አወዛጋቢው የኮንጎ ሪፓብሊክ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት | አፍሪቃ | DW | 31.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አወዛጋቢው የኮንጎ ሪፓብሊክ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት

በኮንጎ ሪፓብሊክ የመምረጥ መብት ካለው ሕዝብ መካከል 92 ከመቶው ፕሬዚደንት ሳሱ ዴኒ ንጌሶ ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን መወዳደር እንዲችሉ እና ለፕሬዚደንትነት የሚወዳደረው እጩ ዕድሜም ከ70 መብለጥ የለበትም በሚል አርፎ የነበረው ገደብ እንዲሰረዝ በሕገ-መንግሥቱ ላይ ይደረጉ የተባሉትን ማሻሻያ አንቀጾች ባለፈው እሁዱ ሕዝበ ውሳኔ ደገፉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:20
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:20 ደቂቃ

የኮንጎ ሪፓብሊክ ሕዝበ ውሳኔ

ፕሬዚደንት ሳሱ ንጌሶ ይህችኑ 4,5 ሚልዮን ህዝብ ያላትን የማዕከላይ አፍሪቃ ሃገር እአአ ከ1997 ዓም ወዲህ በመምራት ላይ ይገኛሉ። በአፍሪቃ ለብዙ ዓመታት በርዕሰ ብሔርነት ስልጣን ላይ ከሚገኙት መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የ71 ዓመቱ ሳሱ ንጌሶ እአአ ከ1979 እስከ 1992 ዓምም ፣ በምርጫ ተሸንፈው እስከወረዱበት ጊዜ ድረስ ሃገሪቱን በፕሬዚደንትነት መርተዋል፣ ከዚያ ላጭር ጊዜ በሃገሪቱ የተካሄደው የርስበርስ ጦርነት እአአ በ1997 በኋላ እንደገና ወደሃገር መሪነቱ ስልጣን በመመለስ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሁለቴ ምርጫ አሸንፈዋል።

አሁን በህገ መንግሥቱ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ሳሱ ንጌሶ በሚቀጥለው አውሮጳዊ ዓመት በኮንጎ ሬፓብሊክ በሚደረገው ምርጫ ላይ ለተጨማሪ የሰባት ዓመት ዘመነ ስልጣን ማሸነፍ የሚችሉበትን መንገድ እንዳመቻቸላቸው ተመልክተውታል።

በኮንጎ ሬፓብሊክ ሁለቱ ዋነኛ የተቃዋሚ ቡድኖች፣ የሕገ መንግሥት እና ዴሞክራሲ አስከባሪ ግንባር እና ለኮንጎ ዴሞክራሲ መዳበር የሚጥረው ፓርቲ የሬፈረንደሙን መደረግና እና ውጤቱን አንድ ከፍተኛ የተቃዋሚው ቡድን አባል ሕገ ወጥ ሲሉ አጣጥለውታል።

« የጥቅምት 25፣ 2015 ዓም ሬፈረንደም ነፃም፣ ትክክለኛምአልነበረም፣ እንዲያውም፣ ሕገ ወጥ ነው። በዚህም የተነሳ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሚደረገውን ለውጥ የሚቃወሙት ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ኃይላት የሬፈረንደሙን ውጤት አይቀበሉትም፣ »

ቀደም ሲል መራጩ ሕዝብ ከሬፈረንደሙ እንዲርቅ ጥሪ ያስተላለፉት ሁለቱ ፓርቲዎች የሃገራቸው መንግሥት ፕሬዚደንቱ ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን እንዲቆዩ ያስቻለውን በሕገ መንግሥቱ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ እንዲሽር ግፊት ለማሳረፍ ሃገር አቀፍ ተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል።

ለንደን የሚገኘው «ቻተም ሀውስ» የሚባለው የብሪታንያውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ክፍል ተንታኝ ፖል ሜሊ ግልጽነት የጎደለው ሬፈረንደም ለገዢው መንግሥት ያደላ ነው በሚል የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት በጥርጣሬ ነው የተመለከቱት።

«በአጠቃላይ ሲታይ መንግሥት የምርጫውን ሂደት በሚቆጣጠርበት በዚችው ሃገር የሬፈረንደሙ ውጤት ልክ እንደተጠበቀው ነው የሆነው። በሃገሪቱ እአአ ከ2002 ዓም ወዲህ እንደተካሄዱት ሌሎች ምርጫዎች ሁሉ ያሁኑም ምርጫ ለቁጥጥር ክፍት ያልነበረ እና ለተቃዋሚዎች ጥሪ ንዑሱን ትኩረት ብቻ የሰጠ እና ለገዢው መንግሥት ያደላ ነው። ተቃዋሚዎች የመራጩ ሕዝብ ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን ቢናገሩም፣ መንግሥት በአንፃራቸው ተሳትፎው ከፍተኛ እንደነበር ነው የገለጸው፣ስለዚህ የምርጫው ውጤት ሌላ ቢሆን ኖሮ ነበር የሚያስደንቀው።»

Wahlen im Kongo: Menschenschlange vor Wahllokal in Brazzaville Flash-Galerie

ይሁንና፣ መንግሥት በይፋ ያቀረበውን ውጤት ማጣራት የሚቻልበት መንገድ እንደሌለ እና ብዙው የኮንጎ ዜጎችም የሬፈረንደሙን ሂደት በሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ ሙከራ አድርገው እንዳላዩት ፖል ሜሊ አስረድተዋል።

«የምርጫው ሂደት በጣም ቁጥጥር የበዛበት በመሆኑ ብዙዎቹ የተቃዋሚ ቡድን ደጋፊዎች በምርጫው መሳተፉ ፋይዳ ያመጣል ብለው አያስቡም። እአአ የ2009 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫን ብንወስድ፣ የመራጭ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር እና ለፕሬዚደንቱ ትልቅ ድል እንዳስገኘ የሚያሳይ ይፋ መግለጫ ወጥቶ ነበር። ይሁንና፣ ከምርጫው ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ ውስጥ ብዙዎቹ የተቃዋሚው ወገን እጩዎች መሳተፋ አይችሉም በሚል የአስመራጩ ኮሚሽን ባለስልጣናት እጩነታቸው ሰርዘውባቸዋል። የመራጭ ተሳትፎን በተመለከተ መንግሥት ያቀረበው ቁጥርም ቢሆን ገሀዱን በፍፁም የማያንፀባርቅ ነው። እና መራጩ የኮንጎ ሕዝብ ይህ በሃገሪቱ ታሪክ አዲስ ያልሆነው አሰራር ለውጥ አያስገኝም ብሎ በማሰቡ በምርጫው ያለለመሳተፉን አዝማሚያ ነው የያዘው።»

የአውሮጳ ህብረትም የኮንጎን ሬፈረንደም ተዓማኒ ነው ብሎ እንደማይመለከተው ከምርጫው ሂደት በኋላ አስታውቋል።

በሕገ መንግሥቱ ተቀምጠው የነበሩት የፕሬዚደንቱን ዘመነ ስልጣን እና የመወዳደሪያ ዕድሜ ገደብ አሁን በመነሳታቸው እአአ በ2016 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የሚወዳደሩት ፕሬዚደንት ዴኒ ሳሱ ንጌሶ ፣ የሃገሪቱ የምርጫ ታሪክ እንደሚያሳየው፣ ማሸነፋቸው እንደማይቀር ይጠበቃል። ይሁንና፣ ይህ፣ ይላሉ የ«ቻተም ሀውስ» የፖለቲካ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ክፍል ተንታኝ ፖል ሜሊ ቀላል ይሆናል ብሎ በርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

«ምክንያቱም ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆኑት አፍሪቃውያት ሃገራት በወቅቱ በለውጥ ሂደት ላይ ነው የሚገኙት። እርግጥ፣ ብዙው ለውጥ የሚታየው ዴሞክራሲያዊውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ተክለው መንቀሳቀስ በጀመሩት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ነው። ያም ቢሆን ግን፣ ይኸው የለውጥ ሂደት በሌሎቹ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አፍሪቃውያት ሃገራትም ላይ ሰፊ ተፅዕኖ አሳርፏል።»

የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ በኮንጎ ሬፓብሊክ ባለፈው እሁድ የተደረገውን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት፣ ምንም እንኳን የሂደቱ ትክክለኛነት ወቀሳ ባያጣውም፣ ደግፋለች፣ ይኸው ድጋፏ ግን ማጠያየቁ ባይቀርም፣ ለዚሁ ውሳኔዋ የራሷ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችል ነው የ«ቻተም ሀውስ የአፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝ ፖል ሜሊ የሚገምቱት።

«እንደሚመስለኝ፣ እዚህ ላይ ሁለቱ ጉዳዮችን ልብ ልንል ይገባል። የመጀመሪያው፣ ፈረንሳይ በአፍሪቃ ፖለቲካዊ ተሀድሶ እንዲነቃቃ እና ስርዓተ ዴሞክራሲ እንዲተከል እያበረታታች ነው። ይሁንና፣ ይህንን ስታደርግ የአፍሪቃውያኑን የመወሰን ኃይል በማክበር ነው። በሌላ አነጋገር፣ እንደ አንድ ጣልቃ የሚገባ የውጭ ኃይል መታየት አትፈልግም። ይህም በተግባር ሲተረጎም፣ ስርዓተ ዴሞክራሲን በመትከሉ መንገድ ላይ እየተጓዙ ካሉ አፍሪቃውያት ሃገራት ጋር የሚታየው የፈረንሳይ ግንኙነት በጣም ቅርብ እና ድጋፍ የታከለበት ነው።»

በአፍሪቃ የሃገር መሪዎች በሕገ መንግሥቱ ከተወሰነው የስልጣን ዘመን በላይ በስልጣን መቆየት አለባቸው ወይ በሚል በአሁኑ ጊዜ ብርቱ ወቀሳ ከተፈራረቀባቸው በርካታ ሃገራት መካከል አንዷ የኮንጎ ሬፓብሊክ ናት። እንደሚታወሰው፣ የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ከጥቂት ወራት በፊት በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ በማስደረግ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን የተመረጡበት ድርጊት በሃገሪቱ የተነሳው ውዝግብ አሁንም ገና አልበረደም።

የጎረቤት ርዋንዳ ምክር ቤትም፣ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ እአአ በ2017 ዓም ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን መወዳደር የሚያስችላቸውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያን አፅድቆታል። ምክር ቤቱ ይህንኑ ረቂቅ ያፀደቀው የፕሬዚደንቱን የስልጣን ዘመን የሚገድበው የሕገ መንግሥት አንቀጽ 101 እንዲሻሻል የቀረበውን ሀሳብ ከ11,7 ሚልዮኑ የርዋንዳ ሕዝብ መካከል 3,5 ሚልዮኑ ከፈረሙት በኋላ ነው። ይኸው ማሻሻያ ወደፊት ለሕዝበ ውሳኔ የሚቀርብ ሲሆን፣ በቀላሉ ድጋፍ እንደሚያገኝ ብዙዎች ገምተዋል። እንደብዙዎቹ አፍሪቃውያን መሪዎች ስልጣናቸውን መልቀቅ አይፈልጉም ያላቸውን የፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ለተጨማሪ ዘመነ ስልጣን መወዳደርን በመቃወም የተቃዋሚው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ያስገባውን የክስ ማመልከቻ የርዋንዳ ላዕላይ ፍርድ ቤት ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ውድቅ አድርጎታል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic