አውሮፓውያን ከቻይና የሚሹት የአፍሪቃ ልማት ሽርክና | ኤኮኖሚ | DW | 06.02.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አውሮፓውያን ከቻይና የሚሹት የአፍሪቃ ልማት ሽርክና

የአውሮፓ ኮሚሢዮን በቅርቡ በአፍሪቃ ዕድገት ላይ ከቻይና ጋር ሽርክና ለመፍጠር የሚያስችል አንድ ዕቅድ እንደሚያስተዋውቅ የሕብረቱ የልማት ኮሜሣር ሉዊ ሚሼል ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ገልጸው ነበር። የዚህ ዕቅድ መንስዔና ዓላማው ምንድነው?

default

የቻይና ተጽዕኖ በአፍሪቃ እጅግ እየጠነከረ መሄድ ለአውሮፓውያን መንግሥታት የራስ ምታት ሆኖ የቆየ ጉዳይ ነው። ቻይና ከአፍሪቃ ጋር ያላት የኤኮኖሚና የንግድ ግንኙነት በብዙ ዕጅ እየሰፋ ሲመጣ ቀጣይነት በማግኘቱም የሚጠራጠር የለም። ይህ ደግሞ የአፍሪቃ የተፈጥሮ ጸጋ ይበልጥ እየተፈለገ በሄደበት በዛሬው ወቅት አውሮፓውያንም ጥቅማቸውን ለማስከበር የግንኙነት ተሃድሶ ለማስፈን መላ እንዲመቱ እያደረገ ነው። የሕብረት የልማት ኮሜሣር ሉዊ ሚሼል በአፍሪቃ ላይ የአውሮፓና የቻይና የልማት ሽርክና ያሉትን ዕቅዳቸውን በፊታችን መጋቢት ወር ቤይጂንግን ከጎበኙ በኋላ በይፋ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
የግዙፏ የእሢያ አገር ተጽዕኖ በተፈጥሮ ሃብት በታደለችው በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም እያደገ መሄድ አውሮፓውያኑን ይበልጥ እያሰጋ መምጣቱ የተሰወረ ነገር አይደለም። የሉዊ ሚሼል ጥረትም ከዚህ ሃቅ የመነጨ ሣይሆን አልቀረም። ኮሜሣሩ ራሳቸው እንዳሉት አፍሪቃ ዛሬ ከፈላጊ ይልቅ ተፈላጊ እየሆነች ነው የምትገኘው። የሉዊ ሚሼል ቃል-አቀባይ ጆን ክላንሢይ እንዲህ ይላሉ።

“እርግጥ ነው ኮሚሢዮኑ በጥር ወር መጀመሪያ ገደማ፤ እኛ እንደምንጠራው የሥስት ወገን ሽርክና በአውሮፓ ሕብረት፣ በቻይናና በአፍሪቃ መካከል መስፈን የሚችልበትን ሁኔታ ለማፈላለግ ዕቅድ እንዳለው አስታውቆ ነበር። የሽርክናውን ትክክለኛ ይዘት በተመለከተም ኮሚሢዮኑ በወቅቱ በሥራ ላይ ይገኛል። ይህ ደግሞ ገና መጠናቀቅ ያለበት ጉዳይ ነው። ሽርክናውን በማራመዱ በኩል የመጀመሪያው ዕርምጃ እንግዲህ ይህ ነው የሚሆነው። እና በወቅቱ ለመናገር የምችለው ከኮሚሢዮኑ ፕሬዚደንት መግለጫ በኋላ ሽርክናው ሊሰፍን የሚችልበትን ሁኔታ እያጣራን መሆናችንን ነው”

ክላንሢይ የቻይና ባለሥልጣናት ሃሣቡን ወዲያው በመደገፍ አበረታች ምላሽ መስጠታቸውንም አስረድተዋል። ቻይና የተፋጠነ ዕድገቷ የሚጠይቀውን የነዳጅና ሌላ የተፈጥሮ ሃብት ጥም ለመወጣት ዕጣዋን በዚሁ ጸጋ በሰፊው ከታደለችው ከአፍሪቃ ጋር በጥብቅ ማስተሳሰሯ ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው። አድጎ ማሳደግ የሚል መርኋ በአፍሪቃ መንግሥታት ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እያገኘ መሄዱም አልቀረም። ቻይና ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር የምታካሂደው ንግድና የምታቀርበው መዋዕለ-ነዋይ መጠን በ 50ኛዎቹ ዓመታት ከአሥር ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም ነበር።
ዛሬ ግን አርባ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይጠጋል። አፍሪቃ ወደ ቻይና የምትሸጠው ምርትም በአሥር ዕጅ በመጨመር ከሃያ ቢሊዮን ዶላር በልጧል። የቻይና ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ በአፍሪቃ በ 2005 1.3 ቢሊዮን ዶላር ሰደርስ በርሷው ገንዘብ አፍሪቃ ውስጥ የተቋቋሙት ኩብንያዎች ደግሞ ከ 800 ይበልጣሉ። በቻይና ዕርዳታ አፍሪቃ ውስጥ የሚራመዱ ፕሮዤዎች ቁጥርም እንዲሁ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። ትምሕርት ቤቶች፣ መንገዶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንግሥታዊ ሕንጻዎችና ስታዲዮሞችን የመሳሰሉትን ያዳርሳል። ቻይና ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ለ 31 ሃገራት የ 1.3 ቢሊዮን ዳላር የዕዳ ስረዛም አድርጋለች።
አፍሪቃውያን በሚሸጡላት በርካታ የምርት ዓይነቶች ላይ የቀረጥ ነጻነት ማስፈኗም ሌላው ትስስሩን ለማጠናከር የበጀ ዕርምጃ ነው። ቻይናን በአፍሪቃ መንግሥታት ዘንድ ተመራጭ ያደረጋት እርግጥ ይህ ሰፊ የንግድና የኤኮኖሚ ተባባሪነቷ ብቻ አይደለም። በሌሎች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት በሚል የውጭ ፖሊሲዋ እንደ አውሮፓውያኑ በጎ አስተዳደርንና የሰብዓዊ መብት ከበሬታን የመሳሰሉ የፖለቲካ ቅድመ-ግዴታዎች የማታቀርብ መሆኗም አመቺ ያደርጋታል። ትስስሩን ያፋጠነውም ይሄው ነው። አውሮፓውያን መንግሥታት በአንጻሩ ለዓመታት ሲከተሉት የቆየው የልማት ፖሊሲ ፍቱን መሆኑን ዛሬ አጠያያቂ የሚያደርጉት ብዙዎች ናቸው። ለአሠርተ-ዓመታት ሰፈስ የኖረው የልማት ዕርዳታ ፍሬያማነት በሕዝብ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል አልተከሰተም።

የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪቃ ላይ የሚከተለው የልማት ፖሊሲ ጊዜውን ተከትሎ ተገቢው መሻሻል አልተደረገበትም ማለት ነው። ታዲያ በአፍሪቃ ልማት ላይ ከቻይና ሽርክና የሚለው የሉዊ ሚሼል የወቅቱ ዕቅድ አውሮፓ በአፍሪቃ ያላትን ጥቅም ይበልጥ እንዳታጣ ለመግታት የተወጠነ ነው የሚመስለው። በተለይ የነዳጅ ዘይት ዋጋ እጅግ እየናረ በሚገኝበት በአሁኑ ጊዜ የአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብት ይበልጥ የዓይን ማረፊያ እየሆነ መሄዱ አይታበልም። ይሁንና ቃል-አቀባዩ ጆን ክላንሢይ የአውሮፓው ሕብረት ዓላማ ይህ አይደለም ባይ ናቸው። “ይህ ትክክለኛው አመለካከት አይደለም። ጥረቱ የተመሠረተው ሁሉም ወገኖች ለሶሥት ወገኑ ሽርክና ሊያበረክቱ በሚችሉት የጋራ ድርሻ ላይ ነው። ይህን በአንድ ላይ ማምጣቱ ነው ዓላማው። እና ነገሩን ጎጂ በሆነ መልክ ማየቱ ተገቢ አይመስለኝም። ገንቢ ሆኖ መታየት አለበት”

ሉዊ ሚሼል እርግጥ ሽርክናው በአፍሪቃውያን ጀርባ እንዳይሰፍን ውይይቱ የሶሥት ወገን ሆኖ እንዲካሄድ የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ግን ሽርክናው ምን መልክ እንደሚኖረውም ሆነ ምን ጉዳዮችን እንደሚጠቀልል ፍንጭ አልሰጡም። ጥያቄው የአፍሪቃ ልማት ሆኖ ሳለ ሕብረቱ ከአፍሪቃ ጋር ቀጥተኛ የሁለት ወገን ንግግርን አለመሻቱስ ለምን? ይህም አንድ ራሱን የቻለ አጠያያቂ ጉዳይ ነው። ለማንኛውም ሕብረቱና ቻይና የአፍሪቃን ልማት በተመለከተ እርስበርስ የሚጻረር አቋም ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል። ቻይና ወደ አፍሪቃ ባደረችውና በምታደርገው ግፊት ለበጎ አስተዳደር መስፈን ደንታ የላትም፤ ጥቅሟን ብቻ ነው የምትመለከተው በሚል በአውሮፓውያኑ መንግሥታት ስትወቀስ ነው የቆየችው።
ታዲያ ልዩነቱን ማቀራረብ ይቻላል? ቤይጂንግ ከናካቴው ሽርክናውን ትቀበለዋለች ብሎ መጠበቅስ ይቻላል ወይ? ጆን ክላንሢይ እንደሚሉት የአውሮፓውያኑ አቋም ወደፊትም አይለወጥም። “የኮሚሢዮኑና የሕብረቱ ፖሊሲ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊትም አይቀየርም። ግን ይህ ማለት የጋራ ጥቅምን በተመለከተ አንወያይም፤ አንነጋገርም ማለት አይደለም። በግልጽ ለመናገር በአውሮፓ ሕብረት፣ በቻይናና በአፍሪቃ መካከል ለሚሰፍን ሽርክና ዋናው ጉዳይ አብሮ በመሥራት ሁላችንም ተጠቃሚ መሆናችንና ወደ ጋራ ግብ ማምራት መቻላችን ነው። በተለይም ለአፍሪቃ ጥቅም! ቻይናም ጉዳዩን እንደኛ መመልከቷ ነው አስደሳቹ ነገር። አፍሪቃ የሽርክናው ተጠቃሚ መሆን አለባት፤ ከተፈለገ አመራሩን መያዝ ትችላለች። እኛ በበኩላችን ለመተባበር ዝግጁ ነን። ግን እንደገና ልናገር፤ አፍሪቃ ናት ግንባር ቀደም ሚና ሊኖራት የሚገባው”

ጥያቄው የአውሮፓው ሕብረት አፍሪቃውያን መንግሥታትን ሊማርክ የሚችል ምን አዲስ ጽንሰ-ሃሣብ ይዞ ይቀርባል ነው። የአፍሪቃ መንግሥታት በልማት ዕርዳታም ሀነ በንግድ ረገድ የሚያቀርቡት ቅድመ-ግዴታዎች የማይዋጡላቸው እየሆኑ እንደሄዱ ታይቷል። የቅርቡ የሊዝበኑ የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባዔ ይህን መሰሉ ሁኔታ ጎልቶ ከታየባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ነበር። የቻይና ተጽዕኖ በአፍሪቃ መስፋፋት እንግዲህ የሚዛን ለውጥ ማድረጉ አልቀረም። ይሁን እንጂ የሕብረቱ ኮሚሢዮን በሌላ በኩል የወደፊቱን ሂደት ያን ያህል ከባድ አድርጎ አይመለከተውም። ጆን ክላንሢይ ሲያስረዱ፤

“የሊዝበኑ የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባዔ በበኩሌ ስኬታማ ነበር ብዬ አስባለሁ። እርግጥ በአንዳንድ ዘርፎች ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን እኛ ሁሉንም ነገር ከራሳችን አስተሳሰብ አንጻር ብቻ እንደምንመለከት ሆኖ መታየት የለበትም። የሊዝበኑ ጉባዔ መካሄዱ ራሱ ለወደፊቱ ትብብር መልካም ጥርጊያን የከፈተ ጉዳይ ነው። እና አንዳንዴ ችግር ማጋጠሙ ባይቀርም በሰከነ መንገድ መነጋገሩ ትክክለኛው መንገድ ይመስለኛል። መፍትሄው ይህ ብቻ ነው። እንዲህ ከሆነ ለሁሉም የሚጠቅም ዕርምጃ ለማድረግ ይቻላል”

የሊዝበኑ ጉባዔ ከተነሣ አይቀር በዚሁ ጉባዔ አኳያ የተሰበሰቡ የአፍሪቃና የአውሮፓ የሲቪክ ሕብረተሰብ ተወካዮች በአንጻሩ ውጤቱን አፍሪቃን የከዳ ሲሉ ነበር የነቀፉት። እነዚሁ ባወጡት የጋራ መግለጫ ጉባዔው አዲስ ሽርክና ለማስፈን በያዘው አቅጣጫ ብርቱ ስጋት ያደረባቸው መሆኑንም ገልጸዋል። የጉባዔው ውጤት በወቅቱ በአፍሪቃ ላይ ተደቅነው የሚገኙትን ችግሮች ከመፍታት የራቀ ነው፤ ለወደፊቱ ትውልድ የኤኮኖሚ ዕድገት ዕድል ዋጋ አልሰጠም ብለውትም ነበር። የቀድሞዎቹ ቅኝ ገዥ መንግሥታት አፍሪቃን ከወደቀችበት አዘቅት የማውጣት የራሳቸውም ድርሻ አለባቸው። የነዚሁኑ መንግሥታት ልማት የሚያፋጥን ፍትሃዊ ንግድ እንዲሰፍን ማድረጉ አንዱ ነው። በአንጻሩ በእኩልነት ላይ ባልተመሠረተ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ታዳጊዎቹ አገሮች ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ ለማድረግ የተያዘው ግፊት በረጅም ጊዜ ትስስሩን የሚያዳብር ሊሆን አይችልም።

ወደ ሣይኖ-አውሮፓው የትብብር ዕቅድ እንመለስና ለመሆኑ አፍሪቃ ውስጥ በሰፊው የተቆናጠጠችው ቻይና ከኮሚሢዮኑ ጋር ሊሰፍን በሚችል ሽርክና ልታገኝ የምትችለው ምን የተለየ ጥቅም አለ? ይህ ታዛቢዎች በሰፊው የሚሰነዝሩት ጥያቄ ነው። ሉዊ ሚሼል በበኩላቸው የተማረው አፍሪቃዊ በክፍለ-ዓለሚቱ እያደገ የሚሄደው የቻይና ተጽዕኖ አሳስቦታል፤ ይህም ተቃውሞን መቀስቀሱ አይቀርም ባይ ናቸው። ሚሼል እንዲያውም የአፍሪቃና የቻይና የሰመረ ግንኙነት ወደ መጨረሻው እየተጠጋ ነው እስከማለት ነው የደረሱት። እርግጥ የቻይና የአፍሪቃ ፖሊሲ በተግባር የሚያስከፋ ነገር ባይታጣበትም ሣይኖ-አፍሪቃው ትስስር ዘላቂ ከማይሆንበት ደረጃ መድረሱን ማየቱ በወቅቱ ሲበዛ የሚያዳግት ነው። ቀሪውን ከፊታችን ወር የሚሼል የቤይጂንግ ጉብኝት በኋላ ጠብቆ መታዘቡ ይመረጣል።