አካለ ጉዳተኛው ብርቱ ጦረኛ፤ ሱንጃታ ኬታ | አፍሪቃ | DW | 26.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አካለ ጉዳተኛው ብርቱ ጦረኛ፤ ሱንጃታ ኬታ

አካለ ጉዳተኛ ኾነው ቢወለዱም ኋላ ላይ ብርቱ ጦረኛ ወጥቷቸዋል ይላል አፈ ታሪክ። በአንድ ወቅት ለግዞት ቢዳረጉም ጠንካራ ጦር ይዘው ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል ሲል ይቀጥላል። የማንዲንጎ ጎሦችን በማዋሀድ በመካከለኛው ክፍለ-ዘመን በምዕራብ አፍሪቃ ሰፊውና እጅግ ኃያሉ የማሊ ንጉሣዊ ግዛትን የመሰረቱት አንበሳው የሚባሉት ንጉሥ ሱንጃታ ኬታ ይባላሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:26

አንበሳው ንጉሥ ተብለው ይቆላመጡ ነበር

አካለ ጉዳተኛ ኾነው ቢወለዱም ኋላ ላይ ብርቱ ጦረኛ ወጥቷቸዋል ይላል አፈ ታሪክ። በአንድ ወቅት ለግዞት ቢዳረጉም ጠንካራ ጦር ይዘው ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል ሲል ይቀጥላል። የማንዲንጎ ጎሦችን በማዋሀድ በመካከለኛው ክፍለ-ዘመን በምዕራብ አፍሪቃ ሰፊውና እጅግ ኃያሉ የማሊ ንጉሣዊ ግዛትን የመሰረቱት አንበሳው የሚባሉት ንጉሥ ሱንጃታ ኬታ ይባላሉ።

በሉ አድምጡ የማንዲንጎ ልጆች፤ የጥቁር ሕዝቦች ልጆች አድምጡ… የጀግንነት ገድላቸው ስለተነገረላቸው ሱንጃታ የምላችሁን አድምጡኝ። ከረዥም ጊዜ አንስቶ ጀግንነታቸው የሰው ልጆችን ስላስደነቀው ብርቱ ሰው የምነግራችሁን አድምጡኝ…

ይኽ ጊሮስ የተሰኙት የምዕራብ አፍሪቃ ተራኪዎች አንበሳው በሚል ስለሚንቆለጳጰሱት ንጉሥ ሱንጃታ ኬታ የጥንት ታሪክ መተረክ ሲጀምሩ የሚንደረደሩበት ነው። ከትውልድ ትውልድ በቃል ሲነገር፤ ሲወርድ ሲዋረድ እዚህ ደርሷል።

በ13ኛው ክፍለ ዘመን መንደርደሪያ ሱንጃታ ኬታ የማንዲንጎ ማኅበረሰብን ሰበሰቡ ይላል ገድለ-ታሪኩ። ንጉሣዊ ግዛታቸው በሌሎች ጎሳዎች ተወሮ ነበር። እናም ሱንጃታ የጎሣ አለቃዎችን ወደ ጦርነቱ መርተው ድል አድርገዋል። ይኽ ድል የማሊ ንጉሣዊ ግዛት መጀመሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። ንጉሣዊ ግዛቱ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት ከምዕራብ አፍሪቃ የባሕር ጠረፍ  እስከ ኒጀር ወንዝ 2,000 ኪሎ ሜትር የመሬት ይዞታዎችን ያካተተ ነበር። ግዛቱ ከዚያም ያለፈ ነበር የሚሉ አሉ። ግዛቱ የተለያዩ ጎሳዎችን ያዋሃደ ነበር ይላሉ ማሊ ውስጥ የሚገኘው የባማኮ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ሴይዶ ካማራ።

የማንዲንጎ ሥርወ-መንግሥትን አዋህደዋል። ማንዲንጎ የተለያዩ ጎሣዎች የሚገኙበት፤ የትራኦሬ፣ የኪዬታ፣ የካማራ፣ የኮኔ እና የመሳሰሉት ጎሳዎች የተዋሃዱበት ንጉሣዊ አገዛዝ ነበር። ሱንጃታ በንጉሣዊ አገዛዙ ሠላምን አስፍነዋል፤ ታላቅ ንጉሣዊ ግዛትንም ነው የመሠረቱት፤ እጅግ ሰፊ፣ የሠለጠነ፣ የተዋሃደ፣ ጠንካራ እና በሐብት የበለጸገ ንጉሣዊ ግዛት። ይኽ የሱንጃታ ሕልም ነበር፤ ተግብረውታልም።  

በ20 ዓመት አገዛዛቸው ሱንጃታ የእርሻ ሥራን ከፍ አድርገው፤ የጨው እና የወርቅ ንግድን በመቆጣጠር ማሊ ሐብታም እና ኃያል እንድትኾን ረድተዋል። በመአከላዊነት የተደራጀ መንግሥት አዋቅረው የባርያ ሥርዓትን ከልክለዋል ይላሉ ሴዶ ካማራ።  

ስለ ሕይወት በአጠቃላይ ይጨነቁ ነበር። ተፈጥሮን ለመንከባከብ፤ የማኅበረሰቡን እሴት ለመጠበቅ ተግተዋል።  ስለ ሴቶች፣ ስለ የውጭ ዜጎች፤ ስለ መብት እና ግዴታም ሕግጋትን አስተግብረዋል። 

የሱንጃታ ታሪክ ተቀናቃኞቻቸውን ድል በማድረግ ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም። የግላቸውን ተግዳሮት ድል ማድረግንም ያካትታል። የንጉሥ ልጅ የነበሩት ሱንጃታ ሲወለዱ አካል ጉዳተኛ ኾነው ነው። አንድ ቀን ግን ቆመው መራመድ ችለዋል። በአንድ በኩል በቁርጠኝነት በሌላ መልኩ ደግሞ በድግምት ይላል ገድለ-ታሪካቸው ። እነሆ ለመጀመሪያ ጊዜ የተራመዱት የአንበሳው ንጉሥ ሱንጃታ ገድለ-ታሪክ። 

ትንፋሻቸው መለስ ሲል የንጉሡ ልጅ ምርኩዛቸውን ወዲያ ጣሉ። ተሰብስቦ የነበረው ሀገሬው በንጉሡ የመጀመሪያ ርምጃ እጅግ ተደመመ። እናም አጀቡ ገለል በሉ፤ ገለል በሉ አንበሳው እየተራመዱ ነው ሲል ጮኸ። 

በሱንጃታ ታሪክ እውነታን ከልብወለድ መለየት ይከብዳል። በአብዛኛው ከዓረብ ነጋዴዎች የተገኙ የጽሑፍ መረጃዎች ሱንጃታ ኬይታ በእውን የነበሩ ሰው ስለመኾናቸው ያረጋግጣል። ኾኖም እነዚህ ምንጮች ስለ ሕይወታቸው ብዙም አይተርኩም። በቃል የተነገሩት ታሪካቸው ደግሞ በተወሰነ መልኩ ለማመን የማይቻሉ እንደኾኑ ሴይዶ ካማራ ይጠቅሳሉ።   

ታሪክ ከትውስታ ማኅደር የሚገኝ ነው። ትውስታ ደግሞ በቀላሉ ሊዛባ ይችላል፤ የቃል ትርክቱ ልማድ በበኩሉ የበርካታ ምዕተ ዓመታት ክስተቶችን የአንድ ክፍለ ዘመን ብሎም የአንድ ግለሰብ አድርጎ ሊያተረማምሳቸው ይችላል። ይኽ የሥነ-ቃል ችግሩ ነው።.

የማሊ ንጉሣዊ ግዛት እስከ 1550 ድረስ ተመንድጓል፤ ከዚያም የፖለቲካ ጥንካሬው ቀስ እያለ መዳከም ጀመረ። እጅግ ጠቃሚ ከተሞችን የአነስተኛ ግዛት አማጺያን እና ከጎረቤት የሚገኙ ቡድኖች ተቆጣጠሩ። ንጉሳዊ ግዛቱ ተንኮታኮተ።  

ኾኖም እድሜ ለግሮይትስ ትውስታዎች ሱንጃታ ኬይታ ዛሬም ይዘከራሉ።

((ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።))

ታማራ ዋኬርናግል/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

 ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

Audios and videos on the topic