አንጎላ ዶሽ ሳንቶሽን የሚተካ ፕሬዝደንት ትመርጣለች | አፍሪቃ | DW | 23.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አንጎላ ዶሽ ሳንቶሽን የሚተካ ፕሬዝደንት ትመርጣለች

አንጎላ ለ38 ዓመታት የዘለቀዉን የኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽን ዘመነ ስልጣን የሚያከትም ታሪካዊ ምርጫ ዛሬ አካሂዳለች። የነዳጅ ዘይት ዋጋ መዉረድ እና ከፍተኛ ግሽበት በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉ ሀገር ሲመራ የከረመዉ የሕዝቦች ንቅናቄ ለአንጎላ ነፃነት በምህጻሩ MPLA የተባለዉ ገዢ ፓርቲያቸዉ መንበሩ እየተንገጫገጨ እንደሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:51
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:51 ደቂቃ

አንጎላዉያን ለዉጥ ይፈልጋሉ፤

በጎርጎሪዮሳዊዉ 1979ዓ,ም መስከረም 20 ቀን ነበር ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ አንጎላ ከቅኝ ተገዢነት ነጻ ከሆነች በኋላ የመጀመሪያዉ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት የነበሩት አጉስቲኖ ኔቶ  ሲሞቱ በእግራቸዉ የተተኩት። ያኔ የሶቪየት ወዳጅ የነበረዉ የዶሽ ሳንቶሽ ፓርቲ  የሕዝቦች ንቅናቄ ለአንጎላ ነፃነት በምህጻሩ MPLA፤ ከምዕራባዉያን ወዳጁ ብሔራዊ አንድነት ለአንጎላ አጠቃላይ ነፃነት በምህፃሩ UNITA እና ከለአንጎላ ነፃነት ብሔራዊ ግንባር ጋር ከእርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ ገብቶ ነበር።  በወቅቱ የደቡብ አፍሪቃዉ አፓርታይድ UNITAን ሲደግፍ የኩባ ኃይሎች ደግሞ ከMPLA ጎን ቆመዋል። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1991 ዶሽ ሳንቶሽ እና የUNITAዉ መሪ ኾናስ ሳቪምቢ የሰላም ስምምነት አደረጉ። በቀጣዩ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደዉ ዴሞክራሲያዊ ምርጫም MPLA አሸነፈ። UNITA ዉጤቱን አልቀበልም በማለቱ ዳግም የእርስበርስ ዉጊያ ዉስጥ ገቡ። በ1994 ድጋሚ የሰላም ዉልተፈራረሙ። በስምምነቱ መሠረት የUNITA መሪዎች የተካተቱበት የአንድነት መንግሥት ተቋቋመ። ብዙም ሳይቆይ በቀጣዩ ዓመት ዳግም የእርስ በርስ ጦርነቱ አገረሸ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2002ዓ,ም የዩኒታ መሪ ሳቪምቢ ተገደሉ። በአንጎላ ጦር እና በዩኒታ መካከልም የእርስ በርሱን ጦርነት የሚያከትም የተኩስ አቁም ዉል ተደረሰ። የ27 ዓመቱ ጦርነትም በትንሹ 500 ሺህ ዜጎችን መፍጀቱ ተመዝግቧል።

አንጎላ ሰላም ከሰፈነባት በኋላም የዛሬ ዘጠኝ ዓመት በተካሄደዉ ምርጫ MPLA በከፍተኛ ድምጽ አሸነፎ የስልጣን መንበሩን አረጋጋ። ቀጠለና ከአራት ዓመታት በኋላ አንጎላ ባካሄደችዉ ምርጫ 71,8 በመቶ የሚሆነዉን የሕዝቡን ድምጽ አገኘ። ዶሽ ሳንቶሽም በተረጋጋችዉ ሀገር ይፋዊ ስልጣናቸዉን በቃለ መሃላ ያዙ። ሕዝቡ ዴሞክራሲ እና ሃሳብን የመግለፅ ነጻነት እንዲሁም የተሻለ የኑሮ ሁኔታን በመጠየቅ ተቃዉሞ ለማሰማት አደባባይ ሲወጣ በዶሽ ሳንቶሽ አገዛዝ ሥር ኃይል የተቀላቀለ የፖሊስ ምላሽ ሲያስተናግደዉ ቆይቷል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የሚፈጸመዉን ጥቃት እና የተቃዉሞ ፖለቲካ አራማጆች ላይ የሚቀርበዉን ክስ፤ እንዲሁም ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች የሚደርስባቸዉን ጫና ሲያወግዙ ተሰምቷል።

Angola Wahl João Lourenço (Getty Images/AFP/A. Rogerio)

የዶሽ ሳንቶሽ እጩ ፕሬዝደንት ዦዉ ሉሬንሶ

ባለፈዉ ጥር ወር ማለቂያ ገደማ ዶሽ ሳንቶሽ ዛሬ በሚካሄደዉ ምርጫ ለዉድድር እንደማይቀርቡ ይፋ አደረጉ። በእግራቸዉ እንዲተኩም ቀኝ እጃቸዉ የሆኑትን የሀገሪቱን የመከላከያ ሚኒስትር ዦዋዉ ሉሬንሶ  በእጩ አቀረቡ። ባለፈዉ ቅዳሜ ፓርቲያቸዉ ባካሄደዉ የምርጫዉ ቅስቀሳ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በመገኘትም ነባሩን የፓርቲያቸዉን መፈክር «አንጎላን እንወዳለን! ትግሉ ይቀጥላል1 አሉታ ኮንቲኒዋ! አስተጋቡ። ፓርቲያቸዉ MPLA በዛሬዉ ምርጫ ማሸነፉን አይጠራጠሩም። አብዛኞቹ አንጎላዉያንም ግምታቸዉ ከእሳቸዉ የሚቃረን አይነት አይደለም ። የ35 ዓመቱ የሂፖፕ ሙዚቃ ተጫዋች ሉዋቲ ቢራዩ አንጎላ ዉስጥ ምርጫ ማለት «ያረጀዉን ፊልም» ዳግም ለእይታ ማቅረብ እንደ ማለት ነዉ። በተቃራኒዉ ግን ወጣቱ ትዉልድ ለዉጥ ይፈልጋል፤ በመንግሥት አስተዳደር ዉስጥ የሚሳተፍ አዲስ ኃይል ለማየት ይመኛል። ሙዚቀኛዉ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከዶሽ ሳንቶሽ መንግሥት ጋር ከሚፋለሙ ጥቂት የመብት ተሟጋቾች አንዱ ነዉ። በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ ታስሯል። አሁንም ግን ትችትና ተቃዉሞዉን አላቆመም።

«በ2017ም ያንኑ በ2012 ያየነዉን ፊልም ነዉ የምናየዉ። እዚህ እየተደረገ ያለዉን ለተመለከተዉ አሳፋሪ ነዉ። የተዛቡ እና መራጮች ድምሳጸዉን ለመስጠት እንዳይችሉ የሚያደርግ ነገር እናያለን፤ አብዛኛዎቹ መራጮች የመምረጥ መብታቸዉን መጠቀም አይችሉም። ለምሳሌ ድምጽ የሚሰጡበት ቦታ ከመኖሪያ ቦታቸዉ በጣም የራቀ ነዉ፤ የአንዳንዶቹም በሌላ ክፍለ ሀገር ነዉ፤ ልክ በ2012 ዓ,ም ከሆነዉ ጋር ተመሳሳይ ነዉ።»

ባለፉት አራት ሳምንታት በተካሄደዉ የምርቻ ቅስቀሳ ገዢዉ MPLA ከፍተኛ ተፅዕኖ ማድረጉ ታይቷል። የቀረበዉ የምርጫ ካርድ መጠንም ሲታይ ለፉክክት የቀረቡት አምስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዢዉ ፓርቲ ጥግ ሊደርሱ እንዳይችሉ የሚያደርግ መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ። በመገናኛ ብዙሃንን ለመቅረቡም ቢሆን እኩል ዕድሉን አግኝተዋል ማለት ፈጽሞ አይቻልም። የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃኑ ሰፊዉን ድርሻ ለገዢዉ ፓርቲ በሰፊዉ መስጠታቸዉ ታይቷል። የምርጫ ኮሚሽኑ አወቃቀርም ሌላዉ የተቃዋሚ ፓርቲዎቹን ጥርጣሬ ከፍ ያደረገ ነዉ። ከኮሚሽኑ 17 አባላት 10ሩ በገዢዉ ፓርቲ የተሰየሙ ናቸዉ። ሀገሪቱ አሁን የምትገኝበትን ሁኔታ ለማወቅ ሉዋንዳን መመልከቱ ይበቃል። የኤኮኖሚዉ ሁኔታ አደጋ ላይ ወድቋል፤ የሥራ አጡ ቁጥር እጅግ ከፍ ብሏል። በዓለም ገበያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መዉደቅ የሀገሪቱን ቀዳዳ መድፈን የማይችል በጀት አስከትሏል። እናም ሕዝብ ለዉጥ ይፈልጋል።

«በየመንገዱ ሰዎችን ስናነጋግር ለዉጥ ለማየት መፈለጋቸዉን አስተዉለናል ይህ ደግሞ በዴሞክራሲ የሚጠበቅ ነዉ፤ ነገር ግን በመገናኛ ብዙሃን የምንሰማዉ ለአንድ ፓርቲ ብቻ አቆመ ምህረት የለሽ ፕሮፓጋንዳ ፤ ፍትኃዊ ምርጫ እንደሌለ ያመላክታል። ሕዝቡ ለዉጥ መፈለጉ እዉነት ነዉ፤ ሆኖም ግን መጨረሻ ላይ በሚገርም ሁኔታ MPLA አብላጫዉን ድምጽ ማግኘቱን እናያለን።»

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች