አውሮፓና ጀርመን በ2015 | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 29.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

አውሮፓና ጀርመን በ2015

ከነገ ወዲያ እኩለ ለሊት የሚሰናበተው ጎርጎሮሳዊው 2015 ፣በቅርብ ጊዜ የአውሮፓ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ ክስተቶች የተሰተናገዱበት ዓመት ነበር ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:10

አውሮፓና ጀርመን በ2015

አመቱ በተለይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያልታየ በተባለ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ክፍለ ዓለሙ የተጥለቀለቀበት፣ የስደተኞችም ጉዳይ አውሮፓውያንን ሲያስጨንቅ ሲያከራክርና ሲያጨቃጭቅ የከረመበት ነበር ። በዓመቱ ፓሪስ የደረሱት የሽብር ጥቃቶች ክፍለ ዓለሙን ድንጋጤ ቁጭትና ስጋት ውስጥ ከተው አውሮፓውያን የፀጥታ አጠባበቃቸውን እንዲፈትሹ አድርገዋል ።በ2015 ፣28ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በግሪክ ብድርና እዳ ሲወዛገቡ ከርመዋል፤ የግሪክ የፖለቲካ አካሄድና አስደማሚዎቹ የምርጫና የህዝበ ውሳኔ ውጤቶች ከአመቱ መባቻ አንስቶ እስከ አጋማሹ ድረስ የአውሮፓውያን አብይ መነጋገሪያዎች ነበሩ ። በበጀርመን ራሱን «የምዕራብ ፀረ-እስልምና የአውሮፓ አርበኞች» በጀርመንኛው ምህፃሩ ፔጊዳ ብሎ የሚጠራው ቡድን የተቃውሞ ሰልፍና ና ፀረ ፔጊዳ ተቃውሞ ተጠናክሮ የቀጠለበት ዓመትም ነበር ።
2015 አንድ ሲል 2.9 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሰሜን አውሮፓዊቷ ትንሽትዋ ሃገር ሊትዌንያ 19 ነኛዋ የዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገር ሆነች ። በሊትዌንያ የዩሮ ተጠቃሚነት የተጀመረው 2015 ሲብት በጀርመን ራሱን «የምዕራብ ፀረ-እስልምና የአውሮፓ አርበኞች» በጀርመንኛው ምህፃሩ ፔጊዳ ብሎ የሚጠራው ቡድን ፣በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 2014 በምሥራቅ ጀርመንዋ በድሬስደን ከተማ የጀመረውን ፀረ/እስልምናና የውጭ ዜጎች ተቃውሞ አጠናክሮ ቀጠለ ። ጥር መጀመሪያ ላይ 20ሺህ የሚደርሱ ሰዎች የተገኙበትን የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄደው ፔጊዳ በየሳምንቱ ሰኞ ከድሬስደን አልፎ በተለያዩ ከተሞችም ተቃውሞውን ማሰማቱን ቀጥሎ ነው የከረመው ።አውሮፓ በሙስሊሞች መወረሩ ይቁም ፣ የውጭ ዜጎች ከጀርመን ይውጡ ጀርመን ለጀርመናውያን ብቻ የሚል አቋም ያለውን የቡድኑን እንቅስቃሴ የሚቃወሙ ሰልፎችም በዓሙቱ ንቅናቄው

በተጀመረበት በድሬስደንና በሌሎችም የጀርመን ትላላቅ ከተሞች ተካሂደዋል ። በዚሁ በጥር ወር ንቅናቄው ከተለያዩ አቅጣጫዎች በደረሰበት ውግዘት ከመስራቾች የተወሰኑት ራሳቸውን ከቡድኑ ቢያገሉም በ2015 በርካታ ስደተኞች ወደ
በ2015 በመጀመሪያው ወር በሰባተኛው ቀን የፈረንሳይን ውብ ከተማ ፓሪስን ያናወጠ የሽብር ጥቃት ደረሰ ። ታጣቂዎች አወዛጋቢ ምፀታዊ ምስሎችን የሚያወጣውን የሻርሊ ኤብዶ ጋዜጣ የፓሪስ ቢሮ ሰብረው የጋዜጣውን ሠራተኞችና ፖሊሶችን በአጠቃላይ 12 ሰዎችን ገደሉ ። ይህ የሽብር ጥቃት አስደንግጦና አስቆጥቶ ሳያበቃ በማግስቱ እዚያው ፓሪስ ሌላ ታጣቂ ፖሊስ ገደለ ። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ አንድ ተጠርጣሪ 15 ሰዎችን ባገደበት በይሁዲዎች የሸቀጣሸቀጥ መደብር የራሱን ጨምሮ የ5 ሰዎች ህይወት ጠፋ ። ጥቃቱ በደረሰ በ4 ተኛው ቀን የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ኬምረንን ጨምሮ ከ40 በላይ የመንግሥታት መሪዎች ና ቁጥሩ ከ 1 ሚሊዮን በላይ የተገመተ ህዝብ የተካፈለበት ሰልፍ ተካሂዷል ።ሰልፉ በጥቃቱ የተገደሉት 17 ሰዎች የታሰቡበት ብቻ ሳይሆን ሃሳብን በነፃ የመግለጽ ነፃነት ላይ የተቃጣውን ጥቃት ያወገዘ ጭምር ነበር ። ጥቃቱ የአውሮፓ መንግሥታት የፀጥታ አጠባበቃቸውን እንዲፈትሹ መረጃዎችንም ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ በመለዋወጥ ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል ። ጥበቃና

ቁጥጥሩ ቢጠናከርም ፓሪስን ከሁለተኛ የሽብር ጥቃት ግን አላዳነም ። ህዳር 13 2015 በፓሪስ በሙዚቃ ትርኢት አዳራሽ ፣በስታድዮም እና በበቡና ቤቶች በተጣለ የተቀነባባረ የሽብር ጥቃት የ113 ሰዎች ህይወት አለፏል ። ከ350 በላይም ቆስለዋሉ ።ጥቃቱ በአሸባሪዎች መፈፀሙን ያስታወቁት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ደነገጉ ።ጥቃቱን በጣለው ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራውIS በተባለው ቡድን ላይ ፈረንሳይ በሶሪያ የአየር ድብደባ ዘመቻ ከፈተች ።
ጥር ሊገባደድ ሲል የተካሄደው የግሪክ ምርጫ በግሪክና በአውሮፓ ታሪክ ልዩ ስፍራ የተሰጠው ውጤት አስገኝቷል ። በዚህ ምርጫ ግሪክ በአበዳሪዎች የተጫነባትን የቁጠባ እርምጃዎች የሚቃወመው ግራ ዘመሙ የግሪክ ሲሪዛ ፓርቲ ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱ ብቻ ሳይሆን የቁጠባ እርምጃዎችን ከማይቀበለው ቀኝ ፅንፈኛ ከሚባለው የነፃ ግሪኮች ብሔረተኛ ፓርቲ በምህፃሩ ANEL ጋር ተጣማሪ መንግሥት መመሥረቱ አስደምሟል ። በግሪክ የ150 ዓመት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ወጣት መሪ የተባሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፕራስ ከፓርቲያቸው ድል በኋላ ሃገራቸውና ህዝቧ ከአበዳሪዎች ጫና የሚላቀቁበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ብለው ነበር ።
« የሉዓላዊት ሃገር የግሪክ ህዝብ ዛሬ ግልፅ ጠንካራና የማያከራክር ስልጣኑን ሰጥቷል።ግሪክ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተች ነው ። ግሪክ ከተመሰቃቀለው አሰጨናቂ የቁጠባ እርምጃ ፣ከፍርሃትና ከተመረጡ ሃብታሞች አስተዳደር እንዲሁም ካለፉት 5 ዓመታት መሸማቀቅና ህመም እየተገላገለች ነው ።»
ሆኖም አዲሱ የግሪክ መንግሥት ሃገሪቱ አለ አግባብ ተጭነውባታል የሚላቸውን ግዴታዎች አስቀራለሁ ሲል ለመራጩ ህዝብ የገባውን ቃል ለመፈፀም ከአበዳሪዎች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ድርድሮች ቢያካሂድም አልተሳካለትም ። የግሪክ አበዳሪዎች ግሪክ የኤኮኖሚ ተሃድሶ እርምጃዎችን ለመውሰድ በማቅማማትዋ ሃገሪቱን ከገንዘብ ቀውስ ለመታደግ ከታቀደው ብድር የመጨረሻውን 7.2 ቢሊዮን ዩሮ ለመልቀቅ አለመስማማታቸው ያስከተለው ፍጥጫ ግሪክን ከዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገራት ማህበር እስከ መውጣት ሊያደርሳት ይችላል የሚል ስጋትም አስከትሎ ነበር ። አበዳሪዎችን ማሳመን ያቀተው የግሪክ መንግሥት በቁጠባ መርሃ ግብሩ ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ አደረገ ። ህዝቡም ዓለም ዓቀፍ አበዳሪዎች ያስቀመጧቸውን የቁጠባ እርምጃዎች ሳይቀበል ቀረ ። ከህዝበ ውሳኔው በኋላ የግሪክ የገንዘብ ሚኒስትር ያኒስ ቫሩፋኪስ ሥልጣናቸውን ለቀቁ ።ውጣ ውረዱ የሃገሪቱን ባንኮች አዘግቶ የገንዘብ ዝውውርንም ገደበ ። ግሪክ ብድሩ ሳይለቀቅላት ለዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት IMF ዕዳዋን የመክፈያዋ ቀነ ገደብ የጎርጎሮሳዊው ሐምሌ አንድ አለፈ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ጨምሮ የዩሮ ተጠቃሚ ሃገራት መሪዎች ግሪክ የተጣሉባትን መርሃ ግብሮች እንድትቀበል ጫና ካደረጉ በኋላ የግሪክ ፓርላማ

በተሃድሶ እርምጃዎች ተስማምቶ ህብረቱ ነሐሴ አጋማሽ ላይ ለግሪክ በአስቸኳይ ሊደርስ የሚችል የ7.6 ቢሊዮን ዩሮ ብድር ፈቀደ ። ብድሩ ከተፈቀደ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲፕራስ ከሥልጣን ወርደው አዲስ ምርጫ ተጠራ ። በመስከረም በተካሄደው በዚህ ምርጫ ሲፕራስ አሸንፈው የሥልጣን መንበሩን ዳግም ያዙ ። በርሊን ነዋሪ የሆኑት የኤኮኖሚ እድገት መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የኤኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ዶክተር ፈቃዱ በቀለ ያኔ እንደተናገሩት እንደተፈራው ግሪክ ከማህበሩ ብትወጣ ከባድ ችግር ውስጥ ልትወድቅ ትችል ነበር። ችግሩም በግሪክ ብቻ የሚወሰን አይሆንም ነበር ።
በጎርጎሮሳዊው 2015 በአውሮፓ አብዩ ክስተት በርካታ ስደተኞች በቱርክ አቆራርጠው በግሪክ ደሴቶች አድርገው በባልካን ሃገራት በኩል ነው ወደ ሰሜን አውሮጳ መጉረፋቸው ነው ። በ2015 ወደ አውሮጳ የሚጎርፈው ስደተኛ ቁጥር እጅግ እየጨመረ መሄድ የጀመረው በሚያዚያ ወር ነበር ። ሶሪያውያን የሚያመዝኑባቸው ስደተኞች ከግሪክ ወደ መቄዶንያ ከዚያም ወደ ሰርቢያ በመሻገር በሃንጋሪ አድርገው ወደ ሰሜን አውሮፓ ሃገራት መግባት ጀመሩ ።በዚሁ ወር ከሊቢያ የባህር ጠረፍ የተነሱ ቁጥራቸው ወደ 800 ሳይሆኑ እንዳልቀረ የተገመተ ስደተኞች የውሐ ሲሳይ ሳይሆኑ እንዳልቀረ ሲሰማ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች በሜዲቴራንያን ባህር ላይ ለሚካሄደው የድንበር ቁጥጥር የሚሰጠውን እርድታ በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ቃል ገቡ ። ሰዎችን በሚያሸጋግሩ ደላሎች ላይ ያነጣጠረ ወታደራዊ ተልዕኮም ጀመሩ ።በዚሁ ጊዜ በስደተኞች ከተጨናነቁት ከግሪክና ኢጣልያ 40 ሺህ ስደተኞችን ለመከፋፈልና ከህብረቱ አባል ሃገራት ውጭ የሚገኙ 20 ሺህ ስደተኞችንም ለመውሰድ ተስማሙ ።በሐምሌ በአየር እጦት ሳይሞቱ እንዳልቀረ የተገመቱ የ71 ስደተኞች አስከሬን ኦስትሪያ በአንድ መኪና ውስጥ ተገኘ ። መስከረም ላይ እጅግ እየጨመረ በሄደው ስደተኛ የተማረረችው ሃንጋሪ የአውሮፓን የክርስትና እሴቶች ለማስጠበቅ ሙስሊም ስደተኞችን ማስገባት እንደማትፈልግ ተናግራ ከሰርቢያ ጋር የሚያዋስናትን 177 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ድንበር አጠረች ። የሃንጋሪ ድንበር ሲዘጋ ስደተኛው አቅጣጫውን ወደ ክሮኤሽያ ቀየረ ።በነዚህ መንገዶች አውሮፓ የገቡትን ስደተኞች 160ሺሁኑ የመከፋፈሉ ጥያቄ ከቀረበላቸው የአውሮፓ ህብረት ህብረት አባል ሃገራት የምሥራቅ አውሮጳዎቹ ሃንጋሪ ፣ቼክ

ሪፐብሊክ ፣ ስሎቫክያ ፣ፖላንድ ና ሮማንያ አዎንታዊ ምላሽ አልሰጡም ። ችግሩ አፋጣኝ የጋራ መፍትሄ እንደሚያሻው ብዙ በርካታ ስደተኞችን ያስገባችው ጀርመን ስታሳስብ ነበር ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አግባቢ መፍትሄ ላይ ለመድረስ የተቻለው ሁሉጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ጠይቀው ነበር ። ።
« እንደ አውሮፓውያን በጋራ የመቆም የሞራል ግዴታችንን መወጣት አለብን ።ይህ ማለት 28ቱም የአውሮፓ ህብረት አባል መንግሥታት ስደተኞችን ማስተናገድን በመሰሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ በአብላጫ ድምፅና ፣አንዱ ከሌላው ይበልጣል በሚል አስተሳሰብ ከመወሰን ይልቅ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መጣርና ሃላፊነትን እኩል መሸከም ይኖርብናል ። »
በዚሁ በመስከረም ወር ቼክ ሪፐብሊክ ሃንጋሪ ሮማንያና ስሎቫክያ በድምፅ ብልጫ ተረተው ህብረቱ ከግሪክ ከኢጣልያና ከሌሎች ስደተኞች በብዛት ከሚገቡባቸው የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት 160 ሺህ ስደተኞች ለመከፋፈል ተስማምቷል ።ህብረቱ ከዚህ ሌላ በህዳር ወር ከአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች ጋር በተካሄደ ጉባኤ አፍሪቃውያን ወደ አውሮፓ እንዳይሰደዱ ለመግታት የሚውል 1.9 ቢሊዮን ዩሮ መደቧል ።ከመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት በቱርክ በኩል የሚካሄድ ስደትን ለማስቆምም ከቱርክ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል ። ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልም ፍሮንቴክስ የተባለውን የህብረቱን የድንበር ጠባቂ ድርጅት፣የተጠናከረ አቅም ይኖረዋል በተባለው የአውሮፓ የድንበርና ጠረፍ ጠባቂ ድርጅት ለመቀየር የታቀደው ከአንድ ሳምንት በፊት ነው ።
ከአውሮፓ የትልቁ የመኪና አምራች ኩባንያ የፎልክስክ ቫገን የማጭበርበር ቅሌት የተጋለጠው በመስከረም 2015 ዓም ነበር ። ኩባንያው 11 ሚሊዮን ለሚደርሱ በናፍጣ ለሚሰሩት መኪናዎቹ የብክለት ምርመራን ማለፍ የሚያስችል የተጭበረበረ ሶፍትዌር በመግጠም ተከሶ ጥፋቱን አምኗል ። ኩባንያው በዚህ ቅሌት እስከ 18 ሚሊዮን ዶላር ሊቀጣ ይችላል ።
ጀርመን ጥብቅ የተባለ አዲስ የተገን አሰጣጥ ያወጣችውም በተገባደደው በ2015 ነበር ። ወደ ጀርመን የሚገባው ስደተኛ ቁጥር ከተጠበቀው በላይ እየጨመረ ከሄደ በኋላ ባለፈውጥቅምት ከወጣው ከዚህ ህግ ዓላማዎች ውስጥ የተገን አሰጣጥ ሂደትን ማፋጠንና ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን በአስቸኳይ ወደ ሃገራቸው ማባረር በዋነኛነት ይጠቀሳሉ ።
ይህ ህግ በወጣ በሁለተኛው ቀን ለምዕራብ ጀርመንዋ ለኮሎኝ ከተማ ከንቲባነት የምርጫ ዘመቻ በማድረግ ላይ የነበሩት እጩ ተወዳዳሪ ሄነሪተ ሬከር ስደተኞች ጀርመን መግባታቸውን በሚቃወም ግለሰብ አንገታቸው ላይ በስለት ተወጉ ። በማግሥቱ በተካሄደ ምርጫ አሸንፉ ። ለቀናት ራሳቸውን ስተው የቆዩት ሬከር ድነው በተመረጡበት ሃላፊነት ላይ ይገኛሉ ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic