አወዛጋቢው የጤፍ የባለቤትነት መብት ክርክር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 06.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አወዛጋቢው የጤፍ የባለቤትነት መብት ክርክር

መነጋገሪያ ሆኖ የከረመው የጤፍ የባለቤትነት ጉዳይ በኔዘርላንድስ መቋጫ ያገኘ ቢመስልም በአራት የአውሮፓ ሀገራት ግን አሁንም በአንድ የግል ድርጅት ስም እንደተመዘገበ አለ። የጤፍ ዳቦን ለደንበኞቹ ለማቅረብ ሲዘጋጅ የተከሰሰው የኔዘርላንድስ ኩባንያ የችሎት ሙግቱን ካሸነፈ በኋላ የቀደመ እቅዱን ተግባራዊ ሊያደርግ ቀን መቁረጡን አስታውቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:33

አወዛጋቢው የጤፍ የባለቤትነት መብት ክርክር

ከተመሰረተ አንድ ምዕት ዓመት ያለፈው ባክልስ የተሰኘው የኔዘርላንድስ ኩባንያ በዳቦ ምርቶቹ ዝናን ያተረፈ ነው። ሁለት ሺህ ገደማ የምርት አይነቶች አሉኝ የሚለው ይህ ኩባንያ በ115 ዓመት ታሪኩ ከምርት ግብዓቶች ጋር በተያያዘ የተከሰሰው አንዴ ብቻ መሆኑን ይገልጻል። ይህን ብቸኛ ክስም ቢሆን ሶስት ዓመት ከፈጀ የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ ውድቅ አስደርጓል። እንዲያም ቢሆን ግን ኩባንያው እዚህ ሁሉ ውዝግብ ውስጥ ያስገባውን የምርት ግብዓት ችላ አላለም። ይልቁንም ይህን ግብዓት ተጠቅሞ የሚያመርተውን አዲስ አይነት ዳቦ በመጪው ወር ተጠቃሚዎች ዘንድ ለማድረስ ሽር ጉዱን ተያይዞታል። የባክልስ ኩባንያን ፈተና ውስጥ ከትቶት የቆየው ግብዓት የኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን መለያ ተብሎ የሚታወቀው ጤፍ ነው።

የኔዘርላንድሱ ኩባንያ ከጤፍ የሚጋገር ዳቦን ለማምረት የወሰነው የዛሬ ሶስት ዓመት ግድም ነበር። ለዳቦ ምርቱ የሚለውን ግብዓትም የጤፍ ዱቄትን በኔዘርላንድስ በማከፋፈል ከሚታወቀው ሚሊቴስ ፕሌስ ከተሰኘው ኩባንያ ለመውሰድ ስምምነት ላይ ደርሶ እንቅስቃሴ ይጀምራል። ይሄኔ ባክልስ ያልጠበቀው ተግዳሮት ከፊቱ ይደቀናል። የባክልስ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሮናልድ ሜንቲንግ በወቅቱ የገጠማቸውን ያስረዳሉ።

“የባንክ አካውንቶቻችን አንሼይንት ግሬይን በተባለ ኩባንያ እንዲታገድ ተደረገ። አንሼይንት ግሬይን ጤፍን ተጠቅሟችኋል በሚል የከሰሰን ኩባንያ ነው። ጤፍን ለምርቶቻችን በግብዓትነት እንዳንጠቀም የሚከለክሉ ሁለት የባለቤነት መብቶች እንዳሏቸው አመልክተው ነበር” ይላሉ።  

አንሼይንት ግሬይን የጠቀሳቸው የባለቤትነት መብቶች እንዴት ለማግኘት እንደበቃ ለመረዳት 16 ዓመት ወደ ኋላ መጓዝ ግድ ይላል። ያኔ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በምህጻረ ቃሉ ኤስ ኤንድ ሲ ተብሎ ከሚታወቀው የኔዘርላንድስ ኩባንያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ይፈራረማል። ስምምነቱ የኔዘርላንዱ ኩባንያ በጤፍ ላይ ምርምር እንዲያደርግ እና ከጤፍ የሚመረቱ ውጤቶችን ለዓለም ገበያ እንዲያስተዋውውቅ የሚያስችለው ነበር። ይህን ተከትሎ 1440 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ 12 አይነት ዝርያ ያላቸው የጤፍ አይነቶች ለምርምር ወደ ለኔዘርላንድሱ ኩባንያ ተላከ፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ ከተፈጸመ ከአምስት ወር በኋላ፤ በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 2003፤ ኤስ ኤንድ ሲ ኩባንያ በጤፍ ላይ የባለቤትነት መብት (ፓተንት) ማመልከቻ ለሚመለከተው የኔዘርላንድስ መስሪያ ቤት ያቀርባል። ማመልከቻው በጤፍ ዱቄት እና ተያያዥነት ባላቸው ምርቶች አመራረት ላይ ኩባንያው በኔዘርላንድስ ብቸኛ የባለቤትነት መብት ያለው በመሆኑ ይሄው እንዲመዘገብለት የሚጠይቅ ነበር።

ስሙን ሄልዝ ኤንድ ፕርፎርማንስ ኢንተርናሽናል (HPFI) ወደሚል የቀየረው ኩባንያው ከአንድ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ማመልከቻ ለአውሮፓ የባለቤትነት መብት ጽህፈት ቤት አስገብቷል። ማመልከቻውን ሲመረምር የቆየው የአውሮፓው ጽህፈት ቤት በጎርጎሮሳዊው 2007 ዓ. ም. የጤፍ አዘገጃጀት ሂደት የባለቤትነት መብቱን በኩባንያው ስም መመዝገቡን አሳውቋል። ኩባንያው ኢትዮጵያን ገሸሽ አድርጎ የባለቤትነት መብት ጥያቄውን በአሜሪካ እና ጃፓን ለማስመዝገብም ጠይቋል።

HPFI ኩባንያ መክሰሩን አውጆ በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ. ም. ቢዘጋም የጤፍ የባለቤትነት መብት ጉዳይ በዚያው አልተዳፈነም። የባለቤትነት መብቱ የHPFI ኩባንያ ዳይሬክተሮች ከነበሩት ግለሰቦች ባንዱ ወደተቋቁመ አዲስ ኩባንያ መዛወሩ የታወቀው ከዓመታት በኋላ በመብት ጥሰት በፍርድ ቤት ክስ ሲመሰረት ነው። ያንስ ሮስጀን የተባሉት እኚህ ግለሰብ ያቋቁሙት ኩባንያ አንሼይንት ግሬይን ይባላል።

 

አንሼይንት ግሬይን የጤፍ የባለቤትነት መብቴ በሌላ የኔዘርላንድስ ኩባንያ ተጥሶብኛል በሚል ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ ባለ ችሎት ክስ የመሰረተው የዛሬ ሶስት ዓመት ግድም ነው። ኩባንያው ጤፍ ለሌላ ምርትነት እንዲውል በሚያስችለው የአዘገጃጀት ሂደት ላይ የፈጠራ ባለቤትነት መብት እንዳለው በክሱ ላይ ጠቅሷል። ጤፍን ከሌላ ማንኛውም እህል ጋር ለማደባለቅ የድርጅቱ ፍቃድ እንደሚያስፈልግ በክሱ ላይ ያመለከተው ኩባንያው ሆኖም ቤክልስ የተሰኘው ድርጅት ይህን ተላልፎ ተገኝቷል ሲል ወንጅሏል።

ጉዳዮን ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤት ባለፈው ህዳር 12 ቀን 2011 ዓ. ም. በዋለው ችሎት ተከሳሽን በነጻ እንዳሰናበታቸው  የቤክልስ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሮናልድ ሜንቲንግ ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ አንሼይንት ግሬይን ያቀረባቸውን ሁለት የጤፍ የባለቤትነት መብቶች “ህጋዊ አይደሉም” ሲል ውሳኔ ማስተላለፉንም ገልጸዋል። “ውሳኔው አንሼይንት ግሬይን ያቀረባቸው ክርክሮች መሰረት አልባ ሆነው ተገኝተዋል የሚል ነው። በዚህ አካሄድ የአንሼይንት ግሬይን የባለቤትነት መብት ህጋዊ ያልሆነ ነው ማለት ነው” ሲሉ ውሳኔውን ያብራራሉ። 

ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ የአንሼይንት ግሬይን ሰዎች “የባለቤትነት መብቶቹን ላይጠቀሙባቸው ይችላሉ” ሲሉም ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ግምታቸውን ተናግረዋል። ለዚህም የድርጅታቸው ጠበቆች የፍርድ ውሳኔውን ለማስፈጸም በተንቀሳቀሱበት ወቅት ያጋጠማቸውን በምሳሌነት አንስተዋል። አንሼይንት ግሬይን ባቀረበው ክስ በመረታቱ የተከላካይ ወገን ለፍርድ ሂደት ያወጣውን ወጪ እንዲከፍል እንደተወሰነበት አስታውሰው ነገር ግን ጠበቆቻቸው ከድርጅቱ ምንም ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ተከሳሹ የቤክልስ ኩባንያ እና ሚሌትስ ፕሌስ የተሰኘው አጋር ድርጅቱ ለፍርድ ሂደቱ ያወጡት 130 ሺህ ዩሮ “ባክኖ ቀርቷል” ብለዋል።

የጤፍ አዘገጃጀት ሂደት የባለቤትነት መብት አለኝ የሚለው አንሼይንት ግሬይን በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የማለት መብት ቢኖረውም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ይግባኝ የማስገቢያ ቀነ ገደቡ መጠናቀቁን ተከትሎ የቀድሞው የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር እና በቅርቡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አቶ ፍጹም አረጋ ደስታቸውን በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። አቶ ፍጹም የፍርድ ቤቱ ውሳኔን “ለኢትዮጵያ ድል” መሆኑን መግለጻቸው በርካቶች “ኢትዮጵያ ተነጥቃው የነበረው የጤፍ የባለቤትነት መብት ተመለሰላት” እንዲሉ አድርጓቸዋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ግን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከኢትዮጵያ የጤፍ የባለቤትነት መብት ጉዳይ ጋር እንደማይገናኝ ጠቅሰው በርካቶች የተቀባበሉትን መረጃ አስተባብለዋል። ጠቅላይ አቃቤ ህጉ “ኢትዮጵያ መብቷን ለመጠየቅ ዝግጅቷን መጨረሷን” ጠቅሰው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመሟገትም የህግ ድርጅት መመደቧን አስታውቀዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የጠቅላይ አቃቤ ሕግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም “ገና መረጃ እያጠናቀርን ነው” የሚል ምላሽ ከመስጠት በዘለለ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ኢትዮጵያ የጤፍ የባለቤትነት መብትን ለማስመለስ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተካተቱበት ኮሚቴ አዋቅራ መንቀሳቀስ ከጀመረች ቆይታለች። የኢትዮጵያ የአእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤትም ለኮሚቴው ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ሲሳሳተፍ ነበር። በጽህፈት ቤቱ ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ወርቅነህ የመስሪያ ቤታቸውን ተሳትፎ እና የነበረውን እንቅስቃሴ በአጭሩ ያስረዳሉ።

አቶ ብሩክ ዘሄግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ “ለኢትዮጵያ ይጠቅማል” ይላሉ። ኢትዮጵያ የጤፍ አዘገጃጀቱ ሂደት በባለቤትነት መብት በተመዘገበበት በኔዘርላንድስም ሆነ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ተመሳሳይ ክስ ብትመሰርት ኖሮ እንዴት ትጠቀም እንደነበር ያብራራሉ። አንሼይንት ግሬይን የተባለው ድርጅት የጤፍ የአዘገጃጀት የፈጠራ የባለቤትነት መብት በፍርድ ቤት ውድቅ በመደረጉ ኢትዮጵያ  የጤፍ የባለቤትነት መብትን የምታገኝበት አግባብ እንደሌለ ግን ጊዜያዊ ዳይሬክተሩ ያስገነዝባሉ።

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic