አውቶሞቢል የተሠራበት 125ኛ ዓመት፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 02.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አውቶሞቢል የተሠራበት 125ኛ ዓመት፣

ባለፈው ቅዳሜ፣ ጥር 21 ቀን 2003 ፣ ካርል ቤንዝ የተባሉት ጀርመናዊ ኢንጅኔር፤ በዓለም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎዳና መሽከርከር የሚችል አውቶሞቢል ሠርተው የፈጠራ ውጤታቸውን ያስመዘገቡበት 125 ኛ ዓመት በልዩ ሥነ ሥርዓት ታስቧል።

default

የሀገሪቱ መሪ ፣ ወ/ሮ አንጌላ ሜርክልም ፣ ክብረ-በዓሉ በተከናወነበት በእሽቱትጋርት በመገኘት ንግግር አሰምተዋል። ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፣ ያለፉትን 125 ዓመታት የተሽከርካሪ አሠራር ሥነ ቴክኒክ መለስ ብለን እንቃኛለን።

(ሙዚቃ)-----

በዘመኑ ብርቅ ድንቅ የሥነ ቴክኒክ የፈጠራ ውጤት ነበረ፤ ከሠሪዎቹ ጀርመናውያን ይልቅ ጎረቤቶቻቸው ፈረንሳውያን ነበሩ በጣም የተደመሙት! «አውቶ፣» ፣ « አውቶሞቢል» በመባል በታወቀው የጀርመኖች የፈጠራ ውጤት!። በአሁኑ ዘመን እንደ ትንሽ ተወዳጅ ልጅ የሚታየውን አውቶሞቢል ታላላቅ ባለኢንዱስትሪ መንግሥትት ሁሉ ይሠሩታል። ብዙም ሳይቆይ 4 ተሽከርካሪ ጎማዎች ያሉት እንዲሆን ተደርጎ ቢሠራም፤ የመጀመሪያው ተሽከርካሪ (አውቶሞቡል ) ባለ 3 ጎማ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

ኢንጂኔር ካርል ቤንትዝ፤ እ ጎ አ ጥር 29 ቀን 1886 ዓ ም፤ በሞተር ለሚንቀሳቀሰው ባለ 3 ጎማ ተሽከርካሪአቸው፣ የፈጠራ ወጤት ባለቤትነት ይታወቅላቸው ዘንድ ለሚመዘግበው መሥሪያ ቤት ማመልከቻ አቀረቡ። በዓለም ውስጥ የመጀመሪያ የሚሰኘው አውቶሞቢላቸው፣ 0,8 የፈረስ ጉልበት ማለትም 0,6 ኪሎዋት ኃይል ነበረው። ከፍተኛ ፍጥነቱ ፤ በሰዓት 18 ኪሎሜትር!

አውቶሞቢል ተሠርቶ ጎዳና እንዲሽከረከር የበቃበትን 125 ኛ ውን ዓመት ክብረ በዓል አስመልክተው የጀርመን መራኂተ-መንግሥት፤ ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል፤ እሽቱትጋርት ላይ ባሰሙት ንግግር ላይ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«በአሁኑ ጊዜ እንደምናውቀው፤ አውቶሞቢል፤ በዓለም ዙሪያ ከቦታ -ቦታ በፍጥነት ለመንቀሳቀስ ካስቻሉት የፈጠራ ውጤቶች አንዱ ነው። ጀርመን የአውቶሞቢል አገር ናት!።

የአውቶሞቢልን አዲስ ሥነ- ቴክኒክ በተመለከተ ጀርመን፤ ምንጊዜም አዳዲስ የፈጠራ እርምጃዎችን በማንቀሳቀስ ፤ ማለፊ ሥም ያላት አገር ናት። ቤንዚን በመጠቀም የሚከሠቱ ጎጂ ነገሮችን ለመግታት በየጊዜው እርምጃ ተወስዷል። ሥነ-ቴክኒኩም በየጊዜው እንዲሻኡል ተደርጓል። በአሁኑ ጊዜ ወደ ውጭ ከምንልካቸው የታወቁ የኢንዱስትሪ ምርቶች መካከል አንዱ ፣ ንግዱም የደራው፤ የአውቶሞቢል ኤኮኖሚን የሚመለከተው መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም ። ይሁንና እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ፣ አሁንም ብርቱ ፈተና ይጠብቀናል። ስለሆነም፣ አዲስ ሥነ ቴክኒክ የውይይት አጀንዳ ሆኗል ። የተጣመረ ሥነ-ቴክኒክ፣ በኤሌክትሪክ ሞተር የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ለመሥራትም ሆነ ለማምረት ትኩረት አድርጓል። እ ጎ አ እስከ 2020 አንድ ሚልዮን በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶሞቢሎች ይኖሩናል።»

ፍጥነትን ለማሻሻል የሚረዳ መሣሪያ ጎትፍሪድ ዳይምለር በተናጠል እሽቱትጋርት ውስጥ አንድ መሣሪያ ሠሩ። ዳይምለር ፣ ከሞተር ሠሪ ቪልሄልም ማይባህ ጋር በመተባበርም ሁለቱም አመርቂ ተግባር ማከናወናቸው ይነገርላቸዋል። አውቶሞቢል በሞተር ኃይል እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ሲታሰብ በመጀመሪያ የሚጠቀሱት ሌላው ጀርመናዊ ኒኮላውስ አውጉስት ኦቶ ናቸው። እ ጎ አ በ 1876 ዓ ም፣ ለሠሩት ሞተር (የኦቶ ሞተር በማባልም ይጠቃሳል)የፈጠራ ውጤት ባለቤትነት ሰነድ አግኝተው ነበር። በ 1892 ሩዶልፍ ዲዘል የላቀ ጉልበት ያለው ተመሳሳይ ሞተር ሠሩና በበርሊን የፈጠራ ውጤት ባለቤትነታቸውን አሥመሠከሩ።

የሚገርመው የመጀመሪያው እጅግ ፈጣን አውቶሞቢል፣ በቤንዚን ኃይል የሚሽከረከረው ሳይሆን፣ በኤልክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሰው ነበረ። በ 1901 (እ ጎ አ)፣ አንድ አውቶሞቢል በሰዓት 100 ኪሎሜትር ፍጥነት ሊኖረው እንደሚችል በዘመኑ በተደረገ ሙከራ ተረጋገጠ። በቤንዚን የሚንቀሳቀሱ አውቶሞቢሎች የመሪነቱን ሥፍራ እስኪይዙ ጊዜ ወስዷል። ሙከራው በመቀጠል ላይ እንዳለ በዩናይትድ እስቴትስ በተለያየ የኃይል ምንጭ የሚነቀሳቀሱ አውቶሞቢሎች በ 1900 ዓ ም ይሠሩ ነበር። በአጠቃላይ በዚያ ዘመን አውቶሞቢል ከሚሠሩ 75 ፋብሪካዎች፤ 4,192 ተመርተው ነበር። 1,688 ቱ በእንፋሎት ኃይል የሚንቀሳቀሱ፣ 1,575 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ በቤንዚን ኃይል የሚሽከረከሩት ደግሞ 929 ብቻ እንደነበሩ ይታወቃል።

በቤንዚን ኃይል የሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች እ ጎ አ በ 1920 ኛዎቹ ዓመታት ተሻሽለው በመሠረታቸው፣ ፍጥነታቸው እንዲጨምር በመደረጉ ፣ የሚጠቀሙበት ቤንዚንም ዋጋ ርካሽ ስለነበረ፣ በሚደክም ባትሪ ሳቢያ ራቅ ወዳለ ቦታ መጓዙን እምብዛም ከማይደፍሩት ተሽከርካሪዎች የላቀ ተወዳጅነት አገኙ።

የመጀመሪያዎቹ የአውቶሞቢል ፋብሪካዎች በአውሮፓና አሜሪካ የተገነቡት ከ 1890 አንስቶ ነው። በአሜሪካ፤ ሄንሪ ፎርድ የተባለው አውቶሞቢል ሠሪ፣ ለሃብታሞች ብቻ ሳይሆን፤ መለስተኛ ገቢ ያላቸውም ሁሉ የመኪና ባለቤቶች መሆን የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ዲትሮይት በተሰኘችው ከተማ ያን ያህል ውድ የማይባሉ ተሽከርካሪዎች እንዲሠሩ አበቃ። እናም በዚያ ዘመን በተለይ እ ጎ አ ከ 1908 ዓ ም አንስቶ ተወዳጅ የነበረው የሄንሪ ፎርድ (T-Model)ተሽከርካሪ፤ እስከ 1927 ዓ ም ድረስ ሞዴሉ ሳይለውጥ ይመረት ነበር። በዚህ ሞዴል የተሠሩት አውቶሞቢሎች ቁጥር 15 ሚሊዮን ሲሆን፣ እስከ 1972 ለ 45 ዓመታት ክብረ-ወሰን ይዘው መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

በዓለም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አውቶሞቢል ወደሠራችው ሀገር ወደ ጀርመን ስንመለስ፣ በ 1926 ጎትሊብ ዳይምለርና ካርል ቤንትዝ የአውቶሞቢል ፋብሪካዎቻቸውን አዋኻዱ።

በዳይምለር- ቤንዝ ፋብሪካ ሥም የሚመረቱ አውቶሞቢሎች «ሜርሰደስ » የሚል ሥያሜ ተሰጣቸው። የሜርሰደስ ኮከብ ምልክት እየተደረገባቸው የሚመረቱ አውቶሞቢሎች ዋጋቸው በጣም ውድ ከመሆኑ የተነሣ ፣ ያኔ ለተወሰኑ ሰዎች በትእዛዝ ነበረ የሚሠሩት። ዛሬም ቢሆን በጣም ውድ ናቸው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ ፣ ወደ 90 በሚጠጉ ፋብሪካዎች ይሠሩ የነበሩ የጀርመን አውቶሞቢሎችም ሁሉ ዋጋቸው ውድ እንደነበረ ነው የሚነገረው።

በ 1930 የዳይምለር ሞተር አክሲዮም ማኅበር መሪ የነበሩት ታዋቂ እንጂኔር ፈርዲናንድ ፖርሸ፣ ከአብዛኛው ህዝብ እጅ ሊገባ የሚችል ተሽከረካሪ ለመሥራት አቅደው የራሳቸውን ድርጅት አቋቁመው እንደነበረ ቢታወቅም ከ 4 ዓመት በኋላ፣ በዘመኑ ከነበረው መንግሥት ጋር በፈረሙት ውል መሠረት «ፎልክስቫገን» (የህዝብ አውቶሞቢል) የተሰኘውን ተሽከርካሪ ለማምረት ተነሣሱ። በ 1937 የፎልክስቫገን ቅርጽ ተነደፈ። በዓመቱ የሚሠራበት ቦታ በሰሜን ጀርመን ተመረጠ። ይሁንና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመጀመሩ ፣ አውቶሞቢል ሳይሆን ጦር መሣሪያ ይመረት ጀመር። የፎልክስቫገን ሥራ የተጀመረው ጦርነቱ ባለቀ ማግሥት ነው። በ 1954 በ ቮልፍስቡርግ የተሠሩት አዲሶቹ ፎልክስቫገን ተሽከርካሪዎች ቁጥር 50,000 ደረሰ። በ 1972 የጢንዚዛ ቅርጽ ያላት፤ ጀርመናውያን «ኬፈር» የሚሏት ተሽከርካሪ ፣ ከ 15 ሚሊዮን በላይ ተመርታ፣ የፎርድ )ቲ ሞዴልን) ከብረ-ወሰን ነጠቀች።

(የተሰማው በ 1960ኛዎቹና 70ኛዎቹ ዓመታት፣ 34 የፈረስ ጉልበት የነበራት «ፎልክስቫገን» አውቶሞቢል ድምፅ ነበረ)

አውቶሞቢሎች በቀጥታ ለህዝብ፣ ለቤተሰብ መገልገያ ብቻ ሳይሆን፣ ለእስፖርት ውድድርም መዋል ከጀመሩ ቆይቷል።

(የአውቶሞቢል ድምፅ)---------

«እንደምትመለከቱት 34 የፈረስ ጉልበት ያላት «ፋው ቬ ኬፈር» (የጢንዚዛ ቅርጽ ያላትን አውቶሞቢል ማለታቸው ነው) ያኔ ፣ በ 60ኛ ዎቹና 70ኛዎቹ ዓመታት ባለ 34 የፈረስ ጉልበት አውቶሞቢል የምትጠቀምበት የቤንዚን መጠንና በአሁኑ ጊዜ ባለ 500 የፈረስ ጉልበት ተሽከርካሪዎች የሚወስዱት ቤንዚን መጠን ያው ነው። ቆጣቢ ሞተር በመሥራት ረገድ ትልቅ ለውጥ ነው የተደረገው። በተቻለ መጠን በቁጠባና በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠቀም የሚያስችል እርምጃ ነው የተወሰደው። ለአስፖርት የሚሆነው የውድድር አውቶሞቢል፤ በግልፅ ለመናገር የቤተ-ሙከራ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ለአውቶሞቢል ሠሪዎች ጭምር ማለት ነው። ምክንያቱም፣ ፈጣን እርምጃ የሚጠይቅ በመሆኑ ተወዳዳሪዎች በልጠው እንዳይገኙ ራሱ ልቆ ወይም ቀድሞ መገኘትን ነው የሚሻው»

ጢንዚዛ የምትመስለው የፎልክስባገን አውቶሞቢል ፋብሪካ ከሰሜን ጀርመን ፤ ቮልፍስቡርግ፣ ወደ ሜክሲኮ ከተዛወረ ከ 30 ዓመታት በላይ በኋላ፤ እ ጎ አ ሐምሌ 30 ቀን 2003 የፎልክስቫገን ሥራ በሜክሲኮም ከእነአካቴው ቆመ። ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ማለፊያ ሥም ካተረፉት በዛ ካሉት የአውቶሞቢል ፋብሪካዎቿ መካከል፤ ትልቅ ስም ያላቸው የአውቶሞቢል ፋብሪካዎች፣ ፎልክስቫገን እንዲሁም አውዲ፣ የዳይምለር ቤንትዝ «ሜርሰደስ » ና «ቤ ሜ ቬ» ናቸው። በዓለም ውስጥ በብዛት አውቶሞቢል በመሸጥ የታወቁት 3 ታላላቅ ፋብሪካዎች፣የጀርመኑ ፎልክስቫገን፣ የጃፓኑ ቶዮታና የአሜሪካው ጀኔራል ሞተርስ ናቸው።

በ 2010 በዓለም ዙሪያ 60 ሚሊዮን ያህል አዳዲስ አውቶሞቢሎች ተሸጠዋል። ዘንድሮ በ 2011 67 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። በዓለም ዙሪያ የአውቶሞቢሎች ቁጥር አንድ ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይታሰባል።

አውቶሞቢል ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ሲሆን፤ የንጉሠ ነገሥቱን አውቶሞቢል ያሽከረከሩ ዘንድ ለሥልጠና ወደ ጀርመን ብቅ ብለው የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፣ በመሰንቆ ራሳቸውን አጅበው ያንጎራጎራቸውን ባህላዊ ዜማዎችም በዚያው ዘመን የድምጽ መቅረጫ ዘዴ ማስቀረጻቸው የሚታወስ ነው።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ