አዉሮጳዉያንን ያፋጠጠዉ የስደተኞች ጎርፍ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 17.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

አዉሮጳዉያንን ያፋጠጠዉ የስደተኞች ጎርፍ

ወደአንድ መቶ ሺ ገደማ የሚሆኑ ስደተኞች በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻ ወደአዉሮጳ ገብተዋል። ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ 2,000 የሚሆኑት ወደአዉሮጳ ለመግባት ሲጓዙ መንገድ ላይ ሕይወታቸዉ አልፏል አለያም የደረሱበት አልታወቀም።

የስደተኞቹ የመጀመሪያ መግቢያ የሆኑት ጣሊያንና ግሪክ አሁን የተሸከሙት የጥገኝነት ፈላጊ ብዛት ሳያንሳቸዉ ገና ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት ቀናት ተጨማሪ ስደተኞች ተበራክተዉ ሊመጡ እንደሚችሉ በመገመት ከወዲሁ በስጋት ተዉጠዋል። በተለያዩ የአዉሮጳ ግዛቶች የሚገኙ ተሰዳጆች ከአንዱ ሀገር ይሻለናል ወዳሉት ለመሸጋገር ይሞክራሉ። የሚሳካላቸዉ ግን ሁሉም አይደሉም።

የአዉሮጳ ኅብረት የአባል ሃገራት የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስደተኞችን በየሀገራቱ በእኩል ደረጃ ለመከፋፈል የጀመሩት ዉይይት እጅግም አዎንታዊ ዉጤት አላስገኘም። ጣሊያን መንግሥታቱ ሊተባበሯት ፈቃደኛ ካልሆኑ ስደተኞቹን ወደፈለጉበት መሄድ እንዲችሉ ልትለቃቸዉ እንደምትችል እያስፈራራች ነዉ። ፈረንሳይና ጣሊያን ድንበር አካባቢ የተሰባሰቡ ስደተኞችን ትናንት የሁለቱም ሀገራት ፖሊሶች ከግዛታቸዉ ሊያስወጡ ሲታገሉ በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ታይቷል።

ጣሊያን በስደተኞች ጎርፍ በመጥለቅለቋ ወደግዛቷ የገቡትን ጥገኝነት ፈላጊዎች ሳትመዘግብ ወደተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት እንዲሻገሩ መንገዱን የከፈተች ይመስላል። ጣሊያን ዉስጥ ያልተመዘገቡ ደግሞ በአብዛኛዉ ወደብሪታንያ ነዉ መጓዝ የሚሹት። ነገር ግን ብሪታንያ ድንበሮቿን ሁሉ በጥብቅ አጥራለች። በዚህ ምክንያትም አብዛኞቹ ተሰዳጆች በፈረንሳይዋ የድንበር ከተማ ካሌ ለመከማቸት ተገደዋል። ከዚያ ተነስተዉ ነዉ በመርከብ፤ በባቡር ወይም በትላልቅ እቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ተሸሽገዉ ወደብሪታንያ ለመግባት የሚሞክሩት።

ዩኒስ አልመሃዲ ከሱዳን ወደሊቢያ ለመድረስ ከዚያም በሜዲትራንያን ባህርን አቋርጦ ወደአዉሮጳ ለመግባት ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቶበታል። በመጨረሻ ካሰብኩበት ደረስኮ ብሎ ነበር። ግን ደግሞ አሁን በፈረንሳይዋ ካሌ ግዛት በድንኳን መጠለያ ዉስጥ ነዉ። አሁንም ጉዞዉ ገና አላበቃም ብሪታንያ እገባለሁ ባይነዉ።

«ለጊዜዉ ተስፋዬ የተሟጠጠና የተከፋሁ ነኝ። አዉሮጳ ዉስጥ የምገኝበት በተለይም እዚህ ያለዉ የፈረንሳይ ሁኔታ ያስከፋል። ክብር የነበረኝ ሰዉ ነበርኩ ግን አሁን ያንን አጥቻለሁ። እዚህ ልክ እንደእንስሳ ነዉ የምንያዘዉ።»

በድንገት በመጠለያቸዉ አካባቢ አንድ ድምጽ ተሰማ። ወደብሪታንያ በሚወስደዉ አዉራ ጎዳና ላይ ተሽከርካሪዎች በረድፍ ተደርድረዉ እየተጠባበቁ ይጓዛሉ። በዚህ ጊዜ እያንዳንዱ ተሰዳጅ ከሚጓዙት ትላልቅ ተሽከርካሪዎች ላይ ዘልሎ በመዉጣት ወደሚመኛት ሀገር ለመሄድ እድሉን የሚሞክርበት አጋጣሚ እንደሆነ ያዉቃል። ሆኖም ግን ተሽከርካሪዎቹ ሁሉ ተሰዉሮ ለመጓዝ የሚመቹ አይነቶች አይደሉም። አንዳንዶቹ ከባድ ሸክሞችን ጭነዋል፤ ያ ቢቀር እንኳ ከፖሊስ ለመሰወር አይቻልምም ይሆናል።

«ታዉቃለህ በየጊዜዉ ይህንን መሞከር ይኖርብኛል። ምናልባት ዛሬ ለሁለተኛ ወይም ለሶስተኛ ጊዜ። እዚህ ያሉት በሙሉ እንዲሁ ደጋግመዉ መሞከር ይኖርባቸዋል።»

ወደመጠለያቸዉ ስንመለስ የካሌ ጫካ ይሉታል። ወደ4,000 የሚሆኑ ሴቶችና ወንዶች እንዲሁም ሕፃናት በዚህ ጊዜያዊ መጠለያ ይኖራሉ፤ በየቀኑም አዳዲስ ይጨመሩባቸዋል። የግል የእርዳታ ድርጅቶች በቀን አንድ ጊዜ ምግብ ያከፋፍሏቸዋል። ሆኖም ግን ቁጥራቸዉ እየጨመረ በመሄዱ ማሳሰቡ አልቀረም። ላበርግ ደ ሚግራንትስ L'Auberge des Migrantsከተሰኘዉ ማኅበር ክርስቲያን ሳሎሜ ይህንኑ ነዉ የሚያስረዱት፤

«ባለፈዉ ዓመት 2,500 ስደተኞች ነበሩን እዚህ። በመካከሉ ከሜዲትራንያን የሚጎርፉት ቁጥር በሶስት እጥፍ ጨመረ። በቅርቡ በካሌ አድርገዉ ወደብሪታንያ ለመግባት የሚሹት ስደተኞች 8000 ይደርሳሉ። በዚህ አይነት የሚያባራ አይመስልም።»

በማዕከላዊ ካሌ ስደተኞቹ የከተማዋ ገፅታ ሆነዋል። የፈረንሳይዋ የድንበር ግዛት ወደብሪታንያ የመግባት የሚሹ ተሰዳጆች በብዛት የሚገኙባት ትልቋ መዳረሻ ናት። ወደእቃ መጫና መርከቦችና ትላልቅ ተሽከርካሪዎች እንዳይወጡ እንዲያግድ በወደቡ ላይ አንድ ሜትር ከፍታ ያለዉ አጥር ብሪታንያ መንግሥት ዘርግቷል። ሃሳቡም ስደተኞች ድንበር አልፈዉ እንዳይገቡ ቁጥጥሩን ለማጥበቅ ነዉ። ዩኒስ አልመሃዲ

« ከፖሊስ ጋ እዚህ እንጋጫለን። በዚያም ላይ ከማኅበረሰቡና ከድርጅቶችጋም እንጋጫለን። በእዉነት እዚህ መኖር አይቻለም። ሆኖም ግን እዚሁ ተቀምጠናል።»

ወደብሪታንያ ቢሻገርም ለዩኑስ የተሻለ ሕይወት የማግኘቱ ተስፋ እጅግ አናሳ ነዉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብሪታንያ ዉስጥ እጅግ በጣም ጥቂት የጥገኝነት ጥያቄዎች ናቸዉ አዎንታዊ ምላሽ የሚያገኙት። ጥገኝነት ጠያቂዎች ምላሽ ለማግኘት ዓመታት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ግን የዩኑስን እቅድ የሚያስለዉጥ ነገር አይደለም። አሁን ካለበት የከፋ ነገር ይገጥመኛል ብሎ አያምንም።

Lars Scholtyssyk/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic