አውሮጳ፣ የስደተኞች ፖሊስዋና በአፍሪቃ ላይ ያሳረፈችው ጫና | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 10.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

አውሮጳ፣ የስደተኞች ፖሊስዋና በአፍሪቃ ላይ ያሳረፈችው ጫና

የአውሮጳ ህብረት ከአፍሪቃ እና ከመካከለኛ ምሥራቅ ሀገራት ጋር ከቱርክ ጋር የተፈራረመውን ዓይነት ስምምነት ለመድረስ እቅድ እንዳለው ከትናንት በስቲያ አስታውቋል። ይህንኑ ፍላጎቱን አፍሪቃውያት ሀገራት ድንበራቸውን እንዲዘጉ እና ከአውሮጳ የሚመለሱ ስደተኞችንም እንዲቀበሉ ጫና በማሳረፍ እውን ለማድረግ አቅዶዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:29

የሕገ ወጥ ስደተኞች ጉዳይ

ከቱርክ ጋር የደረሰችውን ስምምነት እንደምሳሌ የምትጠቅሰው አውሮጳ በምትከተለው የስደተኞች ፖሊሲ ላይ የአፍሪቃውያኑን ትብብር በማፈላለግ ላይ ትገኛለች። ህብረቱ በዚህ ዓይነቱ ስምምነት እነዚሁ ሀገራት ስደተኞች በትውልድ አገራቸው አቅራቢያ እንዲቆዩ እና ሰዎች ስራ ፍለጋ ብለው ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ ጥረት እንዲያደርጉ ለመገፋፋት ነው ያሰበው።

በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ወደ አውሮጳ ለመምጣት የሚፈልጉ ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ ሊቢያ ውስጥ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ ያሳያል። በተገን አሰጣጥ ሂደት ላይ አሁንም ትልቅ ልዩነት የሚታይባቸው አባል ሀገራት ስደተኞችን ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኞች አለመሆናቸውን የአውሮጳ ህብረት በሚገባ ያውቃል። ህብረቱ እንዳመለከተው፣ አሁን በመሀሉ በአደገኛው የሜድትሬንያን ባህር በኩል እያደረጉ ወደ ኢጣልያ የሚመጡት ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን እና ከነዚህም ሁሉም ማለት ይቻላል አፍሪቃውያን ናቸው። በዚህም የተነሳ ኮሚሽኑ ከዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ ቱኒዝያ፣ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ኢትዮጵያ እና ሊቢያ ጋር ከቱርክ ጋር የደረሰውን ዓይነት የትብብር ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልግ ነው ያስታወቀው። ይሁንና፣ ከቱርክ ጋር የተደረሰውን ዓይነት ስምምነት ከአፍሪቃውያቱ እና ከመካከለኛ ምሥራቅ ሀገራት ጋር በመድረስ፣ ማለትም፣ ገንዘብ በመስጠት ስደተኞች ወደአውሮጳ እንዳይመጡ ለማከላከል መሞከሩ እንደማይሰራ በአውሮጳ ምክር ቤት የለዘብተኞቹ እንደራሴዎች መሪ ጊ ፈርሆፍስታድት በማስታወቅ፣ አማራጭ ያሉትን ሀሳብ እንዲህ አቅርበዋል።


« ብቸኛው መንገድ በነዚህ ሀገራት ውስጥ የመቀበያ ጣቢያዎችን መክፈት ይሆናል፣ እነዚሁ ጣቢያዎች በአውሮጳ ህብረት ኃላፊነት እና ከሚከፈቱባቸው ሀገራት ጋር በሚዘጋጅ የጋራ አስተዳደር ስር ይውላሉ። በነዚህ ጣቢያዎችም ውስጥ ስደተኛው በትክክል ስደተኛ ካልሆነ እንዴት ሊረዳ እንደሚችል፣ ስደተኛ ከሆነ ደግሞ እንዴት መልሰን ልናሰፍረው እንደምንችል ለመለየት እንችላለን። »
ዜጎቻቸው እንዳይሰደዱ ለማከላከል የድንበሮቻቸውን ቁጥጥር ለማጠናከር ፣ አውሮጳ የምትመልሳቸውን ሕገ ወጥ ስደተኞች መልሰው ለመቀበል እና የስደተኞች መቀበያ ጣቢያዎች የሚገነባበትን ርምጃ ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ ሀገራትን ህብረቱ በምላሹ እንዲደጉም፣ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ደግሞ እንዲቀጣ በአውሮጳ ምክር ቤት የለዘብተኞቹ እንደራሴዎች መሪ ጊ ፈርሆፍስታድት ሀሳብ አቅርበዋል።
« አዎንታዊ እና አሉታዊ ፣ ማለትም፣ የማበረታቻ እና የመቅጫ ርምጃዎችን የያዙ ሁለት ሀሳቦችን አቅርበናል። ከኛ ጋር በደንብ ለመስራት የሚፈልጉትን ሶስተኛ አገሮች በመደጎም ለማበረታታት፣ የማይተባበሩትን ደግሞ ርማጃቸው መዘዝ እንደሚያስከትልባቸው ግልጽ እናደርጋለን። ይህም በልማት እና በንግድ ፖሊሲዎቻችን በመጠቀም ጫና ማሳረፍን ያካትታል። »
በሌላ አነጋገር ከህብረቱ ጋር ለመተባባበር በማይፈልጉት አንፃር፣ የሚተባበሩት አገሮች እንደየሁኔታቸው ከህብረቱ ተጨማሪ የልማት ርዳታ ያገኛሉ፣ የተሻለ የንግድ ሁኔታም እንደሚመቻችላቸው ነው ህብረቱ የገለጸው።
የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ከቱርክ ጋር የተደረሰው ዓይነት ስምምነት ከአፍሪቃውያቱ እና ከመካከለኛ ምሥራቅ ሀገራት ጋር ለመድረስ ያቀረበውን ሀሳብ ወግ አጥባቂዎቹ ፓርቲዎች ሲያሞግሱ፣ ለዘብተኞቹ እና የግራ ክንፍ ፓርቲዎች ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ አያስገኝም በሚል ነቅፈውታል።

ባርባራ ቬዝል/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic