1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

አከራካሪው የሕገ መንግስት ጉዳይ

ዓርብ፣ ጥቅምት 15 2017

የኢትዮጵያ አሜሪካ ሲቪል ማኀበራት፣ ለኢትዮጵያ አዘጋጅተነዋል ባሉት አዲስ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ላይ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ውይይት አካሄዱ። በዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት ሰሞኑን ውይይቱን ያካሄዱት ማኀበራቱ፣ ኢትዮጵያን ካለችበት ችግር የሚያውጣት አዲስ ሕገ መንግሥት ያስፈልጋታል ባይ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4mFAp
ሕገ መንግሥት
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት ፎቶ ከማኅደር ምስል Solomon Muche/DW

አከራካሪው የሕገ መንግስት ጉዳይ

 

ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት ኬኔዲ ካውካስ ራስል ጽሕፈት ቤት ተሰብስበው የነበሩት የኢትዮጵያ አሜሪካ ሲቪል ማሕበራት ሊቀመንበር አቶ መስፍን መኮንን ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት፣ በረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተጀመረው ውይይት በተለያየ ጊዜ ሲካሄድ ወደ አንድ ዓመት እያስቆጠረ ነው።

ሕገ መንግሥቱ የጋረጠው አደጋ

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው እና የብሔር ፌዴራሊዝምን መሠረት ያደረገውየኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ የብሔር ግጭቶችን በማቀጣጠል ሀገሪቱን ለመበታተን አደጋ በማጋለጡ ነው ወደዚህ አዲስ የሕገ መንግሥት ረቂቅ ዝግጅት የገቡት።

«ዋናው ምንጩ የሀገራችን ችግር ሕገ መንግሥቱ ስለሆነ፣ ሰውን የሚያምሰውና የሚያጫርሰው እሱ ስለሆነ፣ ሰውን የሚያጋድለው ይሄ የብሔር ፌዴራሊዝም ሕገ መንግሥት በተለይ ካልተወገደ ካልተስተካከለና በሌላ ካልተተካ፣ ማንኛውም  መንግሥት ቢመጣ አሁንም እንደዛ ነው ማለት ነው፤ ምንም ዓይነት መፍትሄ ልናገኝ አንችልም። እንቀጥላለን ገና ያላለቀ ሥራ ነው።»

የአዲስ ሕገ መንግሥት አስፈላጊነት

በተመሳሳይ፤ ለኢትዮጵያ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የአዲስ ሕገ መንግሥትን አስፈላጊነት አጉልተው የሚናገሩትና በውይይት የተሳተፉት ሌላኛው የማሕበራቱ ባልደረባ አቶ መኮንን ዳያሞ በበኩላቸው፣ በዚህ ሂደት የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

«እስከመጨረሻው ድረስ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከህገ መንግሥት ነፃ ወጥቶ ወደ ሕግ የበላይነት እንዲሸጋገር፣ የሕግ የበላይነት ማለት ሕገ መንግሥት ማለት ነው። ከመንግሥት እጅ ነፃ የሆነ የሕግ የበላይነት ረቂቅ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቦ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድምፁ እንቀበላለን አንቀበልም የሚለው ተዘጋጅቶ ድምጹን ሰጥቶ፣ መንግሥትን የመቅጠር ዕድል እንዲያገኝ የአሜሪካ መንግሥት በጣም ወሳኝ ነው ለእኛ።»

የሂደቱ አሳታፊነት ጥያቄ

ጉዳዩ አስመልክተን ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አያና ፈይሳ ግን በዚህረቂቅ ሕገ መንግሥትየማዘጋጀት ሂደት ላይ፣ የአሳታፊነት ጥያቄ ያነሳሉ። አቶ አያና አክለውም ሕገ መንግሥቱ ሙሉ ትርጓሜ አግኝቶ ተፈጻሚነት ያገኝበት ጊዜ አለ ብለው እንደማያምኑም አስረድተዋል።

«ሕገ መንግሥቱ ሰዎች በብሔረሰብ ተነጥለው እንዲፈናቀሉ እንዲጎዱ በፍጹም አይፈቅድም። የመሬት ባለቤትነትም ሆነ የሀገር ባለቤትነት ለዜጎች የሚሰጥ ነው፤ ሕገ መንግሥቱ እና ብዙ ብዙ ነገሮች። አዲስ ሕገ መንግሥት ከ 80 በላይ ለሚበልጡ ብሔሮች፣ በአንድ ብሔር ፖለቲካ ከእዛም ውስጥ በአንድ መንገድ ውስጥ ብቻ፣ ያለ አካል ለአገር ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሥራ ላይ መጠመዱ ጥሩ ልምምድ ቢሆንም፣ የአሜሪካ መንግሥት ጋር ሲወሰድ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ተጽዕኖ አለው። አሜሪካ ከ 80 በላይ ብሔሮች ባልተወከሉበትና ባልተወያዩበት አንድ ድርጅት ብቻ አስጠግታ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሥራ ላይ አትሳተፍም። እንደኔ ሕገ መንግሥቱ ሙሉ ትርጓሜ አግኝቶ፣ ሙሉ በሙሉ በአገሪቱ ላይ ተፈጻሚነት ያገኘበት ጊዜ አለ ብዬም አላምንም።»

ከዚህ ቀደም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው ጥናት፣ በመጠይቁ ካካተታቸው 75 በመቶ የሚሆኑት፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻልን ሀሳብ እንደሚደግፉ ማመልከቱ አይዘነጋም።

ታሪኩ ኃይሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ