አኽመድ ማሃዲ በ«ICC» ተፈረደበት | ባህል | DW | 22.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

አኽመድ ማሃዲ በ«ICC» ተፈረደበት

አኽመድ ኧል ፋቂ ኧል ማሃዲ የተባለ የፅንፈኞች መሪ በሰሜን ማሊ ቲምቡክቱ በዓለም ቅርስ የተመዘገቡ ቅርሶችን በማዉደሙ ዛሬ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ የጥፋተኝነት ብይን ተላለፈበት። ይህ አይነት ክስ በፍርድ ቤቱ ሲቀርብና ብይን ሲሰጥ ዛሬ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ።በሰሜናዊ ማሊ የሚንቀሳቀሰዉና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለዉ የሚነገረዉ አንሳር ዲን የተባለዉ ፅንፈኛ ቡድን መሪ አኽመድ ኧል ፋቂ ኧል ማሃዲ ዛሬ ዴንሃግ ኔዘርላን በሚገኘዉ ዓለም አፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ፤ ክሱን በጥልቅ ኃዘኔታ ማመኑ ተዘግቦአል። አኽመድ ኧል ፋቂ ኧል ማሃዲ ወንጀሉን ካመነ በኋላ የማሊን ማኅበረሰብ ይቅርታ መጠየቁም ተመልክቶአል። በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም ኧል ማሃዲ በቲምቡክቱ የሚገኝ ዘጠኝ ጥንታዊ መቃብር ቤቶችንና አንድ መስጊድን ለማዉደም ጽንፈኞችን አደራጅቶአል በሚል ነበር ክስ የተመሰረተበት። በጥንታዊዋና ንግድ ማዕከል በነበረችዉ ቲምቡክቱ ዉስጥ በመካከለኛዉ ክፍለ ዘመን የታነፀ ታሪካዊ ቅርስ ሲወድም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጣና ሃዘንን ማስነሳቱ ይታወሳል። በሰሜን ማሊ ሰሐራ ምድረ በዳ ጫፍ ላይ የምትገኘው በቲምቡክቱ፤ ከመቶ ዓመታት በላይ የእስላም ዋንኛ ባህላዊ ማዕከል ሆና መቆይትዋ ይታወቃል። ዛሬ ለፍርድ ችሎት የቀረበዉ የፅንፈኛዉ አንሳር ዲን ቡድን መሪን ለፍርድ ያቆሙት የከሳሾች ዋና ተጠሪ ፋቱ ቤንሱዳ ወንጀሉ በማኅበረሰቡ ክብርና ማንነት ላይ የተቃጣ የፈሪ ጥቃት ሲሉ ተናግረዋል።


አዜብ ታደሰ


አርያም ተክሌ