አወዛጋቢው የቦሪስ ጆንሰን የብሬግዚት እቅድ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 06.08.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

አወዛጋቢው የቦሪስ ጆንሰን የብሬግዚት እቅድ

የጆንሰን ግትር አቋም ከፓርቲያቸው አባላትም ተቃውሞ ገጥሞታል።ሦስቱ የብሪታንያ ግዛቶችም ጆንሰን ከህብረቱ ካለ ስምምነት እንዳይወጡ እያስጠነቀቁ ነው።ተቃዋሚዎችም ሃገራቸው ያለ ስምምነት ከህብረቱ መውጣትዋን ለማስቆም የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል ።ተቃዋሚው ሌበር ብሪታንያ ያለ ስምምነት ከወጣች መዘዙ ከባድ ነይሆናል ሲል አስጠንቅቋል።     

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:44

የቦሪስ ጆንሰን መርሕ

 

አዲሱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ያለ ስምምነትም ቢሆን ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት መውጣትዋ አይቀርም የሚለው አቋማቸው ማወዛገቡ ቀጥሏል። ብሪታንያ ያለ ስምምነት ከህብረቱ መውጣትዋን የሚቃወሙ የወግ አጥባቂ ፓርቲያቸው አባላት የጆንሰን እቅድ እንዳይሳካ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ እየዛቱ ነው።ሦስት የብሪታንያ ግዛቶችም በጆንሰን ሃሳብ አይስማሙም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም ተቃውሞው እና ውዝግቡ የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው።

ሥልጣን ከያዙ ሁለት ሳምንት የሆናቸው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት እንድትወጣ ከፍተኛ ዘመቻ እና ጥረት ሲያደርጉ ከቆዩት ፖለቲከኞች አንዱ እና ዋነኛው ነበሩ።ምኞታቸው ተሳክቶም ከአውሮጳ ህብረት ጋር የመቆየት አለያም ህብረቱን ለቆ የመውጣት ማለትም (የብሬግዚት) ምርጫ የተሰጠው የብሪታንያ ህዝብ ባካሄደው ህዝበ ውሳኔ በጠባብ ልዩነት ብሬግዚትን ከመረጠም ሦስት ዓመት አልፏል።በዚህ ጊዜ ውስጥም ከተከወኑት ጉዳዮች መካከል ብሪታንያ ከህብረቱ አባልነት የምትወጣበት ውል ላይ የተደረሰው ስምምነት ይገኝበታል።ከህዝበ ውሳኔው በኋላ እስከ ዛሬ 15 ቀን ድረስ የቀድሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት የቴሬሳ ሜይ መንግሥት፣ ከህብረቱ ጋር የተስማማበትን ይህን ውል ግን የብሪታንያ ፓርላማ ይሻሻል ሲል በተደጋጋሚ ውድቅ በማድረጉ ሜይ በቅርቡ ከሥልጣናቸው ለመሰናበት ተገደዋል።በብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ሊቀመንበርነት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት

ሜይን የተኩት ቦሪስ ጆንሰንም ይህ ውል ይሻሻል ከሚሉት አንዱ ናቸው።ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ በእቅዱ መሠረት በተያዘው ቀን ገደብ ማለትም በጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 31፣2019 ወይም ጥቅምት 20፣2012 ዓም ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ መውጣትዋ እንደማይቀር ነው ደጋግመው የሚናገሩት።ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ለሃገሪቱ ፓርላማ ብሬግዚትን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ማሳካት ሃገሪቱን ለማበልጸግ መንገድን ይጠርጋል ሲሉ ራዕያቸውን ገልጸዋል።

«የኛ ተልዕኮ ታላቂቷን ብሪታንያን አንድ ለማድረግ ፣ ዳግም ኃያል እንድታገኝ እና በምድር ላያ ካሉ ሃገራት ታላቅ ስፍራ እንድትሆን ብሬግዚትን በጎርጎሮሳዊው ኦክቶበር 31 ገቢራዊ ማድረግ ነው። አንዳንዶች የተጋነነ ነው ሲሉ እኔን ሊወቅሱ እንደሚችሉ አውቃለሁ።ሆኖም አሁን የምንሄድበትን መንገድ መገመቱ ጠቃሚ ነው። እኛ ባስተዋወቅነው በአዲሱ የንግድ መረብ ውሎች ብሪታንያ በ2050  በአውሮጳ ግዙፍ እና እጅግ የበለፀገ ኤኮኖሚ የሚኖራት ሃገር የበለፀገ ኤኮኖሚ የሚኖራት ሃገር መሆንዋ ጥያቄ የማያስነሳ ነው።»

ብሬግዚት ገቢራዊ እንዲሆን የሚፈልጉበትን ምክንያት በዚህ መንገድ ያስቀመጡት ቦሪስ ጆንሰን ፣የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ከአውሮጳ ህብረት ጋር የተስማሙበት የብሬግዚት ውል እንዲሻሻል ይፈልጋሉ።በቅርቡ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የመንግሥታቸው ዓላማ  ከአውሮጳ ህብረት ያለ ስምምነት መውጣት እንዳይደለ ፣ይህም የሃገሪቱ መጨረሻ ይሆናል ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል።ሆኖም እንደ ጆንሰን ይህ የሚወሰነውም ከባህሩ ባሻገር የሚገኙ ባሏቸው ወዳጆቻችው እና አጋሮቻቸው ፍላጎት  እንደሆነ አስረድተዋል።

«የብሪታንያ ምክር ቤት ሦስት ጊዜ የተቃወመው ከብሬግዚት በኋላ በተለይ በሰሜን አየርላንድ እና በአየርላንድ ሪፐብሊክ ድንበር ላይ የላላ ቁጥጥር እንዲካሄድ የተደረሰበትን ስምምነት ነው።በምንም ዓይነት ይህን ልናካትት አንችልም።ይህን የውሉን ክፍል የግድ ማስወጣት አለብን።አሁን ባለው ህብረቱን ለቆ የመውጣት ስምምነት ልንቀጥል አንችልም።የሞተ ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ይረዳል።ይህን መልዕክት ለወዳጆቻችን ማድረስ ይገባናል።ከተረዱልን ውድድሩ ውስጥ የምንገባ ይመስለኛል።አግባቢ ሃሳብ ካላመጡ በግልጽ ያለ ስምምነት ህብረቱን ለቆ ለመውጣት መዘጋጀት አለብን።እና እንደሚመስለኝ እናደርገዋለን።»

የአውሮጳ ህብረት ከብሪታንያ ጋር የተስማማበት የብሬግዚትን ውል ሊሆን የሚችል የተሻለው ስምምነት መሆኑን ገልጾ ውሉ ለድርድር እንደማይቀርብም አስታውቋል።ሆኖም ከብሪታንያ ጋር ለመነጋገር ግን ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል። የህብረቱ ቃል አቀባይ ትናንት እንዳሉት የህብረቱ ኮሚሽን ከጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነው።ህብረቱ ይህን ቢልም ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን በበኩላቸው ተደራዳሪዎች የሰሜን አየርላንድን ድንበር የተመለከተውን የውሉን ክፍል ለማውጣት ፈቃደኛ እስካልሆኑ ድረስ አዲስ ንግግር ማካሄዱ ምንም ትርጉም አይሰጥም ሲሉ ከዚህ ቀደም አስታውቀዋል።ይህ የጆንሰን ግትር የሚመስል አቋም ከፓርቲያቸው አባላትም ተቃውሞ ገጥሞታል።ሦስቱ የብሪታንያ ግዛቶችም ጆንሰን ከህብረቱ ካለ ስምምነት እንዳይወጡ እያስጠነቀቁ ነው።የለነደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነህ እንደሚለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ከየአቅጣጫው ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።

ተቃዋሚዎችም ሃገራቸው ያለ ስምምነት ከህብረቱ መውጣትዋን ለማስቆም የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ እያስጠነቀቁ ነው።የብሪታንያ ተቃዋሚ ፓርቲ የሌበር ሊቀ መንበር ጀርሚ

ኮርቢን የጆንሰንን አካሄድ ኮንነው ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ያለ ስምምነት ከወጣች መዘዙ ከባድ እንደሚሆንም አስጠንቅቀዋል።     

«ያለስምምነት ህብረቱን ለቆ መውጣትን ለማስቀረት በተገቢው እና በጣም ቀደም ባለ ጊዜ ያለመተመ,ኛ ድምጽን ጨምሮ ሁሉንም ነገር እናደርጋለን።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለ ስምምነት ለመውጣት የመንሸራተት ሙከራ እያደረጉ ይመስላል።ከፓርላማው የመንሸራተት፤ ከብሪታንያ ህዝብ የመንሸራተት።አዝናለሁ ያለ ስምምነት መልቀቅ በእውነት ከባድ ነው።ለምግብ ዋጋ፣ ለመድኃኒት አቅርቦት፣ ለንግድ ለውረታ ከባድ ነው።እናም ይህ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቦሪስ ጆንሰን ጋር ሊያካሂዱ ወደ ሚፈልጉት ንግድ እጅ ውስጥ ሰተት አድርጎ የሚወስድ ነው የሚሆነው።»

ድልነሳው እንደሚለው የንግዱ ማህበረሰብም ስጋትም ከቀድሞው አሁን ይበልጥ ጨምሯል።ታዲያ በዚህ ሁሉ ተቃውሞ የተከበቡት አዲሱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን

ብሪታንያን ከህብረቱ ያለ ስምምነትም ቢሆን ለማስወጣት የያዙት እቅድ ታዲያ እንዴት ይሳካላቸው ይሆን? ድልነሳው

ድልነሳው እንደሚለው ይህም ቢሆን ለርሳቸው ጥሩ እድል ይዞ የሚመጣ አይሆንም።ምናልባትም ሥልጣናቸውንም ሊያጡ ይችላሉ።

ከዚህ ሌላ በቅርቡ ብሬከል እና ኢንደርሸር በተባለ አካባቢ በተካሄደ የሟሟያ ምርጫ የጆንሰን ፓርቲ መሸነፉ፣ፓርቲያቸው በፓርላማው የነበረው አብላጫ ድምጽ እንዲቀንስ ማድረጉም ለጆንሰን ተጨማሪ ችግር ሆኗል ይላል ድልነሳው።

ጆንሰን ብሬግዚትን ያለ ስምምነትም ቢሆን በጥቅምት 20 2012፣ተግባራዊ አደርጋለሁ ብለዋል።መሰናክሉን አልፈው ይህን እቅዳቸውን ማሳካት አለማሳካታቸው የሚታወቀው እንግዲህ ከ2 ወር በኋላ ነው። አብረን የምንሰማው የምናየው ይሆናል።   

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic