አውሮፓ፤ የኤኮኖሚ ዕድገትና የሥራ ገበያ ችግር | ኤኮኖሚ | DW | 31.03.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አውሮፓ፤ የኤኮኖሚ ዕድገትና የሥራ ገበያ ችግር

የብራስልሱ የመሪዎች ጉባዔ

የብራስልሱ የመሪዎች ጉባዔ

በዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ፍጻሜ የተለመደው የመሪዎች ጉባዔ ከሥራ ገበያው ሁኔታ እስከ ጋራ የኤነርጂ ፖሊሲ ጽንሰ ሃሣብ ድረስ በአንዳንድ ጉዳዮች ከመግባባት ቢደርስም በሌል በኩል አጥጋቢ አልነበረም የሚሉ ተቺዎች መኖራቸውም አልቀረም። የብራስልሱ ጉባዔና ስብሰባውን በሂደቱ ጋርዶት ያለፈው በፈረንሣይ የሥራ ገበያ ለውጥ የቀሰቀሰው ብርቱ ተቃውሞ በዚህ ዝግጅት አጣምረን የምንመለከታቸው ሁለት ርዕሰ-ጉዳዮች ናቸው።

በጀርመን ማለቂያ ያጣ የሠራተኛ አድማ፣ በፈረንሣይ ዓመጽ የተዋሃደው ተቃውሞ፣ በአጠቃላይ ከፍተኛ የሥራ አጥ ብዛትና የመነመነ የኤኮኖሚ ዕድገት፤ የአውሮፓውያኑ መንግሥታት መሪዎች ባለፈው ሣምንት በምጣኔ-ሐብት ፖሊሲያቸው ላይ ለመምከር የተሰበሰቡት የሕብረቱ ገጽታ ይህን በመሰለበት ወቅት ነው። የመንግሥታቱ መሪዎች በያመቱ በወርሃ-መጋቢት እየተሰበሰቡ የኤኮኖሚ ዕድገትን ለማራመድና የሥራ መስኮችን ለማስፋፋት ከስድሥት ዓመታት በፊት የተስማሙበት “የሊዝበር ስትራቴጂ” የተሰኘ ዕቅድ ምን ዕርምጃ እንዳሣየ ሲመረምሩ ቆይተዋል። የሊዝበኑ ዕቅድ እርግጥ እስካሁን ብዙም የረባ ለውጥን አላስከተለም። በመሆኑም የመንግሥታቱ መሪዎች ዘንድሮ ጭብጥ ግቦችን አስቀምጦ ለመለያየት ቁርጠኛ ሆነው ነበር ወደ ብራስልስ ብቅ ያሉት።

“የሊዝበኑ ስምምነት” ዓላማ የአውሮፓን ሕብረት ክልል እስከ 2010 በዓለም ላይ ጠንካራ የኤኮኖሚ ዕድገት አካባቢ ማድረግ እንደነበር የሚታወስ ነው። ግን ዛሬ ሃሣቡ የሩቅ ሕልም መስሎ ነው የሚታየው። በብራስልሱ የሁለት ቀናት ጉባዔ ዋዜማ በተለይም የኤነርጂ ጉዳይ በዓባል መንግሥታቱ ዘንድ አከራካሪ ሆኖ ታይቷል። ካትሪናን የመሰለ ሃያል ማዕበል በሜክሢኮው ባሕረ-ሰላጤ የነዳጅ ዘይት ማውጣት ተግባርን ክፉኛ ማሰናከል፣ ሩሢያ በኡክራኒያ ላይ የጋዝ ቧምቧዋን በመዝጋት ከፍተኛ ዋጋ መጠየቋ፣ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ቻይናና ሕንድም ሰፊ በሆነ ፍጆት ለኤነርጂ ዋጋ ወደላይ መተኮስ መንስዔ መሆናቸው፤ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የአውሮፓን ሕብረት ክፉኛ ማስደንገጡ አልቀረም። ለዚህም ነው፤ ችግሩ፤ ርካሽ የኤነርጂ አቅርቦትን ዘላቂ አድርጎ የማረጋገጡም ጉዳይ በሕብረቱ ዘንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓቢይ ርዕስ ሊሆን የበቃው።

የሕብረቱ ኮሚሢዮን ርዕስ ሮማኖ ፕሮዲ በበኩላቸው በአውሮፓ ደረጃ የኤነርጂ አጠቃቀም ቅንጅት መኖሩን፤ ማለትም የጋራ ፖሊሲ መኖሩን ይመርጣሉ። ባሮሶ በጉባዔው ዋዜማ እንዲህ ሲሉ ነበር በመንግሥታቱ መሪዎች አቅጣጫ የቅስቀሣ ሃሣባቸውን ሲሰነዝሩ “የጋራ የኤነርጂ ፖሊሲ እንደሚያስፈልገን አጠቃላይ የሃሣብ ስምምነት አለ። የተለያዩ ፖሊሲዎች ወይም የተለያዩ ገበዮች መኖራቸው ትርጉም አይኖረውም። በሌላ በኩል ፍላጎቱ ካለንና ጠንከር ብለን በጋራ ከሰራን ግን ብዙ መጠቀም መቻላችን ግልጽ ነው” ነበር ያሉት።
ይሁንና አብዛኞቹ የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት የኤነርጂን ፖሊሲ ብሄራዊ ጉዳይ አድርገው መቀጠሉን ነው የሚሹት። ለምሳሌ ፈረንሣይና ስፓኝ በቅርቡ የሕብረቱ ሃገራት ተፎካካሪ ኢንዱስትሪዎች ሃይል አመንጭ ኩባንያቸውን ገዝቶ ለመጠቅለል ያደረጉትን ሙከራ ለማደናቀፍ ሲጥሩ ታይተዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ብሪታኒያ በኤነርጂ ፖሊሲዋ አኳያ ያላትን የመወሰን ሥልጣን ብራስልስ ላይ ተቀማጭ ለሆነው ለሕብረቱ ማዕከል አሳልፎ ለመስጠት ጨርሶ ፈቃደኛ አይደለችም።

በብሪታኒያ አባባል እርግጥ ለተሻለ ቅንብር መወያየት ይቻላል። ግን ለምሳሌ የትኛው የሃይል ምንጭ በምን መጠን ወደ አገር እንደሚገባም ሆነ በአቅርቦቱ ዋስትና ጉዳይ መወሰኑ ለእያንዳንዱ አገር ሊተው የሚገባው ጉዳይ ነው። የለንደን አቋም እንግዲህ አንድ ወጥ ፖሊሲ የሚሹትን ወገኖች ብዙም የሚያበረታታ አይደለም። እርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒይ ብሌይር ችግሩን አቃለው መቅረባቸው አልቀረም። “በመንግሥት መቀመጫዬ በ Downing Street 10 ጥቅም ላይ የሚውለው የኤሌክትሪክ ሃይል ከአንድ የፈረንሣይ ኩባንያ፤ ውሃውም ከጀርመን ሲሆን፤ ከአራቱ ጋዝ አቅራቢ ኩባንያዎች ሶሥቱ ደግሞ የብሪታኒያ አይደሉም። ይህ ለኛ ችግር አይደለም” ሲሉ ነበር ብሌይር ለዘብ ብለው የቀረቡት።
ግን ሃቁ ልዩነቱ እንዲህ ተቃሎ የሚታይ አለመሆኑ ነው። በኤነርጂው ፖሊሲና በውስጣዊ የሥራ ገበያ ነጻ መለቀቅ ጉዳይ ጀርመንም ብትሆን የአውሮፓ ኮሚሢዮን ተጨማሪ ሥልጣን ማግኘቱን ያን ያህል አትፈቅደውም። ጀርመን የሥራ ገበያውን በተመለከተ ከአዳዲሶቹ የምሥራቅ አውሮፓ የሕብረቱ ዓባል አገሮች ሠራተኞች ወደዚህ መጉራፋቸውን ቢቀር እስከ 2009 ዓ.ም. ገድባ ለመያዝ ነው የምትፈልገው። ከአምሥት ሚሊዮን የሚበልጡትን የራሷን ሥራ አጦች ችግር በቅድሚያ ለመፍታት ትፈልጋለች።

የብራስልሱ ጉባዔ የውስጣዊውን ገበያ ይዞታ ለማለዘብ የሚጥሩትና ብሄራዊ ጥቅምን በመከላከል ዓላማቸው የጸኑት መንግሥታት ሁለት ተጻጻሪ አመለካከቶች ጎልተው የታዩበት ነበር። ሆኖም የሁለቱንም ወገን ፍላጎት ያቻቻለ አስታራቂ መፍትሄ በመፈለጉ ጉዳዩ የለየለት ውዝግብን አላስከተለም። ወደፊት የኤነርጂ ፖሊሲን ለማጣጣምና ከዋነኛዋ ጋዝ አቅራቢ ከሩሢያ ጋር ውል ለማስፈን ከስምምነት ተደርሷል። የአልግሎት ሰጪው ዘርፍ የገበያ ነጻነትም በዝግመቱ ዕውን እየሆነ እንዲሄድ ለማድረግ፤ የቢሮክራሲ መሰናክሎችንም ለማስወገድ አንድ ድምጽ መሰማቱ አልቀረም።

23 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጉት የሕብረቱ አነስተኛና መለስተኛ ኩባንያዎች ከቢሮክራሲ መዘዝ እንዲላቀቁና በሚገባ እንዲራመዱ፤ የምርምር ተግባርም ከፍ እንዲል ግቦች ተነድፈዋል። ጥያቄው ቃልና ተግባር ተጣጥመው መታየታቸው ላይ ነው። ከሊዝበኑ ስምምነት ወዲህ የታየው ሃቅ ለዚህ የሚያበረታታ አይደለም።

የሥራ አጦችን ቁጥር የመቀነሱ ጉዳይ አንዱ ነጥብ የነበረበትን የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ የፈረንሣዩ የሥራ ገበያ ለውጥ የቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋርዶት መሰንበቱም አልቀረም። የፈረንሣይ መንግሥት የማሕበራዊ ፖሊሲ ለውጥ ለማስፈን በሚያደርገው ጥረት በሠራተኞች በተለይም በወጣቶች ተቃውሞ ተወጥሮ ነው የሚገኘው። የአገሪቱ አሠሪዎች ወጣት ተቀጣሪዎችን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት በቀላሉ ከሙያ መስካቸው እንዲያሰናብቱ ጥርጊያ የሚከፍተው የመንግሥቱ ለውጥ በቀላሉ ተቀባይነት የሚያገኝ አልሆነም።
በጉዳዩ እየተካረረ መሄድ ፈረንሣይ አገር-አቀፍ ከሆነ ረጅም የሠራተኛ አድማ የተቃረበች ነው የሚመስለው። ግትር አቋም የሚያራምደው የፈረንሣይ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶሚኒክ-ዴ-ቪልፓን ደጋግመው የውይይት ጥሪ ቢሰነዝሩም ከአገሪቱ የሙያ ማሕበራት ተጠሪዎች ጋር የተካሄደው ንግግር እስካሁን ችግሩን ሊያበርድ አልቻለም። በፈረንሣይ ዋነኛው የተማሪዎች ማሕበርም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ቀጥተኛ ንግግር ለማካሄድ የቀረበለትን ግብዣ ባለፈው ሰንበት ሳይቀበለው ቀርቷል። ይህም ካለ ምክንያት አልነበረም።

“ግብዣው ላይ የሰፈረው ከቪልፓን ጋር ስለ አዲሱ የሥራ ውል መነጋገር እንዳለብን ነው። ግን እኛ የምንፈልገው በለውጡ ላይ ስለሚደረጉ ስለሆኑ ጥቃቅን ማሻሻያዎች አይደለም። የመንግሥቱ ለውጥ ተቀጣሪዎችን በሁለት መደብ የሚከፍል በመሆኑ በአጠቃላይ መወገድ ይኖርበታል። አንጋፎቹ ሁሉም መብት ይኖራቸዋል፤ ወጣቶቹ ግን ምንም አይቀራቸውም። በዚህ ሆኔታ ለንግግር አንሄድም” ሲል ነው የተማሪው ማሕበር አፈ-ቀላጤ ካርል ሽቱክል የተናገረው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶሚኒክ-ዴቪልፓን ባለፉት ቀናት ባሣዩት ግትርነት በወጣቱ ትውልድ ዘንድ ለተፈጠረው ፍርሃቻና ለሕዝቡ ስሜት ደንታ እንደሌላቸው አሣይተዋል ሲሉ ነው ተማሪዎቹ የሚወቅሱት። ፈረንሣይ ውስጥ የወጣት ሥራ-አጦች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። መንግሥት ራሱ እንደሚለው ለውጡን የፈለገውም ለወጣቶች አዳዲስ የሥራ መስኮችን ለመፍጠር ነው። ግን ብዙሃኑ የፈረንሣይ ሕዝብ ለውጡን አምኖ አልተቀበለውም፤ አልፈቀደውም።
በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕጉን በአደባባይ ሲቃወሙ ሣምንታት አልፈዋል። ተቃውሞውም ዓመጽ የጋረደው እየሆነ መምጠቱ በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው። በርካታ መደብሮች ተዘርፈዋል፣ አውቶሞቢሎችም በእሣት ቃጠሉ ጋይተዋል። ተቃውሞው ከጀመረ ወዲህ በመቶዎች የሚገመቱ ሰዎች ሲቆስሉ ከሺህ የሚበልጡ ደግሞ ተይዘው መታሰራቸው ነው የሚነገረው።
የአገርግዛት ሚኒስትሩ ኒኮላይ ሣርኮዚይ ውዝግቡ እንዳይካረር ማስጠንቀቅ ይዘዋል። የፈረንሣይ የሙያ ማሕበራት መንግሥት ያወጣውን ሕግ መልሶ ይስብ ዘንል ለማስገደድ ከትናንት በስቲያ የአንድ ቀን የሥራ ማቆም አድማ አካሂደዋል። በአገር-አቀፍ ደረጃ አያሌ ሠራተኞች የተሳተፉበት አድማ የተማሪዎቹን ተቃውሞ ሃይል እንደሰጠው አያጠራጥርም። ፈረንሣይ ወዴት እያመራች ነው? ማለቂያው የማይታወቅ የሠራተኛ አድማና የወጣቶች ዓመጽ የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ሁኔታውን የባሰ ቀውስ ላይ እንዳይጥለው በጣሙን ያሰጋል።