን መላክተ ሞት፤ ማለት እና ያዉ መሰንቆዉ የእዝራ፤ እናም የእዝራ ልጆች ነን። አዝማሪ ማለት ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነዉ። አዝማሪ ማለት አዘመረ አመሰገነ ነዉ የሚባል። እኔ በመሰንቆ ከዘፈንኩ አርባ ዓመቱ ነዉ በመሰንቆ ነዉ የምተዳደረዉ። እኔ አዝማሪ ብለዉ ነዉ ሲጠሩኝ ነዉ የምወደዉ። አጫዋች ቢሉኝ ሰዉ በአሻንጉሊት ስለሆን የሚጫወት፤ ዘመረ አዝማሪ የሚለዉን ነዉ የምወደዉ። ከባለቤቴ ጋር ተግብተን ስንኖር 35 ዓመታችን ነዉ» የአዝማሪ ነጋ ሙሉዓለም ባለቤት ወ/ሮ ምግብ የስድስት ልጆች እናት አዝማሪ እንደሆኑ ገልፀዉልናል።

«እናቴም አባቴም አዝማሪ ነበሩ እኔም እንግዲህ አዝማሪ ነኝ ። በባህር ዳር ዩንቨርስቲ በነበረዉ ስብሰባ በጣም ደስ ነዉ ያለን። እነሱም ተከብረዉ እኛንም አስከበሩን። ስብሰባዉን የተካፈልን አዝማሪዎች በሙሉ ምስክር ወረቀት ተቀብለናል። ለኔ አዝማሪ ማለት መኩርያ፤ ማስደሰቻ ማስተዋወቅያ ነዉ ምግብ ቤትም ሆነ ሌላ ቦታ ሙዚቃ ካልተከፈተ ምንም ነገር አይሆንም። ሙዚቃ የአዝማሪ ለአንጎል መነቃነቅያ ለጭንቅላት ማደሻ አዝማሪ ነዉ ዋናዉ ማስደሰቻ። አንዳንዶች ይሰድቡናል የሚተቹን አሉ፤ ያ አለማወቃቸዉ ነዉ። አዝማሪነት ያደግንበት የተወለድንበት የዘራችን ስለሆነ አይደንቀንም። አሁን ግን መቆየት ደግ ነዉ፤ ሞያችን ሥራችን እየተተዋወቀልን ነዉ።» አዝማሪ ምግብ በቃለ ምልልሱ መሰናበቻ ለዶይቼ ቬለ ስንኝ ቋጥረዋል።

« አይመጣም እያሉ ሰዉ ሁሉ ሲቆጣ የጀርመን ጣብያችን ሰነጣጥቆት ወጣ ። ኸረ እናንተ ሰዎች ከታሪክ ተማሩ ጥንት አባቶቻችን ምን እንደነበሩ፤ አዝማሪ ይሉናል አዝማሪ ክሳቸዉ፤ የተበላሸዉን ስላደስንላቸዉ፤ ዳዊት በበገና እያጫወታት እዝራ በመሰንቆ እያጫወታት፤ ሳታየዉ አለፈች ያን መላከ ሞት »

በሥራ ላይ ሳለ ያገኘነዉ አዝማሪ ትዕዛዙ አስናቀዉ በአዝማሪነት ሞያ 25 ዓመቱን ይዞአል። በዚህ ሞያ ወደ ስራ የተሰማራዉ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ነዉ አዝማሪ ትዕዛዙ በቴክኒክ ሞያ ቢመረቅም በአዝማሪነት ሞያዉ መቀጠሉን ገልጾልናል። እንደዉም አዝማሪ ትዕዛዙ ከባልደረቦቹ ጋር እዝራ የአዝማሪዎች ማኅበርን መሥርቶአል።

Äthiopien Internationale Azmari Konferenz

በሀንቡርግ ዩንቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ


« ማኅበራችን እንግዶች ከዉጭ ሲመጡ፤ መንግስት ሲወስደን እንግዶችን ከአዉሮፕላን ማረፍያ ጀምሮ አቀባበል እናደርጋለን። አሁን ግን ትንሽ ተቀዛቅዘናል ያደግሞ ትኩረት የሚሰጠዉ አካል ትኩረት አልሰጠን ሲል እኛ ዝም ብለን ቁች ብለናል። በአሁኑ ሰዓት የ።ግል ሥራችንን እየሰራን ነዉ ያለነዉ። የማኅበሩ ዓላማ፤ የራሳችን የሆነ ምግብ አለን የራሳችን የሆነ መጠጥ አለን ፤ የራሳችን የመጠጥ ማቅረብያ አለን፤ የራሳችን የአመጋገብ ስርዓት አለን፤ የራሳችን ዘፈን ያለን። ሰዎች ከአዉሮጳ ወይም ከአሜሪካ ሲመጣ ዉድ ዉስኪ ገዝተዉ ያቀርቡለታል። እና ግን አጎዛ አድርገን ፤ በሳር ቤታችን የባህል ልብስን አድርገን፤ ጀንዴዉ፤ አጎዛዉ፤ ሰሌኑ ተነጥፎ፤ በዋንጫ በአንኮላ ጠላ፤ በብርሌ ጠጁ በመለክያ አረቄዉ በመሶብ እንጀራዉ፤ ቀርቦ ቡናም ቀርቦ፤ ያኔ አዝማሪዉ ጋቢዉን አጣፍቶ ተጨባቡን፤ ጃኑን ለብሶ፤ወዲህና ወድያ ሲል፤ ያ ነዉ መገለጫችን ያንን ለማስተላለፍ ነዉ ትግል እያደረግን ያለዉ፤ ግን ያዉ የሚመለከተዉ አካል ትኩረት ስላልሰጠን ዝም ብለን አንድ ቀን ይሆናል ብለን እየጠበቅን አለን»

ሌላዉ ከቴላቪቭ እስራኤል ወደ ባሕር ዳር የተጓዘዉ አዝማሪ ደጀን ማንችሎት ባቀረበዉ ሙዚቃ መወደሱ ተነግሮለታል።
«መሰንቆ ሲመታ ታሪክ ሲመሰክር ዛሬ በአንደበቱ፤ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ቡርባክስ መሰረቱ፤ ማክሰኝት ጎመን ጌጥ ፤ በለሳ ወገራ፤ ደንብያ ጥግ አዘዞ። መሰንቆ በራሱ አምስት መስቀል አለዉ ዝንጨቱ ከዋንዛ ጭራዉ ከፈረስ ነዉ አንፃኝ የምትኖር እንደላሊበላ የፈረስ ችራዬ ሰርታ የምታበላ፤ የፈረስ ጭራዬ ሰርታ የምታበላ። እግዚአብሄር ጥበቡን ለማን ነዉ ያደለዉ መሰንቆን ለእዝራ ዜናም ለያሬድ ነዉ መሰንቆ ሲመታ በእየሩሳሌም ላሊበላ አኖረዉ ከቤተልሄም። »

ደጀን ማንችሎት ቡርባክስ መንደር የአዝማሪ መፍለቅያ ናት ሲል ያስቀምጣታል። «ከፎገራም ከበለሳም ከሌላም ቦታ ዋናዉ የአዝማሪ መፍለቅያ ቡርባክስ ነዉ። የታወቁ ዘፋኞች ታዋቂ ባለመሰንቆዎች ፤ ትልልቅ የሞያ አባቶቻችን የመጡት ከቡርባክስ ነዉ። ቡርባክስ የሚለዉ ስያሜ ከጥንት ጀምሮ የተሰጠ መሆኑ ይነገርለታል። ይኸዉም አንድ አዝማሪ ነበር በየክፍለ አገሩ እየሄደ የሚዘፍን ሰዉ ተጣልቶ ተገድሎ ኖሮ ፤ይህ አዝማሪ ለገዳዩ ሰዉ የገደለዉን ሰዉ ዋስ ሆኖት ከቡርባክስ ይኖራል ፤ ብር በዋስ ማለት ነዉ። በብር ዋስ የሆነኝ ሰዉዩ አገር ነዉ ብሎ ሰይሞት ነዉ ፤ ከዝያ ቡርባክስ የሚለዉ ስያሜ የመጣዉ።»

Konferenz über Azmari Kultur aus Äthiopien Universität Hildesheim

1ኛዉ የዓለም አቀፍ የአዝማሪ ጉባዔ በጀርመን ሂልደስሃይም ከተማ በሚገኘዉ የዓለም የሙዚቃ ተቋም በተካሄደበት ወቅት ተጋብዘዉ የነበሩት ሁለት አዝማሪዎችመሰንቆ እንደበገና እንደከበሮ ለቤተክርስትያን እንዲያገለግል ነበር ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከቤተክርስትያን ከወጣ በኋላ ተመልሶ ክብርን አላገኘም በየሰርጉ በየቡና ቤቱ ሲዞር በመቅረቱ ክብሩን መልሶ ሳያገኝ ቀረ እንጂ ፈጣሪን ማመስገኛ ማወደሻ መሳርያችን ነዉ መሰንቆ ሲል ሁለተኛዉን ዓለም አቀፍ የአዝማሪ አዉደ ጥናት ባህር ዳር ላይ ተካፋይ የነበረዉ አዝማሪ ደጀን ማንችሎት ገልፆአል።

የዛሬ አራት ዓመት ግድም ለመጀመርያ ጊዜ እዚህ ጀርመን ዓለም አቀፍ የአዝማሪ ጉባኤ ከተካሄደ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜም ከሁለት ሳምንታት በፊት በባሕር ዳር ዩንቨርስቲ ተካሂዶአል። ይህ ዓዉደ ጥናት ለአዝማርያኑም ሆነ ለሞያዉ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዉ ይሆን በሀንቡርግ ዩንቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ በዝርዝር አስረድተዋል።
በባሕር ዳር ዩንቨርስቲ ስለተካሄደዉ ስለሁለተኛዉ ዓለማቀፍ የአዝማሪ ዓዉደ ጥናት ያዘጋጀነዉ መሰናዶ እስከዚሁ ነበር። የባሕር ዳር ዩንቨርስቲ በአዝማሪና ሥራዎቹ ላይ የጀመረዉን ጥናት ሙያዉን ይበልጥ ለማሳወቅና ለማስከበር ይረዳል ተብሎ ይታመናል። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን ማዕቀፍ በመጫን ያድምጡ።አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic