አንጋፋው አዝማሪ ደጀን ማንችሎት | ባህል | DW | 11.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

አንጋፋው አዝማሪ ደጀን ማንችሎት

አዝማሪነት ከወላጆቹ የወረሰው ሙያ ነው። ከልጅነቱ አንስቶ የሚጫወተውን ማሲንቆን«ከወላጆቼ ነጥዬ የማላየው ህይወቴ »ነው የሚለው፤ ደጀን ማንችሎት «ዓለምን የዞርኩበት ደስታን ያገኘሁበት» በሚለው በዚህ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ እውቅና ካተረፉት ኢትዮጵያውን ሙዚቀኞች አንዱ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:59

ደጀን ማንችሎት

በአዝማሪነቱ በጣም እንደሚኮራ የሚናገረው ደጀን ተወልዶ ያደገው ጎንደር ፣ ከጎንደርም በታወቀው የአዝማሪዎች መንደር በቡርቧክስ ነው። አሁን ታዋቂ የሆነበትን ሙያውን የወረሰው ከአዝማሪዎቹ እናት እና አባቱ ቢሆንም በሙያው ለመግፋት ምክንያት ሆኑኝ የሚለው ከርሱ የቀደሙትን እና ከመካከላቸው የሥጋ ዝምድና ያለውን አንጋፋዎቹን ማሲንቆ ተጫዋቾች እና ታዋቂ ድምጻውያንን ነው። ከ9 ዓመቱ አንስቶ በትውልድ አካባቢው ማሲንቆ መጫወት የጀመረው ደጀን በ13 ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ ሄደ። አዲስ አበባ በገባ በዓመቱ በሙያው ለማደግና ዕውቅናን ለማትረፍ የበቃበት ያያኔው አምባሳደር ቲያትር በኋላም ራስ ቲያትር የባህል ሙዚቃ ክፍል ሲመሰረት በማሲንቆ ተጫዋችነት እና በድምጻዊነት ተቀጠረ። ራስ ቲያትር አሥር ዓመት በቆየባቸው ጊዜያትም ከሙዚቃ ቡድኑ ጋር በበርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጉዞዎች ተካፍሏል። ለ1977 የኢትዮጵያ ድርቅ ዓለም ላደረገው እርዳታ ምስጋና ለማቅረብ ታዋቂ አርቲስቶች በተካፈሉበት በ1979 በተካሄደው የህዝብ ለህዝብ የሙዚቃ ትርዒትም ላይ ተካፍሏል። በዚህ ጉዞ 39 ሀገር እና 48 ያህል ከተማ ለማየት መብቃቱን የሚናገረው ደጀን ከሁሉ ተደሰትኩበት የሚለው ግን የመጀመሪያውን የውጭ ጉዞ ነው። እስከ 1980 ራስ ትያትር የሰራው ደጀን ከዚያ ወጥቶ ታዋቂ ድምጻውያን ባቋቋሙት የግዮን ሆቴል የባህል ሙዚቃ ባንድ ውስጥ መሥራት ጀመረ።

Äthiopien - Dejen Manchelot Musiker in Masinqo

ደጀን ከዛሬ 10 ዓመት ወዲህ እሥራኤል ነው የሚኖረው።

ከዚያን ጊዜ አንስቶም ከ330 በላይ በሚሆኑ ካሴቶች የወጡ ዘፈኖችን እንዲሁም ከ270 በላይ በካሴት የወጡ መዝሙሮችን በማሲንቆ አጅቧል። ደጀን ከዛሬ 10 ዓመት ወዲህ እሥራኤል ነው የሚኖረው።ደጀን በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጭ አዝማሪና ማሲንቆን በተመለከቱ  የተለያዩ ጉባኤዎች ላይ በእንግድነት ይጋበዛል። ጀርመን የተለያዩ ከተሞች በተካሄዱ ሦስት መሰል ጉባኤዎች ላይ ተገኝቶ ልምዱን አካፍሏል።ታዳሚዎችንም አዝናንቷል። በሚወደው ሙያ ተሰማርቶ እስካሁን በመዝለቅ በመቻሉ ደስተኛ ነው ከዚያ በላይ የምደሰተው ግን በቤተሰብ በመመስረቴ እና ልጆች በመውለዴ ነው ይላል። ደጀን ባለትዳርና  የአራት ወንዶች ልጆች ልጆች አባት ነው።

ኂሩት መለሰ

ልደት አበበ

 

Audios and videos on the topic