አውሎ ነፋስ የቀላቀለ የባህር ማዕበል | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 18.09.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አውሎ ነፋስ የቀላቀለ የባህር ማዕበል

በኢትዮጵያ ፣ መስከረም ወር ፣ክረምት አልፎ ከባድ ደመና የሚገፍበት ሰማዩ የሚጠራበት ፤ ምድሪቱ በለምለም ሳርና በተፈጥሮ አበባ አጊጣ የምትታይበት ወቅት፣ ጥቢ ሲሆን ፣ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ደግሞ ብርቱ ዝናም የሚያጋጥምበት ፣ ማዕበልም

ከውቅያኖስ የሚነሣበት ጊዜ ነው። ለምሳሌ ያህል የአትላንቲክ ምዕራባዊ ከፍል፣ የካራይብ ባህርና የሜክሲኮ ባህረ ሰላጤ አዋሳኝ አገሮችና ጠረፎች!

ከሰሞኑ ፤ ነፋስ የቀላቀለ የባህር ማዕበል ፤ ዶፍ በማውረድ ከተሞችንና ጎዳናዎችን በማጥለቅለቅ፣ የብዙ ሰዎች ሕይወት የቀጠፈው አሰቃቂ የተፈጥሮ ቁጣ ይበልጥ የተከሠተው በሜክሲኮ ነው። በሜክሲኮ ብቻ ፣እስከዛሬ ቢያንስ 57 ሰዎች ናቸው ህይወታቸውን ያጡት። የሜክሲኮ ብሔራዊ የነፍስ አድን አገልግሎት እንዳስታወቀው፤ ቬራክሩዝ፤ ገሬሮ፤ ፑየብላ፤ ኢዳልጎ፣ ሚቾዋካንና ኦክሳካ በተባሉት ክፍለተ ሀገር የደረሰው ብርቱ ማጥለቅለቅ ከዚህ ቀደም ታይቶ ያልታወቀ ነው። አካባቢው ከሁለት አቅጣጫ ከአውሎ ነፋስ ጋር ማዕበል ቀላቅሎ በመጣ አደጋ ነው ክፉኛ የተጠቁት። «ኢንግሪድ » የሚል ስያሜ የተሰጣት ከሜክሲኮ ባህረሰላጤ የተነሳች ማዕበል፤ እንዲሁም « ማኑኤል» የተባለው ከሰላማዊው ውቅያኖስ የተነሳውና በአካፑልኮ የወደብ ከተማና በሌሎችም ጥፋት ያደረሰው ማዕበል፣ ሁለቱም፣ መኻል ላይ ተገናኝተው ነው ፣ ከባህር ፣ በአውሎ ነፋስ የጫኑትን ወሃ በተጠቀሱት ክፍላተ ሀገር የዘረገፉት።

የአካፑልኮ ከተማ ከንቲባ ፣ እንደገለጡት ፣ በዚሁ አደገኛ ማዕበል ሳቢያ ባለፉት ጥቂት ቀናት 40 ሺ ሀገር ጎብኝዎች ከከተማይቱ ወጥተው መንቀሳቀስ ተስኖአቸው እንደነበረ ሲታወቅ፣ ገና ዛሬ ነው 2,750 ገደማ የሚሆኑትን በወታደራዊና ሲቭል አኤሮፕላኖች ከአካባቢው ማስወጣት የተቻለው። ። የሜክሲኮው ፕሬዚዳንት ኤንሪከ ፔና ኒቶም፤ ከትናንት በስቲያ ፣ ማዕበሉ በአካፑልኮና በገሬሮ ከፊል ግዛት ፤ ጎርፍ ያደረሰውን ብርቱ የማጥለቅለቅ አደጋ በአኤሮፕላን እየተዘዋወሩ ከጎብኙ በኋላ ፤ መንግሥት ተጎጂዎች የሚረዱበት ገንዘብ ፤ መመደቡን አስታውቀዋል። በሜክሲኮ ፣ ጎዳናዎች ከጥቅም ውጭ እስኪሆኑ ሲጥለቀለቁ፣ የአፋርና ቋጥኝ መናድም ከባድ አደጋ ነው ያስከተለው።

አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ማዕበል በየጊዜው ፤ ከሞላ ጎደል በያመቱ እጅግ ከሚያሠጋቸው በካራይብ ባህር ከሚገኙት ደሴቶች መካከል አንዷ፣ እ ጎ አ በ 2010 መግቢያ ገደማ የምድር ነውጥ ሰለባ በመሆን ክፉኛ የተጎነጠችው ፤ በምዕራቡ ንፍቀ ክብብ እጅግ ድሃይቱ ሀገር እየተባለች የምትጠቀሰው ሄይቲ ናት። ሌሎቹን የእርሷን አጎራባች ደሴቶችንም የተፈጥሮው መቅሠፍት ፤ማዕበሉ ፤ ምሯቸው አያውቅም። እጅግ አደገኛው ከውቅያኖስ በሚፈጠር አውሎ ነፋስ ውሃ ጭኖ የሚከንፈው ነፋስ፤ በአትላንቲክና በምሥራቃዊው ሰላማዊው ውቅያኖስ አካባቢ «ሃሪኬን » ሲባል፤ በምዕራባዊው ሰላማዊ ውቅያኖስ «ታይፉን»፤ በህንድ ውቅያኖስና በአውስትሬሊያ ደግሞ «ሳይክሎን» በሚል መጠሪያ ነው የሚታወቀው። በመሠረቱ ፤ ሃሪኬን፤ ታይፉን ተባለ ሳይክሎን ፣ በምድር ሰቅ ዙሪያ በሙቀት ሳቢያ የሚተን ውሃ፣ ከቀዝቃዛ አየር ጋር ተጋጭቶ የሚፈጥረው አውሎ ነፋስና ውህ ጭኖ የሚከንፍ ማዕበል ነው።

የተቀጠለ አየር (CO2) ልቀት እየጨመረ መሄድ የተለያዩ ፣ የኦክስጂን ጋዝ ክምችት(ኦዞን) ፀር የሆኑ ጋዞችም መታከል፣ ከአካባቢ ብክለት ባሻገር የፕላኔታችን ሙቀት እየጨመረ እንዲሄድ በማድረግ ሊያስከትል ስለሚችለው ጥፋት በየጊዜው ነው የሚነገረው። ሙቀት እየጨመረ በመምጣቱ ፣ የአርክቲክና የአንታርክቲክ የበረዶ ተራሮች እየቀለጡ፤ በማናድ ላይ ናቸው። የሙቀት መጨመር አውሎ ነፋስና ማዕበል እንዲጨምር ነው የሚያደርገው።

ታዲያ ከባህር የሚቀሰቀስ ውሃ ተሸክሞ በሚነፍስ አውሎ ነፋስ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ ከመነሻው ከሥር ከመሠረቱ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ቅድመ -ጥንቃቄ ያደረግ ዘንድ መረጃ በማቅረብ ለማስጠንቀቅ አዲስ ሳይንሳዊ ምርምር ለማካሄድ የተነሳሱ አሉ። ከእነዚህም ዋናው የዩናይትድ እስቴትስ ብሔራዊ የበራራና የኅዋ ነክ መስተዳድር (NASA) ሲሆን፤ እርሱም፣ በምድር ሰቅ አካባቢ በሞቃት አየር የሚፈጠሩ ማዕበሎችንና በአውሎ ነፋስ ውሃ ቀላቅሎ የሚከንፍ ማዕበልን (ሃሪኬን) እንቅሥቃሴ የሚከታተሉ ጥቂት ለየት ያሉ አብራሪ የለሽ አኤሮፓላኖችን አሠማርቷል። እነዚህ አብራሪ የለሽ አኤሮፕላኖች፤ ከህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላኖች የበረራ መሥመር እጥፍ መጥቀው ፣

21,000 ሜትር(21 ኪሎሜትር ) ከፍታ ላይ መብረር የሚችሉ ናቸው።በሜክሲኮ የባህር ሰላጤ ጠረፍ እንደሚገኙ የሜክሲኮ ከተሞች ሁሉ፤ በዩናይትድ እስቴትስም ከጠረፍ በ 80 ኪሎሜትር ርቀት መካከል 100 ሚሊዮን ያህል የአካባቢው ዜጎቿ እንደሚኖሩ የታወቀ ነው። ታዲያ፣ እነርሱም የውቅያኖስ ማዕበል የቀላቀለ አውሎ ነፋስ በሚያልፍበት መሥመር ስለሚገኙ በየጊዜው ለአደጋ ሊጋለጡ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ እሙን ነው።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic