አውሮጳን ያሰጋው ስደት | ዓለም | DW | 19.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

አውሮጳን ያሰጋው ስደት

ወደ አውሮጳ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በሶስት እጥፍ መጨመሩን ‘ፍሮንቴክስ’ የተባለው ለአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የድንበር ጥበቃ ድጋፍ ሰጭ ድርጅት አስታወቀ። የስደተኞች ቀውሱ አሳሳቢ ደረጃ በመድረሱ ትኩረት ያሻዋል ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:59

አውሮጳን ያሰጋው ስደት

ለ28ቱ የአውሮጳ ህብረት አባል አገራት የድንበር ጥበቃ ድጋፍ በሚያቀርበው ‘ፍሮንቴክስ’መረጃ መሰረት ወደ አውሮጳ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ባለፈው አመት በተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው በሶስት እጥፍ ጭማሪ አሳይቷል። ድርጅቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ 107 ሺህ ሰዎች በሐምሌ ወር ከአውሮጳ ህብረት አባላት ድንበር መድረሳቸው ተረጋግጧል።

ሁኔታውን አሳሳቢ ያለው ተቋሙ ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር በዚሁ ይቀጥላል ሲል አስታውቋል። በዚህ አመት ከጥር እስከ ሰኔ 340, 000 ስደተኞች አውሮጳ የደረሱ ሲሆን ባለፈው አመት በተመሳሳይ ጊዜ የገቡት ቁጥር ደግሞ 280,000 ነበር።

የድርጅቱ ዋና ኃላፊ ፋብሪስ ላጌሪ «ይህ የአውሮጳ ህብረት አባላትን ትኩረት የሚሻ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።» ሲሉ ተናግረዋል። የአውሮጳ ህብረት ቃል አቀባይ ክርስቲያን ዊጋንድ ችግሩ መላ አውሮጳን የሚያሳስብ መሆኑን ይናገራሉ።

«በወርሃ ሐምሌ ብቻ ወደ አውሮጳ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስት እጥፍ አድጎ ከ100,000 በላይ ደርሷል። ከጥር እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ የአውሮጳ ህብረት 28 አባል አገራት ከ400,000 በላይ የተገን ጠያቂ ማመልከቻዎችን ተቀብለዋል። ባለፈው አመት አጠቃላይ የተገን ጠያቂዎች ቁጥር 600 ሺህ ነበር። ይህ የግሪክ፤ የጣሊያን፤ የጀርመን፤ ሃንጋሪ፤ የፈረንሳይ ወይም የኦስትሪያ ብቻ ቀውስ አይደለም። ይህ የመላው ዓለም የስደት ቀውስ ነው። እናም አሁንም ይሁን ወደፊት ጠንካራ እና የተባበረ እርምጃ ይፈልጋል።»

የአውሮጳ ህብረት በስደተኞች ጎርፍ ለተጥለቀለቁት አባል አገራት 2.4 ቢሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ አጽድቋል። አብዛኞቹ ስደተኞች ከሶርያ፤ኢራቅና አፍጋኒስታን አለመረጋጋትና ጦርነት የሚሸሹ ናቸው። እነዚህ ስደተኞች ከግሪክ፤ከኢጣልያና ከምዕራብ ባልካን አገሮችን ወደ አውሮጳ ለመግባት ይመርጣሉ።

ሃንጋሪ ድንበሯን የሚሻገሩ ስደተኞች ላይ ጥብቅ የተባለ እርምጃ ልትወስድ ተዘጋጅታለች። የድንበር ቁጥጥር እና ከሰርቢያ የምትጋራውን የድንበር አካባቢ በአጥር የመከለል እርምጃዎች በአገሪቱ ባለስልጣናት ተግባራዊ ሊሆኑ ነው ተብሏል። ባለፈው ሳምንት ብቻ 21,000 ስደተኞች የተቀበለችው ግሪክ የአውሮጳ ህብረት አባል አገራት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርባለች። የአውሮጳ ህብረት የስደተኞች፤ዜግነትና አገር ውስጥ ጉዳይ ኮሚሽነር ዲሚጥሪስ አቭራምፖሎስ አሁን የተፈጠረውን ቀውስ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጀሪያው ብለውታል።

«ዓለም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ አስከፊ ከሆነ የስደተኞች ቀውስ ገጥሞታል። አውሮጳም በድንበራችን ውስጥ ተገን ጥየቃ በገፍ ከሚመጡ ስደተኞች ጋር በመታገል ላይ ነች። ግሪክ ያለው ሁኔታ እጅጉን አሳሳቢ ነው። ሁኔታውን የመቆጣጠር ኃላፊነት በሁሉም አባል አገራት ላይ የተጣለ ነው። አገራዊ ኃላፊነታችንን አደጋ ውስጥ ሳንጥል አቅማችን በፈቀደ ሁሉ እርዳታ እናቀርባለን።»

28ቱ የአውሮጳ አገራት አሁን ተፈጠረ በተባለው የስደተኞች ቀውስ ግን እኩል ተጠቂ አይደሉም። ወደ አውሮጳ ከሚደርሱ ተገን ጠያቂዎችና ስደተኞች መካከል አንድ ሶስተኛው ወደ ጀርመን ያቀናሉ።በዚህ አመት ብቻ እስከ 750, 000 የሚደርሱ የሶርያና የባልካን አገሮች ስደተኞች ወደ ጀርመን ይገባሉ ተብሏል። ፈረንሳይና እንግሊዝ በካሌ የተፈጠረውን ቀውስ መፍትሄ ለማበጀት አንዳች ስምምነት ለመፈራረም እቅድ ላይ ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የአውሮጳ ህብረት አባል አገራት ተገን ጠያቂዎችን በኮታ በመከፋፈል ጀርመንና ስዊድንን ሊያግዙ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። በከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የምትገኘው ግሪክ በግዛቷ ለሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ምንም አይነት እገዛ ማቅረብ ተስኗታል ተብሏል። ኮስ ከተባለው አነስተኛ ደሴት ስደተኞችን ከሞት ማትረፍ የቻለችው ግሪክ የስደተኞቹን መሰረታዊ የምግብና አልባሳት ወጪ ለመሸፈን የአውሮጳ ህብረትን የገንዘብ ድጋፍ ጠይቃለች ተብሏል።

በስደተኞች ብዛት ለተማረሩት የአውሮጳ ህብረት አባል አገራት ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የሚደመጠው ዜና ግን መልካም አይመስልም። የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ ሰዎች ቁጥር በዚህ አመት መገባደጃ ከ300 ሺህ በላይ እንደሚሆን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic