አውሮፓና ጀርመን በ2012 | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 18.12.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

አውሮፓና ጀርመን በ2012

የአባል ሃገራት መሪዎች የ2012 የመጨረሻ ጉባኤያቸውን ባለፈው ሳምንት ካካሄዱ በኋላ ይፋ እንደሆነው የዩሮ ቀውስና መዘዙ ገና አላበቃም ። የተወሰዱት የማስተካከያ እርምጃዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት አያመጡም ። በ2013 በደቡባዊ አውሮፓ ሃገሮች የኤኮኖሚ እድገት ዝግመት ሥራ አጥነትንና ድህነትን ያባብሳል የሚል ፍራቻ አለ ።

ከ2 ሳምንት በኋላ አምና ብለን በምንጠራው በጎርጎሮሳውያኑ 2012 አም በአውሮፓ አብዩ ጉዳይ አንደቀደሙት 2 አመታት ሁሉ ዩሮ ለገጠመው ፈተና መፍትሄ ማፈላለግ ነበር ። የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በ 2012 ባካሄዷቸው 6 ጉባኤዎች ዋነኛ መነጋገሪያቸው ግሪክ ነበረች ። የእዳ ክምችት እንዲሁም የበጀት ጉድለት ኤኮኖሚዋን ያቃወሰውን ግሪክን ለመታደግ መወስድ የሚገባቸው እርምጃዎች አመቱን ሙሉ ሲያነገጋግሩና ሲያከርክሩ ነው የከረሙት ። በ2012 አጋማሽ ግድም ደግሞ ህብረቱ ግሪክን ከዩሮ ማህበር ሊያስወጣ ነው የሚሉ ወሬዎችም እስከመሰማት ደርሰው ነበር ። ህብረቱ ግን ግሪክን ከጋራው ሸርፍ ዩሮ ተጠቃሚነት የማስወጣት ሃሳብ እንደሌለው ነው የዩሮ ቀጣና አባል ሃገራት ማህበር ፕሬዝዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር በወቅቱ ያሳወቁት ። የግሪክ ብቻ ሳይሆን ህብረቱ የታደጋቸው የስፓኝ ና የኢጣልያ እንዲሁም የነርሱ እጣ ይገጥማቸዋል ተብለው የሚያሰጉ የሌሎች የዩሮ ተጠቃም ሃገሮች ይዞታም በአመቱ አሳሳቢነቱ እንደጎላ ነው የዘለቀው ። በተለይ ሙዲስ የተባለው የሃገሮችን የመበደር አቅም ደረጃ የሚያወጣው ዓለም አቀፍ ድርጅት በ2012 እንደ ፈረንሳይ የመሳሰሉ የትላልቅ ኤኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሃገሮችን የመበደር አቅም ዝቅ ማደረጉ በእጅጉ አስግቷል ። የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆሴ ማኑዌል ባሮሶ 2012ን እንደገመገሙት በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላለው አውሮፓዊ አመቱ ችግር የተሞላበት አመት ነበር ።


«ይህ ዓመት በተለይ በማኅበረሰባችን ለችግር ተጋላጭ ለሆነዉ ወገን በጣም ከባድ ነበር። ሆኖም ግን የችግሩን ሥረ መሠረት እየፈታን ነዉ። የመንግስት ፋይናንስ እየተሻሻለ ነዉ፤ የመወዳደር አቅማቸዉ ዝቅተኛ የሆነ ተፎካካሪዎች ይዞታ እየተሻሻለ ነዉ ፤ የፋይናንስ ዘርፉ ተስተካክሏል ። »
ያም ሆኖ የአባል ሃገራት መሪዎች የ2012 የመጨረሻ ጉባኤያቸውን ባለፈው ሳምንት ካካሄዱ በኋላ ይፋ እንደሆነው የዩሮ ቀውስና መዘዙ ገና አላበቃም ። የተወሰዱት የማስተካከያ እርምጃዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት አያመጡም ። መሪዎቹ የአመቱ መዝጊያ በሆነው 6ተኛ ጉባኤያቸው ለቀውሱ ማስተካከያ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ የዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገራት ባንኮች የበላይ ተቆጣጣሪ ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም ለግሪክ 50 ቢሊዮን ዩሮ አዲስ እርዳታ ለመልቀቅ ተስማምተዋል ። መሪዎቹ የተስማሙባቸው ጉዳዮች የተረጋጋ የኤኮኖሚና የገንዘብ ህብረት ለመፍጠር ወሳኝ እርምጃዎች መሆናቸው ተነግሯል ።

ይሁንና በ2013 በተለይ በደቡባዊ አውሮፓ ሃገሮች ያጋጥማል ተብሎ የሚያሰጋው የኤኮኖሚ እድገት ዝግመት ሥራ አጥነትንና ድህነትን ያባብሳል የሚል ፍራቻ አለ ። በ2012 የአውሮፓ ህብረት አብይ ትኩረት ከነበረው የዩሮ ቀውስ ወደ ሌሎች የአውሮፓ አበይት ክንውኖች ስንሸጋገር በፈረንሳይ በኢጣሊያና በግሪክ የተካሄዱትን የመንግሥት ለውጦች እናገኛለን ። ፈረንሳይ በ2012 አዲስ ሶሻሊስት መሪ አግኝታለች ።
የፈረንሳይ ሶሻሊስት ፓርቲን ወክለው በምርጫው ለመወዳደር ያቀዱት የቀድሞው የአለም የገንዘብ ድርጅት ፕሬዝዳንት ዶምኒክ ስትራውስ ካን ኒውዮርክ አሜሪካን በወሲብ ቅሉት ተጠርጥረው ለምርመራ ከተያዙ በኋላ ከሃላፊነታቸው ሲወርዱ እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ የመቅረብ እቅዳቸውን በመሰረዛቸው ኦሎንድ ተተኩ ። በአጋጣሚው በእጩነት የቀረቡት ኦሎንድም ተፎካካሪያቸውን ኒኮላ ሳርኮዚን አሸነፉ
ኦሎንድ ፈረንሳይን በአሰከፊ የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት የመሩት ሳርኮዚና ሌሎችም የአውሮፓ መሪዎች የሚደጋግሙትን ቁጠባና የበጀት ቁጥጥርን ፣ እድገት በሚለው አዲስ መርህ እንደሚለውጡ ቃል መግባታቸው ለድላቸው ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል ። በኢጣልያም እንዲሁ የመንግሥት ለውጥ ተደርጓል ። አወዛጋቢው የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ በምጣኔ ሃብት ምሁሩና በጠንካራ ተደራዳሪው ማርዮ ሞንቲ የተተኩት በገባደድነው በ2012 ነው ።


የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑት የ 68 አመቱ ሞንቲ የመሰረቱት የሽግግር መንግሥት የሚቆየውም ምርጫ እስከሚካሄደበት እስከ 2013 መጀመሪያ ነው ። አመቱን በሙሉ የመላውን አለም ትኩረት ባልተለያት በግሪክም እንዲሁ በአመቱ አጋማሽ በተካሄደ ምርጫ አሸናፊው አዲሱ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ከሶሻል ዲሞክራቶችና ከግራ ዲሞክራቶች ፓርቲ ጋር ተጣማሪ መንግሥት መስርቷል ። በግሪክ የተካሄደው ምርጫና ውጤት ግን አበዳሪ መንግሥታትና አለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት በጣላቸው አስገዳጅ የቁጠባ እርምጃዎች ላይ ከህዝቡ በኩል ሲቀርብ የቆየው ተቀውሞ አባሰው እንጂ አላስቆመውም ። በ2012 በግሪክ ኃይል የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎችና የስራ ማቆም አድማዎች ተጠናክረው ሲካሄዱ ነው የከረሙት ። በተገባደደው በ2012 ግሪክን ጨምሮ በበርካታ የአውሮፓ ሃገራት የሚገኙ የሠራተኛ ማህበራት በአንድ ቀን ተቃውሞአቸውን በህብረት አስምተውም ነበር ። ወደ ጀርመን ስናተኩር ደግሞ 2012 ባልታሰበ አጋጣሚ ጀርመን አዲስ ፕሬዝዳንት ያገኘችበት አመት ነበር ። ከግለሰብ በአነስተኛ ወለድ በተበደሩት ገንዘብ ሰበብ ከ2011 አንስቶ ለ 2 ወራት ሲብጠለጠሉ የከረሙት 10ኛው የጀርመን ፕሬዝዳንት ክርስቲያን ቩልፍ ግፊቱ በርትቶባቸው በየካቲት 2012 ሥልጣን ለመልቀቅ ተገደዱ ።


ለ 5 ዓመት የሥልጣን ዘመን ቃለ መሃላ ፈፅመው 2 አመት እንኳን ሳይደፍኑ ከሥልጣን የተሰናበቱት ቩልፍ መጋቢት 2012 በሰብአዊ መብት ተሟጋቹ በዮአሂም ጋውክ
ተተኩ ። በቀደመው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከቩልፍ ጋር ተወዳድረው ለጥቂት የተሸነፉት ጋውክ ባልጠበቁበት ሁኔታ ለዚህ ሥልጣን በመብቃታቸው መደነቃቸውን በወቅቱ ተናግረው ነበር ።
ጀርመን ሳይታሰብ አዲስ ፕሬዝዳንት ባገኘችበት በ2012 ፣ ከጀርመን በህዝብ ብዛት ከፍተኛውን ቁጥር በሚይዘው በምዕራባዊው በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር በተካሄደ ምርጫ የተገኘው ውጤት ለተጣማሪው የጀርመን ገዥ ፓርቲ ክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት በጀርመንኛው ምህፃር CDU አስደንጋጭ ነበር ። ግዛቲቱን ተጣምረው የሚገዙት የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲና አረንጓዴዎቹ ፣ CDUን በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል ። ፓርቲያቸው CDU ከ 2 አመት በፊት ካገኘው ውጤት በሩብ መቀነሱን ያስተዋሉት ሜርክል በግዛቱ ሽንፈቱን መራርና የሚያሳምም ነው ያሉት ። CDU በግዛቲቱ በገጠመው ሽንፈት ሰበብ ፓርቲውን ወክለው የተወዳደሩት የፌደራል ጀርመን መንግሥት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ኖርበርት ሮትገን ከክፍለ ሃገሩ የፓርቲ መሪነት ለመልቀቅ ተገደዋል ። ። የCDU ው ሮትገን ብዙም ሳይቆዩ ከአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትርነትም ተሽረዋል ።

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አመቱን በድል እያገባደዱ ነው ። ፓርቲያቸውን CDU ን ወክለው በሚቀጥለው አመት ለሚካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ የሚፎካከሪት ሜርክል ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነትና ጠንካራ ኤኮኖሚ ይዘው ነው የሚጓዙት ። ምንም እንኳን የ 58 አመቷ ሜርክል ጥብቅ የቁጠባ እርምጃ በተጣለበት በግሪክና በስፖኝ ህዝብ ዘንድ ቢጠሉም ለጀርመናውያን መድህን በመሆናቸው ይመሰገናሉ ።

ተቃዋሚው SPD በ 2013 የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ፓርቲውን ወክለው የሚወዳደሩ እጩ በይፋ የሰየመው ባለፈው ወር ነበር ። SPD የሰየማቸው እጩ ተወዳዳሪ የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትር ፔር ሽትያንብሩክ ከ2009 አም አንስቶ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ለሰጡት ገለፃና ላደረጉት ንግግር 1.25 ሚሊዮን ለመቀበላቸው ይቅርታ ለመጠየቅ መገደዳቸው ከወዲሁ የሜርክልን የማሸነፍ እጣ ያሰፋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ። ያም ሆነ ይህ የምርጫውን ውጤት ከወዲሁ ለመገመት አስቸጋሪ ነው የሚሉት ይበዛሉ ። በአመቱ የምዕራን ጀርመንዋ የኮሎኝ ከተማ ፍርድ ቤት የወንዶች ልጆችን ግርዘት ህገ ወጥና በአካል ላይ ጉዳት ማድረስ ሲል መቃወሙ ከአወዛጋቢ ጉዳዮች አንዱ ሆኖ ነው የከረመው ። የአይሁድ የሙስሊምና የክርስትና እምነት ተከታዮችን ያስቆጣውን ውሳኔ የጀርመን መንግሥትና የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድቅ አድርገውታል ። በአመቱ ውስጥ በጀርመን የስደተኞች መብት ተሟጋቾችንና ተገን ጠያቂዎችና ያስደሰተም ትእዛዝም ተላልፏል ። ጀርመን ለሚኖሩ ስደተኞች የሚሰጠውን ድጎማ ከፍ እንዲደርግ የተላለፈው ትዕዛዝ ። 2012 በአውሮፓ ና በጀርመን ከሞላ ጎደል ይህን ይመስል ነበር ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic