አውሮጳ እና ጀርመን በ2019 | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 31.12.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

አውሮጳ እና ጀርመን በ2019

በጎርጎሮሳዊው 2019፣የብሬግዚት ሂደትን ፣ በዓመቱ መገባደጃ የተካሄደውን የብሪታንያ ምርጫ ውጤት፣ የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ምርጫ እና ሹመትን፣ የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫንና፣ በጀርመን እና በአውሮጳ የተካሄዱ ወሳኝ ምርጫዎችን እንዲሁም ሌሎችም ክንውኖችን ወደ  ኋላ መለስ ብለን እንቃኛለን።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:01

አውሮጳ እና ጀርመን በ2019

 
ጎርጎሮሳዊውን 2019 ሸኝተን አዲሱን 2020ን ለመቀበል ጥቂት ሰዓታት ብቻ ቀርተዋል። የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅት ዛሬ በሚሸኘው በጎርጎሮሳዊው 2019 በአውሮጳ እና በጀርመን ዐበይት ክንውኖች ላይ ያተኩራል። ጎርጎሮሳዊው 2019 በአውሮጳ በአጠቃላይ እንዲሁም በጀርመን ልዩ ልዩ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዓመት ነበር። የብሬግዚት ሂደት እና በዓመቱ መገባደጃ የተካሄደው የብሪታንያ ምርጫ ውጤት የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ምርጫ እና ሹመት፣ የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ፣ በጀርመን እና በአውሮጳ የተካሄዱ ወሳኝ ምርጫዎች እና ሌሎችም የዓመቱ ዐበይት ክስተቶች የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅት ወደ  ኋላ መለስ ብሎ የሚያስቃኘን ጉዳዮች ናቸው።
በጎርጎሮሳዊው 2019 በአውሮጳ ትኩረት የተሰጣቸው ውይይቶች ክርክሮችና ውዝግቦች ከተካሄዱባቸው ጉዳዮች መካከል ብሬግዚት አንዱና ዋነኛው ነበር። የአውሮጳ ህብረት እና የብሪታንያ መንግሥት ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት በምትወጣበት በብሪግዚት ውል ላይ በተለያዩ ጊዜያት ቢስማሙም የብሪታኒያ ፓርላማ ውሉን ባለማጽደቁ ሂደቱን አጓታል። የብሪታንያ ሕዝብ ከ3 ዓመት በፊት ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት እንድትወጣ በህዝበ ውሳኔ በጠባብ ልዩነት ከወሰነ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ቴሬሳ ሜይ በ2019 ከብሪታንያ ምክር ቤት የገጠማቸውን

የበረታ ተቃውሞ ለማርገብ ብዙ ቢጥሩም አልተሳካላቸውም። ውሉ እንዲሻሻል ምክር ቤታቸው የጠየቃቸው ሜይ በ2019 ከለንደን ብራሰልስ በርሊን ፓሪስ እየተመላለሱ ተሰሚነት ያላቸውን የህብረቱን አባል ሃገራት መሪዎች ለማሳመን ቢሞክሩም ሳይሆን በመቅረቱ በግንቦት ከሥልጣናቸው እንደሚወርዱ አሳውቀው በሐምሌ ተሰናበቱ። ርሳቸው ተክተው ሥልጣኑን የያዙት ቦሪስ ጆንሰንም ተሻሻለ የተባለውን የብሬግዚት ውል ለምክር ቤቱ ቢያቀርቡም የሜይ እጣ ነበር የገጠማቸው። ሆኖም ጆንሰን በታኅሳስ በጠሩት አጠቃላይ ምርጫ ብሬግዚትን ለማሳካት የሚያስችል አብላጫ ድምጽ አገኙ። አስቀድመው እንደተመኙት ፓርቲያቸው አብዛኛውን የምክር ቤት መቀመጫ የተቆጣጠረው ጆንሰን በብሬግዚት ውል ላይ የምክር ቤቱን ይሁንታም አግኝተዋል። ከዚህ ቀደም በገቡት ቃል መሠረትም በጎርጎሮሳዊው ጥር 31፣2020 ብሪታንያን ከአውሮጳ ህብረት አባልነት እንደሚያስወጡ በእርግጠኝነት ተናግረዋል።
«በዚህ ሥልጣን እና በዚህ አብላጫ ድምጽ በስተመጨረሻ ምን ማድረግ እንችላለን «ብሬግዚትን ገቢራዊ ማድረግ «ትኩረት ሰጥታችሁታል።ምክንያቱም ይህ ምርጫ ብሬግዚትን ገቢራዊ

ማድረግ፣አሁን ለድርድር የማይቀርብ፣የማይቋቋሙት እና የማይከራከሩበት የብሪታንያ ሕዝብ ውሳኔ ነው።በዚህ ምርጫም የዳግም ሕዝበ ውሳኔ አሳዛኝ ዛቻ ሁሉ ያበቃል።»
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የብሪታንያ ምርጫ ተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ በ84 ዓመት ታሪኩ አይቶት የማያውቀው ከባድ ሽንፈት ነው የገጠመው። መሪው ጀርሚ ኮርቢን ከኃፊነታቸው እንደሚነሱ አስታውቀዋል።
ለአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ሴት ፕሬዝዳንት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሾመለት ዛሬ ከምንሰናበተው ከ2019 አጋማሽ በኋላ ነበር። የቀድሞ የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር  ፎን ዴር ላየን፣ ሳይጠበቅ እና ከተለመደው አሰራር በተለየ ለዚህ ሃላፊነት መታጨታቸው ቢያወዛግብም የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት የህዝብ እንደራሴዎች፣ ሹመቱን አጽድቆላቸዋል። በተለመደው አሠራር በ2019 በተካሄደው በአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ ፣አብላጫ ድምጽ ያገኙት የአውሮጳ ህዝቦች ፓርቲ በምህጻሩ የEPP ተቀዳሚ እጩ፣ ማንፍሬድ ቬበር በኮሚሽኑ ፕሬዝዳንትነት ይመረጣሉ የሚል ግምት ነበር። ሆኖም የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ  ቬበር ብቃት እና ልምድም ያንሳቸዋል ሲሉ አጥብቀው በመቃወማቸውና በዚህ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ላይ ሴት እንዲመደብም በመፈለጋቸው ቬበር ቀርተው ነበር ፣ፎን ዴር ላየን የታጩት። ምክር ቤቱ  በሐምሌ 2019 በሰጠው ድምጽ ከፎን ዴር ላየን በተጨማሪ የሥራ ዘመናቸው ባበቃው ሦስት

 ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ምትክ የታጩትን የቀድሞ ቤልጂግ ጠቅላይ ሚኒስትር ቻርልሰ ሚሼል፣ የህብረቱ የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት በምህጻሩ IMF የበላይ እና የቀድሞ የፈረንሳይ የገንዘብ ሚኒስትር ወይዘሮ ክርስቲን ላጋርድ የአውሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ገዥ፣ እንዲሁም የስፓኝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፕ ቦሬልን የህብረቱ የውጭ ጉዳዮች  ሃላፊነት ሹመቶችንም  አጽድቋል። ፎን ዴር ላየን ሥራ በጀመሩ በሳምንቱ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ነበር ያደረጉት። ኮሚሽነሯ የመጀመሪያውን ጉብኝታቸውን በአፍሪቃ ያደረጉበት ምክንያት ሲናገሩም፦ 
«ከአውሮጳ ውጭ የመጀመሪያውን ጉብኝቴን በአፍሪቃ ማድረግን መርጫለሁ።በአፍሪቃ ህብረት መገኘቴ ጠንካራ ፖለቲካዊ መልዕክት ያስተላልፋል።ምክንያቱም የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም እና የአፍሪቃ ህብረት ለአውሮጳ ህብረት እና ለህብረቱ ኮሚሽን አስፈላጊ ናቸውና።»ብለዋል።ፎን ዴር ላየን በጀርመን መራሂተ መንግሥት አስተዳደር ለ14 ዓመታት ሦስት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሚኒስትርነት መርተዋል።
የሩስያ እና የዩክሬንን ጠብ ለማረገብ ጀርመን እና ፈረንሳይ በፓሪስ የሁለቱን ሃገራት መሪዎች የሸመገሉት በዓመቱ የመጨረሻ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ የሩስያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንና፣ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን ፊት ለፊት አገናኝተው በተካሄደው ሽምግልና

ሁለቱ ሃገራት በምሥራቅ ዩክሬን እስከ ዓመቱ መጨረሻ  ሙሉ እና አጠቃላይ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል። ከ5 ዓመት በላይ በዘለቀው በዚህ ጦርነት ከሁለቱም ወገን የተያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምርኮኞችን እሁድ ተለዋውጠዋል። ሩስያ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ አውሮጳ የምታስተላልፍበትን በዩክሬን የሚያልፈውን መስመር እንድትጠቀም ዩክሬን መፍቀዷም ከሽምግልናው ውጤቶች አንዱ ነው። 
በዓመቱ አነጋጋሪ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ በመስከረም ወር ዛክሰን እና ብራንድንቡርግ በተባሉት ሁለት የቀድሞ የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች በተካሄደው ምርጫ  «አማራጭ ለጀርመን» በጀርመንኛው ምህጻር አ ኤፍ ዴ የተባለው የጀርመን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ሁለተኛዉን ከፍተኛ ዉጤት ማግኘቱ ነበር። የዚህ ምርጫ አሸናፊዎች አንጋፋዎቹ የጀርመን ፓርቲዎች የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት በምህጻሩ CDU እና የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ SPD ናቸው።ፓርቲዎቹ ቢያሸንፉም ያገኙት ድምጽ ከዛሬ 5 ዓመቱ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑ አስግቷል። ከሶስት ዓመት በዛሬ 3 ዓመቱ አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ላይም ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም እየተባለ ነው። 
በ2019 በጀርመን ትኩረት ስበው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በጀርመኑ የሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ውስጥ የሚገኘው ካስል የተባለው ከተማ ዋና አስተዳዳሪ የቫልተር ሉብከ ግድያ ነው። የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር CDU ፖለቲከኛ የ64 ዓመቱ ሉብከ በቤታቸው የአትክልት ስፍራ በቅርብ ርቀት ተተኩሶባቸው ነበር የተገደሉት።ፖለቲከኛው የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የስደት ፖሊሲ ደጋፊ ነበሩ። ሉብከ በተገደሉ በሁለተኛው ሳምንት አቃቤ ሕግ በግድያው የጠረጠረውን ሽቴፋን ኢ የተባለ ግለሰብ መያዙን ካሳወቀ በኋላ በጀርመን የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ እያነጋገረ ነው። ከሉብከ ግድያ በኋላ ስደተኞችን በመ,ርዳት የሚታወቁ አራት የተለያዩ የጀርመን ከተሞች ከንቲባዎች ከቀኝ አክራሪዎች የግድያ ዛቻዎች እንደደረሱዋቸው ተናግረዋል። 

በመስከረም 2019 ነበር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሄሰን የሰላም ሽልማት የተሰጣቸው።በጀርመንዋ በሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ በቪስባደን በተካሄደው ዓመታዊ የሄሰን የሰልማ ሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ ተሸላሚው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አልተገኙም።በርሳቸው ስም ሽልማቱን የተቀበሉት የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚልበስነ ስርዓቱ ላይ የዶክተር ዐብይን መልዕክት በንባብ አሰምተው ነበር። 
በሰኔ 2019 በተካሄደው የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ አንጋፋው የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ  እጅግ አነስተኛ ድምጽ ማግኘቱ ፓርቲውን የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ከቶታል። በዚህ ሰበብ የፓርቲው መሪ አንድርያ ናለስ ከሥልጣናቸው ወርደው  ሦስት ጊዜያዊ መሪዎች ከተሰየሙ በኃላ በህዳር  በተካሄደው ምርጫ ኖርበርት ቫልተር ቦርያንስ እና ሳሲካ ኤስከንን በጋራ ፓርቲው  በመሪነት ሰይሟል። 
የናለስ በፈቃዳቸው መነሳት ለጀርመን ፖለቲካ እንደ ድንገተኛ የልብ ድካም ተደርጎ ነው የተወሰደው። ስንብታቸው ለዓመታት ፓርቲውን ሲመዘምዝ የቆየው በሽታ የመጨረሻው ምልክትም ተብሏል። በዓመቱ በአውሮጳ ከደረሱት አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ በጥቅምት ወር ለንደን አቅራቢያ የ39 ሰዎች አስከሬን በእቃ ማመላሻ ከባድ መኪና ውስጥ መገኘቱ ነው። ሟቾቹ መጀመሪያ ላይ ቻይናውያን ናቸው ቢባልም ከቀናት በኋላ ግን የቬይትናም ዜጎች መሆናቸው ተረጋግጧል። ሕገ ወጥ በሚባል ስደት ወደ አውሮጳ ለመሻገር ሲሞክሩ ለንደን አቅራቢያ ሞተው የተገኙት እነዚሁ ቬትናማውያን ከ6 የሃገሪቱ የተለያዩ ክፍላተ ሃገር የመጡ መሆናቸው ተነግሯል። የቬይትናም ባለሥልጣናት እንዳሉት በዚሁ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር  የተጠረጠሩ 11 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

Audios and videos on the topic