አከራካሪው ፣ የአፍሪቃ የማደጎ ህጻናት ጉዳይ፣ | ኢትዮጵያ | DW | 11.10.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

አከራካሪው ፣ የአፍሪቃ የማደጎ ህጻናት ጉዳይ፣

አፍሪቃውያን ህጻናት፣ በማደጎ ሥም፣ ወደ ምዕራቡ ዓለም መጋዛቸው፣የብሩኅ ተስፋ እውንነት ወይስ ዐይን ያወጣ ብዝበዛ!? በአሁኑ ጊዜ፣ ማሳደግ ለሚችሉ ባዕዳን ፣ ልጆቻቸውን ለጉድፈቻ የሚሰጡ አፍሪቃውያን ወላጆች ቁጥር እጅግ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።

default

ታዋቂዋ ድምፃዊት፣ ማዶና፣ ከማላዊ በማደጎ የወሰደችው ልጅ፣

አፍሪቃውያኑ ይህን የሚያደርጉት፣ ድኅነት ክፉኛ ስለሚያጎሳቁላቸው እንጂ ፍቅር በማጣት አይደለም። ይሁንና፣ ልጅን ከወላጆቹ ነጥሎ፣ ባህሉ፣ ቋንቋው፣ የአየሩም ጠባይ የተለየ ወደሆነበት ሩቅ አህጉር እንዲወሰድ ማድረግ፣ ጥቅሙና ጉዳቱ እንዴት ይታያል? የዶቸ ቨለ ባልደረባ፤ ጄን አየኮ ያቀረበችውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ (ድምፃዊት)ማዶና፣ከማላዊ አንድ ልጅ ለማሳደግ መውሰዷ ብቻ ሳይሆን፣ ልጁ ወላጆቹን በሞት ያጣ አለመሆኑ መታወቁ ዓለም-አቀፍ መገናኛ ብዙኀንን አንድ ሰሞን ማነጋገሩና ወቀሳም ማስከተሉ የሚታወስ ነው። ማዶና በበኩሏ፣ ለልጁ የሚበጅ የወደፊት ህይወቱንም ብሩኅ የሚያደርግ እርምጃ ነው የወሰድሁ ስትል መከራከሯም አልቀረም። ልጅ ማግኘት የተሣናቸው ምዕራባውያን ባለትዳሮች፣ በጉድፈቻ የሚያሳድጓቸውን ህጻናት ፍለጋ ፊታቸውን ይበልጥ ያዞሩት ወደ አፍሪቃና እስያ ሆኗል። ከአፍሪቃ ደግሞ፣በአንደኛ ደረጃ፣ ወደ ዩናይትድ እስቴትስ፣ አውስትሬሊያና የተለያዩ ምዕራባውያን አገሮች በብዛት የሚወሰዱት ፤ ኢትዮጵያውያን ህጻናት ሆነዋል። Save the Children የተሰኘው የደንማርክ ድርጅት ፣ የኢትዮጵያው ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሱዛነ ክሪስቲያንሰን፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማደጎ እንዲሰጡ፣ ሲወተወቱ ማየታቸውን ጭምር ይናገራሉ።

«ህጉን አያውቁትም። ልጆቻቸው ምን እንደሚደርስባቸው እምብዛም አያሰላስሉም። አብዛኛውን ጊዜ ከችግሩ መንዛዛት የተነሣ ያን ያህል ሳያንገራግሩ የሚሰጣቸውን ገንዘብ በመቀበል ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እንደተደመደመ ነው የሚያስቡት።»

ልጆች ላሏቸው ቤተሰቦችና እርዳታም ለሚያሻቸው ድጎማ የማይሰጥ መንግሥት ባለበት አገር ፣ ልጅ በመንከባከብ ረገድ ማገዝ ለሚችሉ ቤተሰቦች ችግረኛ ልጅን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ በሌለበት አማራጩና ፈጣኑ መፍትኄ፣ ለማደጎ መስጠት ሆኗል። የኢትዮጵያ ህግ፣ ከወላጆች መካከል እንድም ቢሆን በህይወት እስካለ ድረስ ፣ ልጅን ለማደጎ መስጠት እንደማይገባ ይደነግጋል። ግን ፣ ይህ ህግም ቢሆን፣ ልጆችን ለባእዳን በጉደፈቻ መልክ አሳልፎ መስጠት የሚገታበት አዝማሚያ አያታይም።

«ልጆችን ለማደጎ አሳልፈው የሚሰጡ፤ የተደራጁና የተለያዩ ማታለያ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ድርጅቶች አሉ። ልጆቻቸው፣ ለአሳዳጊዎች ቢሰጡም፣ በየጊዜው እየተመለሱ፣ የሥጋ ወላጆቻቸውን እንደሚጎበኙ ቃል ይገባል። በተጨማሪም፣ ህጻናትን ካንድ ቤተሰብ ወደ ሌላ የማዛወሩ ተግባር ፣ ብዙ ገንዘብ የሚከፈልበት በመሆኑ ፤ አሠራሩ፣ ለሙስና በር የከፈተ፣ መሆኑ አልታበለም። እንደሚመስለኝ፣ ብዙ የማታለል ተግባርም የሚፈጸምበት ነው።»

በሌላ በኩል፣ በአፍሪቃው ክፍለ ዓለም፣ ጋናን በመሳሰሉ አገሮች፣ ህግ ባያግዳቸውም፣ ለማደጎ እጅግ በጣም ጥቂት ልጆች ናቸው የሚሰጡት። በጋና እርዳታ የሚያሻቸውን ልጆች የሚደግፈው Compassion for Humanity Foundation የተሰኘው ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቄስ ኢማኑኤል ክዌሲ ንኩሩማ ፣ ልጆች በጉድፈቻ እንዲያድጉ ማድረጉ ስህተት አይደለም ባይ ናቸው።

«እንደኔ አመለካከት፣ አንድን ልጅ ከጋና ወስዶ ማሳደግ አዎንታዊ ገጽም አለው። ምክንያቱም ፣ ልጁ ከሌላ አገር ባህል፣ ጥሩ ትምህርት ከሚሰጥበትና ክብካቤም ከሚያደርግ ኅብረተሰብ ጋር ይተዋወቃል።»

ጥሩ ክብካቤ ሊኖር ይችላል፤ ግን ጉድፈቻ ከሁሉም የመጨረሻው አማራጭ መፍትኄ ተደርጎ ነው ሊወሰድ የሚገባው የሚለውን ልጆችን የሚመለከተውን ዓለም አቀፍ ደንብ የሚጻረር ነው። ቄስ ንኩሩማ እንደሚሉት፣ ለልጆች እርዳታ እየተባለ፣ በበጎ አድራጎት የሚላክ ገንዘብ ከሚያጭበረብሩ ሰዎች እጅ እየገባ እርዳታ የሚያሻቸው ስለማያገኙት፣ ለማደጎመስጠቱ በቀጥታ ልጁን መጥቀም ይሆናል።

«ተገቢ የሆነ ቁጥጥር እስከሌለ ድረስ፤ አንድ ልጅ የሚገባውን ድጋፍም ሆነ እርዳታ አያገኝም፤ ለዚህም ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ፣ አንድን እርዳታ የሚያሻውን ልጅ፣ በዚያው በትውልድ አገሩ መርዳቱ፤ አስቸጋሪ እየሆነ የሚገኘው።»

በአንዳንድ አገሮች ህጻናት ከትውልድ አገራቸው እንዳይፈናቀሉ የሚያደርጉ ጥብቅ ህግጋት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዩጋንዳ፣ አንድን ዩጋንዳዊ ልጅ በማደጎ መወሰድ የሚፈልጉየውጭ ተወላጆች የሆኑ ባልና ሚስት በዚያች አገር ቢያንስ 3 ዓመት የተቀመጡ፣ እንዲሁም አንድን ልጅ፣ ቢያንስ 3 ዓመት የረዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል። አሁንም ቄስ ንኩሩማ፣ ለአፍሪቃ ልጆች የተሻለ ኑሮ የተሻሉ አማራጮች ወይም መፍትኄዎች እንዳሉ በመጥቀስ ዋናው ምን እንደሆነ ሲጠቅሙ--

«በአንደኛ ደረጃ የሚመረጠው እርዳታ የተቸገሩ ወላጆችን በመደገፍ ልጅን ተንከባክበው እንዲያሳድጉ ማብቃት ነው።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ