አውሮጳ እና ህገ ወጥ የሰው አሻጋሪዎች | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 13.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

አውሮጳ እና ህገ ወጥ የሰው አሻጋሪዎች

የአውሮጳ መንግሥታት ህገ ወጥ የሚሉትን ስደት ለመግታት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች አጠናክረው ቀጥለዋል ። ይሁን እና በሜዲቴራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩት ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:49
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:49 ደቂቃ

ህገ ወጥ የሰው አሻጋሪዎች


ስደተኞች በአደገኛ የባህር ጉዞ አውሮፓ ለመግባት የሚያደርጉትን ሙከራ ለማስቆም የአውሮጳ መንግሥታት በጋራም ሆነ በተናጠል እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል ። ከመካከላቸው ህገ ወጥ የሚባሉ የሰው አሻጋሪዎችን አድኖ መያዝ እና ለፍርድ ማቅረብ ፣ ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር ማድረግ እንዲሁም የስደተኞች ዋነኛ መሸጋገሪያ ከሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት ጋር ውሎች ላይ መድረስ ይገኙበታል ። በ2016 በኢጣልያ በቤልጂግ በፈረንሳይ እና በስዊድን ሰዎች ን በማሻገር የተጠረጠሩ ተይዘዋል ። ከ2015  ዓመተ ምህረት መጨረሻ አንስቶ የጀርመንዋን ደቡባዊ ግዛት ባቫርያን ከኦስትሪያ ጋር የሚያዋስነው 815 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ድንበር ፣ እና እንዲሁም 360 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የጀርመን እና የቼክ ሪፐብሊክ ድንበር ጥብቅ ቁጥጥር ይካሄድባቸዋል ። በ2015፣ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ወደ ሰሜን አውሮጳ ሀገራት የተሻገሩበት ይህ የባልካን የጉዞ መስመር በነዚህ እርምጃዎች ሲዘጋ ስደተኞች ፊታቸውን እንደገና ወደ ሜዲቴራንያን ባህር መልሰዋል ። ሊገባደድ ጥቂት ቀናት በቀሩት በ2016 ብቻ ኢጣልያ ደቡባዊ ወደቦች ከ173 ሺህ በላይ ስደተኞች መግባታቸው ተመዝግቧል ። የአውሮፓ መንግሥታት ህገ ወጥ የሰው አሻጋሪዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየወሰድን ነው በሚሉበት በዚህ ዓመት በሜዴትራንያን ባህር በኩል አውሮጳ የገቡት ስደተኞች ቁጥር አሻቅቧል ለምን ? ኤጀንስያ አበሻ የተሰኘው የባህር ስደተኞችን የሚረዳው ግብረ ሰናይ ድርጅት መሥራችና መሪ አባ ሙሴ ዘርአይ የሰው አሻጋሪዎችን መያዝ መቅጣትና ሌሎችም ቁጥጥሮችን ማድረግ  ተገቢ ነው ይላሉ ። ሆኖም በርሳቸው አባባል ይህ መሠረታዊውን ችግር የሚፈታ እርምጃ ባለመሆኑ ነው በባህር የሚመጣው ስደተኛ ቁጥር እየጨመረ የሄደው  ። 

የተመድ እንደሚለው በ2016 ቢያንስ 4700 የባህር ስደተኞች መንገድ ላይ ህይወታቸው አልፏል ። ይህም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው ።  ኢጣልያ በ2016 ባካሄደችው የተጠናከረ ዘመቻ በየቀኑ ማለት ይቻላል በአደገኛ የባህር ጉዞ ሰዎችን ወደ አውሮጳ በመላክ የሚጠረጠሩ ሰዎችን ስትይዝ ቆይታለች ።በተለይ ከአቅማቸው በላይ ስደተኞችን የሚታጨቁባቸውን ለንቋሳ ጀልባዎችን ሾፍረዋል ተብለው የተጠረጠሩ በርካቶች በፖሊስ ታድነው ታስረዋል ።ፖዞሎ ከተባለችው ደሴት በ2016 ፣179 ሰው በማሻገር የተጠረጠሩ ተይዘዋል ። ከመካከላቸው 26 ቱ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ታዳጊዎች ናቸው ።ከዚህችው ወደብ በ2015 ፣ 147 ተጠርጣሪዎች ወህኒ ወርደዋል ። ከሌላዋ አውጉስታ ከተባለችው የወደብ ከተማም በ2016 ፣ ከ 190 በላይ ተጠርጣሪ ሰው አሻጋሪዎች ታድነው ታስረዋል ፣ ካታንያ በተባለችው ከተማም  ፖሊስ በ2016 የያዛቸው ተጠርጣሪዎች ቁጥር ከ79 በልጧል ። በዚህች ከተማ ከሦስት ዓመት በፊት የተያዙት ቁጥር 13 ነበር ።ይሁን እና አባ ሙሴ እንደሚያስረዱት ኢጣልያ የያዘቻችው እና ለፍርድ ያቀረበቻቸው ቀንደኛዎቹን የሰው አሻጋሪዎች ሳይሆን ፣ በድርጊቱ ተባብረዋል ያለቻቸውን ስደተኞች ነው ።
ይህ እጣ ከገጠማቸው ስደተኞች መካከል  በመሣሪያ ተገድጄ ጀልባውን እንድነዳ ተደረግኩ የሚለው ቶጎዋዊው ማርክ ሳሚ የተባለው ስደተኛ ይገኝበታል ። ማርክ የ7 ወር ተኩል ነፍሰ ጡር ከነበረችው ባለቤቱ ጋር ባለፈው ዓመት ሐምሌ በጀልባ ከሊቢያ ወደ አውሮጳ ለመምጣት ከሚጠባበቁት ስደተኞች አንዱ ነበር ።  ታጣቂ ሰው አሻጋሪዎች ማርክን ከባለቤቱ ነጥለው ሽጉጥ ደቅነውበት አስገድደው የላስቲኳን ጀልባ እንዲነዳ ኮምፓስ እና የሳተላይት ስልክ ሲሰጡት እምቢ ብሎ ነበር ።በእግሩ መሀል ወደ መሬት ተኩሰው አንተንም ባለቤትህንም እንገድላችኋለን ብለው ሲያስፈራሩት ምርጫ ያጣው የ21 ዓመቱ ሳሚ ስደተኞች የተጫኑበትን ጀልባ ለመንዳት መገደዱን ለአሶስየትድ ፕሬስ ተናግሯል ። ሆኖም የህገ ወጥ ሰው አሻጋሪዎች ሰለባው ማርክ ኢጣልያ ከደረሰ በኋላ የወንጀለኞቹ ተባባሪ ተብሎ ተይዟል ። ይህ የሆነው ባለፈው ሐምሌ ሲሆን ያኔ በሚቀጥለው ጀልባ ትመጣለች ብለው ከርሱ የነጠሏትን ባለቤቱን እስካሁን

አይቷት አያውቅም ። ሳሚ የኢጣልያ ፖሊስ አቃቤ ህግ እና ዳኞች ሰው አሻጋሪዎችን ለመያዝ እና ለመቅጣት ባካሂዱት ዘመቻ ከታሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የባህር ስደተኞች እንዱ ነው ። አንዳንድ ዳኞች እንደ ማርክ ጀልባ ለመንዳት የተገደዱትን ስደተኞች በነፃ ለቀዋል  ። ሰው  አሻጋሪዎች በ2000 ዩሮ ገዝተው ስደተኞችን ወደ አውሮጳ ከሚልኩባት ጀልባ የሚያተርፉት ገንዘብ 100 ሺህ ዩሮ ይደርሳል ።አሁን ግን እነዚህ ቡድኖች ከ8 እስከ 9 ሰዓት ብቻ በባህር ላይ ሊቆዩ በሚችሉ ርካሽ ጀልባዎችን ነው ሰዎችን አሳፍረው የሚልኩት ።መጨረሻ ላይ የሚመጡትን ምናልባትም በቂ ገንዘብ የሌላቸውን ስደተኞች ነው ጀልባውን እንዲነዱ የሚያደርጉት ። ሁሉም አደገኛው የባህር ጉዞ እንዴት እንደሚካሄድ ያውቃሉ ። ይሁን እና ችግሩ ሰዎቹ ሥራቸውን የሚያካሂዱት መንግሥት አልባ በሆነችው በሊብያ በመሆኑ እነርሱን ከዚያ አድኖ መያዝ አለመቻሉ ዋናው ችግር ነው ይላሉ የኢጣልያ ባለሥልጣናት ። በሌላ በኩል የአውሮጳ መንግሥታት ስደተኞች እንዳይመጡባቸው ለመከላከል ከአንዳንድ የአፍሪቃ መንግሥታት ጋር ውሎች እየተፈራረሙ ነው ። ይህም በጎርጎሮሳዊው ህዳር 2015 ቫሌታ ማልታ ውስጥ በተደረሰበት   የስደት ምንጮች የተባሉ መሠረታዊ ችግሮችን መፍታት ያስችላል በተባለ የ1.8 ቢሊዮን ዩሮ የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ መንግሥታት የእርዳታ ስምምነት  መሠረት ነው የሚካሄደው ።ህብረቱ ባለፈው እሁድ ከማሊ ጋር የተገን ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን ለመመለስ ተስማምቷል።  እንደ ማሊ ሁሉ ከኢትዮጵያ ከሴኔጋል ከናይጀሪያ እና ከኒዠር እንዲሁም ከአፍጋኒስታን ጋር ስደተኞችን መጠረዝ የሚያስችሉ ተመሳሳይ ውሎች ላይ ለመድረስም እየጣረ ነው ። አባ ሙሴ ግን ይህም ችግሩን በዘላቂነት  ይፈታል ብለው አያምኑም ።በርሳቸው አስተያየት  መፍትሄው ህጋዊውን መንገድ መክፈት ብቻ ነው ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic