አወዛጋቢው የእርዳታ ሠራተኞች ግድያ በደቡብ ሱዳን | አፍሪቃ | DW | 28.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አወዛጋቢው የእርዳታ ሠራተኞች ግድያ በደቡብ ሱዳን

ባለፈው ቅዳሜ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በ6 የእርዳታ ሠራተኞች እን ሾፌራቸው ላይ የተፈፀመው ግድያ እያወዛገበ ነው ። አማጽያን ለግድያው የደቡብ ሱዳን መንግስት ተጠያቂ ነው ሲሉ መንግሥት ደግሞ ከጥቃቱ በስተጀርባ ማን እንዳለ ለማወቅ ጊዜ ገና ነው እያለ ነው ።የተመድ ግድያው ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከል ነው ብሏል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:34

የእርዳታ ሠራተኞች ግድያ

 የዶቼቬለው ዋኬ ሲሞን ዉዱ ከጁባ የላከውን ዘገባ ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።

6ቱ የተመድ የእርዳታ ሠራተኞች እና ሾፌራቸው የተገደሉት ባለፈው ቅዳሜ ከጁባ ተነስተው 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው ወደ ፒቦር ከተማ በመጓዝ ላይ ሳሉ ነበር  ። ከተገደሉት የእርዳታ ሠራተኞች አራቱ ደቡብ ሱዳናውያን  ሦስቱ ደግሞ ኬንያውን ሲሆኑ ግሬዶ የተባለው አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሠራተኞች ነበሩ ። ፒቦር በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለች ከተማ ብትሆንም፣አማጽያን እና የመንግሥት ወታደሮች እንዲሁም በሚሊሽያዎች እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል ውጊያ ይካሄድባታል ። አማጽያን ግድያው የተፈፀመው መንግሥት በሚቆጣጠረው አካባቢ ስለሆነ ተጠያቂው መንግሥት ነው ይላሉ ። መንግስት በአሁን ደረጃ እውነቱ ሳይጣራ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም ሲል ይሟገታል ። በእርዳታ ሠራተኞች ላይ የተፈፀመው ግድያ በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ተጠሪ ኢያን ሪድሊ እንዳሉት በሀገሪቱ ሰዎችን ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት እያሰናከለ ነው ።

« ሊያደርስ የሚችለው ተጽእኖ የእርዳታ ሠራተኞች ለደህንነታችን ያሰጋል ብለው ወደ ነዚህ አካባቢዎች ላለመሄድ ከወሰኑ ለአካባቢው ህዝብ የሚያስፈልገውን ማድረስ አይቻልም ። አስፈላጊ

የሆኑ አቅርቦቶች ፍላጎት ሲጨምር የተጠናከረ ፀጥታ ያስፈልገናል ። አሁን ግን የምናየው ተቃራኒውን ነው ። »

ሪድሊ እንደሚሉት ባለፈው ቅዳሜ በእርዳታ ሠራተኞች ላይ የተፈፀመው ግድያ ፣መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡ የእርዳታ ሠራተኞችን ለመጠበቅ የሚያደርገው ጥረት እንደሌለ ማሳያ ነው  ። ሦስት ዓመት በዘለቀው የደቡብ ሱዳን ጦርነት ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች ግጭቱን እንዲያቆሙ እና በሀገሪቱ መረጋጋትን ለማስፈን እና ፀጥታም እንዲከበር ብቸኛው መፍትሄ ለሆነው ለሰላም እንዲጥሩ  ሃላፊው ጥሪ አቅርበዋል ። የተመ የሰብዓዊ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ደግሞ ግድያው የጦር ወንጀልንም ሊያካትት ስለሚችል እንዲጣራ እና ነፍሰ ገዳዮቹም እንዲከሰሱ ጠይቀዋል ።ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ደቡብ ሱዳንን የጎበኙት አዲሱ የአፍሪቃ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ሞሀመትም ጥቃቱን አውግዘው ፣ለእርዳታ ሠራተኞች ጥበቃ እንዲደረግ ጠይቀዋል ።

“ሰዎችን ሊረዱ በመጡ 6 የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኖች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በጥብቅ እናወግዛለን   ። መንግሥት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ችግር ውስጥ የወደቁ ደቡብ

ሱዳናውያንንለመርዳት እዚህ ለሚገኙት የእርዳታ ሠራተኞቹ ጥበቃ እንዲያደርጉላቸውም ጥሪ እናቀርባለን ። »

የደቡብ ሱዳን መንግሥት በበኩሉ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል ። በትክክል የሆነው ከታወቀ በኋላ መግለጫ እንደሚያወጣ  የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤልያ ሎሙሮ ተናግረዋል ።

«እንደ መንግሥት መረጃ አላገኘንም ። በጉዳዩ ላይ መግለጫ ከመስጠታችን በፊት በትክክል ምን እንደተፈፀመ ለማወቅ የደህንነት ወኪሎቻችን እያጣሩ ነው ። »

የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከጎርጎሮሳዊው 2013 ወዲህ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የተገደሉ የእርዳታ ሠራተኞች ቁጥር ወደ 80 ይጠጋል ። በቅርቡ ረሀብ ባወጀችው በደቡብ ሱዳን 100 ሺህ ሰዎች ለረሀብ አደጋ ተጋልጠዋል ። ያለፈው ሳምንት መጨረሻው ግድያ የእርዳታ ሠራተኞች እና መንግሥት  ሰው ሰራሽ የሚባለውን የደቡብ ሱዳን ረሀብ እንዴት ሊቋቋሙት ይችላሉ የሚለውን ጥያቄ አስነስቷል ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች