አዝመራ በማርስ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 27.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አዝመራ በማርስ

የስበት ኃይል በሌለበት ሕዋ ላይ በብዕር መጻፍ አይቻልም። ቀለሙ እንዲወርድ የሚያደርገው ስበት ስለሌለ። የስበት ኃይል በሌለበት ሕዋ ላይ መራመድ አይቻልም። ተንሳፈን እንዳንቀር የሚያግዘን ስበት ስለሌለ። የስበት ኃይል በሌለበት ሕዋ ላይ ተክሎች ማደግ አይችሉም። ተክሎቹ ውኃም ኾነ ንጥረ ነገርን መምጠጥ ስለማይችሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:35

ማርስ ላይ ማብቀል ይቻል ይኾን?

በሣይንሱ ዓለም ጥልቅ ምርምር የሚያከናውኑ ጠበብት ስበት በሌለበት ኹናቴ ማርስ የተሰኘችው ፕላኔት ላይ ተክሎችን ለማብቀል ምርምር እያከናወኑ ነው። ውጤታማ ኾነው ይኾን? ትሮንድሐይም፤ ኖርዌይ ምድር ቤት ውስጥ በእንጨት የተከለለ ቤተ-ሙከራ ውስጥ ግን ይኽን ተፈጥሯዊ ኩነት የሚሽር ሙከራ እየተደረገ ነው። በቤተ-ሙከራው ተክሎችን የስበት ኃይል በሌለበት ኹናቴ ማብቀል እንደሚቻል ተመራማሪዎች ይፋ አድርገዋል።

አስደንጋጩ ክስተት የሚፈጠረው ማርስ የተሰኘችው ፕላኔት ላይ ነው። ዘመኑም አኹን ከምንኖርበት 20 ዓመታት በኋላ። ሣይንቲስቱ ከማርስ ንጣፍ ስር የተዘረጋውን ምሥጢር ለመፍታት ቋምጠዋል። ከርሰ-ማርስ ጥናት ለማከናወንም ተጣድፈዋል። ድንገት አካባቢውን ውጦ ሊያስቀር የሚችል ሌላ ግዙፍ የአቡዋራ ቧሂት ደርሶ ጠፈርተኞቹን በብናኙ ሊቀብራቸው ከቅርብ ርቀት ሽቅብ እየተጥመለመለ ይከንፋል። ሣይንቲስቱ ነፍሳቸውን ለማዳን የቻሉትን ያኽል ተጣድፈው በመኲራኲራቸው ይወነጨፋሉ። አንድ ሣይንቲስት ግን በማርስ የአቡዋራ ብናኝ ተቀብሮ ቀርቷል። ግን አልሞተም። ይኽ (The Martian) ማርሳዊው የተሰኘው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 ለእይታ የበቃው ሣይንሳዊ ልብወለድ ፊልም አጀማመር ነው።በሳይንሳዊው ፊልም ውስጥ ባልንጀሮቹ ሞተ ብለው ጥለውት የሄዱት ጠፈርተኛ (ማት ዴመን) ከቆይታ በኋላ ሰውነቱ ላይ የተከመረውን ብናኝ አራግፎ ብድግ ይላል። በዚህ ቅጽበት ሣይንቲስቱ ማርስ ላይ የሚገኝ ብቸኛ ፍጡር መኾኑን አውቋል። ምናልባት ምድር ላይ የሚገኙት ባልደረቦቹ ወደፊት አለመሞቱን የሚያውቁ ከኾነ ወደ ምድር ሊመልሱት የሚችሉት ከ4 ዓመታት በኋላ ነው። ሣይንቲስቱ ማርስ ላይ በቀለሷት የምርምር ጎጆ ውስጥ ያለው ምግብ የሚያዛልቅ አይደለም። ቀሪ ምግቡ ግፋ ቢል 309 ቀናት ብቻ ቢያኖረው ነው። ከሦስት ዓመታት በላይ ጠፈርተኛው ምን እየበላ ሊቆይ ነው? ሕይወቱን ለማቆየት ተፈጥሯዊ ባልኾነ መንገድ ማርስ ላይ ድንች ለማብቀል ሲፍጨረጨር ይታይል።

ሙሉ ትኩረታችን ስለፊልሙ አይደለም። በፊልሙ ሞተ የተባለው ሣይንቲስት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር ተመሳሳይ ስለኾነ፥ በምንኖርባት ምድር ላይ ስለሚከናወን ምርምር እንጂ። ትሮንድሐይም፤ ኖርዌይ ምድር ቤት ውስጥ ተመራማሪዎች ከማርስ ከባቢያዊ አየር ጋር በሚመመሳሰል ተፈጥሯዊ ባልኾነ ቤተ-ሙከራ ለምግብ የሚኾኑ ተክሎችን ለማብቀል ለ10 ዓመታት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ማስገኘቱን አስታውቀዋል። ኢትዮጵያዊው ሥነ-ፈለክ እና ጠፈር ተመራማሪ አቶ ጌታቸው መኮንን ደቡብ አፍሪቃ ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፊዚክስ ያስተምራሉ። የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በቅርቡ ለማግኘትም ጥናት እያከናወኑ ነው። የመሬት ስበት በሌለበት ኹናቴ ተክሎችን ማብቀል ይቻላል ብለዋል።አስፈላጊ የኾኑ ነገሮች እስከተሟሉ ድረስ ተክሎችን ማርስ ላይ ያለምንም ተፈጥሯዊ የስበት ኃይል ያለ አፈር ማብቀል ይቻላል። ማብቀል የሚቻለው ግን አነስተኛ ተክሎችን ነው። በዓለም አቀፍ የሕዋ ጣቢያ ውስጥ እስከ 40 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ተክል ማብቀል ተችሎ ወደ ምድር ለምርምር ተልኳል። ተክሉ ተረፈ ምርትን በድጋሚ በመጠቀም ስልት ነው የበቀለው። የሕዋ ተመራማሪዋ ሣይንቲስት ኢርኔ ካሮሊውሰን ተክሉን ለማብቀል «በእናት መንኲራኲር ውስጥ የሚገኘውን ተረፈ ምርት በአጠቃላይ በድጋሚ መጠቀም አስፈልጎናል» ብለዋል። ወደ ምድር የተላከው ተክል ግን ለምግብነት የሚውል አይደለም። አኹን ኖርዌይ የሚደረገው ሙከራ ቲማቲም እና ሰላጣ ማርስ ላይ የሚበቅልበትን ሙሉ ስልት ለማግኘት ነው። ከአፈር የሚገኙ ንጥረ-ነገሮችን ተፈጥሯዊ ባልኾነ የስበት ኃይል ለተክሉ እየመጠጡ አለያም እየሳቡ በመስጠት ነው ተክሉን ያለ አፈር ማብቀል የሚቻለው።

በማርስ ላይ ተክሎችን ያለ ተፍጥሮ የስበት ኃይል ለማብቀል የሚደረገው ምርምር ትሩፋቱ ለምድርም ሊተርፍ ይችላል ተብሏል። ተክሎቹ ያለ አፈር እና ዝናም ተፈጥሯዊ ባልኾኑ መንገዶች ስለኾነ የሚበቅሉት እጅግ ወጪ የሚያስጠይቁ ማዳበሪያዎችን መጠቀም አያስፈልግም። ዝናም ዘነመ አልዘነመ ብሎ መጨነቅ ስለማይኖርም የድርቅ ስጋት አይኖርም።
እስኪ አኹን ደግሞ ወደ ማርስ እንመለስ። ቀደም ሲል ያነሳነውን ማርሳዊው የተሰኘውን ሣይንሳዊ ልቦለድ ፊልምም እንቃኝ። በፊልሙ ዋናው ገጸ-ባሕሪ በአጠገቡ የሚገኘው ምግብ ከማለቁ በፊት እመጠለያው በዘረጋው ብርሃን አሳላፊ ስስ ዳስ ውስጥ እዳሪ እንደማዳበሪያ በመጠቀም የተከለው ድንች በቅሎለት በትኩሱ ሲገምጥ ይታያል። ከመጠለያው ውጪ ቢኾን ስበት ከሌለበት የማርስ ጠባይ አንፃር የሚያላምጠው ድንች ከጉሮሮም ባልወረደ ነበር። ማርስ ላይ ጠፈርተኞቹ ከቀለሱት መጠለያ ውጪ የማርስ ከባቢ አየር ለመኖር ምቹ አይደለም። የፀሐይ ጨረረም ያለከልካይ በቀጥታ ሰውነት ላይ ስለሚርፍ እጅግ አደገኛ ነው። ታዲያ ተክሎቹን የት ነው ማብቀል የሚቻለው?እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2030 የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ ጠፈርተኞችን ወደ ማርስ የመላክ ዕቅድ አለው። በ2050 ደግሞ የሰው ልጅ ሙሉ ለሙሉ ከምድር ጥገኝነት ውጪ ኾኖ ማርስ ላይ ተክል እያበቀለ ለመኖር አልሟል። ይኽ ይሳካ ይኾን? የሕዋ ሣይንስ ምሁሩ አቶ ጌታቸው መኮንን አስቸጋሪ ቢኾንም እንደሚሳካ ግን ተስፋ አላቸው።

ያለ ስበት ኃይል ተክልን ማርስ ላይ ማብቀል እጅግ ፈታኝ ሙከራ ነው። የሰው ልጅ ወደፊት በመንኲራኲሩ ተመራማሪዎችን አሳፍሮ ወደ ማርስ ለማምጠቅ በራሱ እጅግ የተወሳሰበ ሒደት ነው። የምድር እና የማርስ ርቀትም በቀላል ቀጥተኛ ጉዞ የሚጠናቀቅ አይደለም።

በሕዋ ላይ ያለተፍጥሯዊ የስበት ኃይል ተክል ማብቀል በእርግጥ የማይቻል አይደለም። ኾኖም ወደ ማርስ የሚላኩ ጠፈርተኞችን ለረዥም ጊዜ መመገብ የሚችል ተክል ለማብቀል ግን ሣይንቲስቱ ወደ መጨረሻ ምርምራቸው እየተጠጉ ነው። ሰአቱም እየቆጠረ ነው። ናሳ ሰዎችን ጭኖ ወደ ማርስ ለመላክ የቀሩት 15 ዓመታት ናቸው።
አድማጮች «አዝመራ በማርስ» በሚል ርእስ ማርስ ላይ ያለ ስበት ኃይል ተክል ለማብቀል ስለሚደረገው ምርምር ያቀረብንላችሁ ዝግጅት በዚሁ ይጠናቀቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic