አንድ ዓመት የሆነዉ የደቡብ ሱዳን የርስ በእርስ ጦርነት | አፍሪቃ | DW | 16.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አንድ ዓመት የሆነዉ የደቡብ ሱዳን የርስ በእርስ ጦርነት

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርን በሚደግፉ የመንግሥት ወታደሮችና በቀድሞዉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ደጋፊ ኃይላት መካከል የተጀመረዉ ጦርነት አንድ ዓመት አስቆጠረ።


ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት የሰላም ስምምነት እንዲደርሱ በአካባቢዉ ሃገራት የሚደረገዉ ጥረት እስካሁን ፍሬን አላስገኘም። በደቡብ ሱዳኑ የርስ በእርስ ጦርነት እስካሁን በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ተገድሎአል፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ደግሞ ከመኖርያ ቀየዉ ተፈናቅሎአል።

Martin Petry Experte für Entwicklungshilfe EINSCHRÄNKUNG

ጀርመናዊዉ የሰላምና የአስተዳደር ጉዳይ አማካሪ ማርቲን ፔትሪበምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ አደራዳሪነት በደቡብ ሱዳንን የርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም የሚደረገዉ ተደጋጋሚ ጥረት እስካሁን ተጨባጭ ዉጤት አላገኘም። በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቻር የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰላም ለማስፈን ቢስማሙም እስካሁን የፈረሙት ዉል ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አላደረጉትም። ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርን በሚደግፉ የመንግሥት ወታደሮች እና በቀድሞዉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ተፋላሚ ኃይላት መካከል ልክ የዛሬ ዓመት በስልጣን ሽኩቻ ሰበብ የተጀመረዉ ጦርነት ጥልቅ የጎሳ ልዩነት እንደተንፀባረቀበት ነዉ የሚነገረዉ። ጀርመናዊዉ የሰላምና የአስተዳደር ጉዳይ አማካሪ ማርቲን ፔትሪ የደቡብ ሱዳን የርስ በእርስ ጦርነትን ለሰላም ስምምነት ላይ ተደርሶ እልባት ያገኛል የሚል እምነት ነበረኝ ሲሉ የርስ በእርስ ጦርነቱ ከጀመረበት ከዛሬ ዓመቱ ጋር በማነጻጸር ይገልፃሉ።

« ሁላችንም ብንሆን ሁለቱ ተቀናቃኝ ቡድኖች ሰላም ስምምነት ላይ ደርሰዉ፤ የሰላም ጥረቱ መሻሻል ይታይበታል የሚል ተስፋ ነበረን። ይህ ግን አልሆነም። በአንጻሩ ከኅዳር ወር ጀምሮ ምንም አይነት የሰላም ስምምነት አልታየም፤ በሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት መካከል ያለዉ ቅራኔና መቃቃርም እየጨመረ ነዉ፤ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት በየበኩላቸዉ መሳርያ ክምችታቸዉን እያጠናከሩና ለዉግያ እየተጠናከሩ መሆኑን ሁሉም ያዉቃል »

Südsudan Friedensgespräch

የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በየነ መንግስታት ባለሥልጣን «የኢጋድ ዋና አደራዳሪ አምባሳደር ስዩም መስፍን


እንደ ማርቲን ፔትሪ ላለፉት 40 ዓመታት ከተደረገዉ የርስ በእርስ ጦርነት ከታየዉ ልምድ፤ ዉግያዉ ከታህሳስ ወር እስከ ሚያዝያ ባሉት ወራት እጅግ ይጠናከራል። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የአካባቢዉ የአየር ሁኔታ ደረቃማ እና ለመጓጓዝ አመቺ ሁኔታን በመፈጠሩ ነዉ።
የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በየነ መንግስታት ባለሥልጣን «የኢጋድ ዋና አደራዳሪ አምባሳደር ስዩም መስፍን ትናንት አንድ ዓመት የሞላዉን የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት አስታከዉ ስለ ሰላም ድርድሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፤

«ሁለቱ ተፋላሚዎች ከየራሳቸዉ ደጋፊዎች ጋርና ከሚመለከታቸዉ አመራሮች ጋር እንዲመካከሩበት ጊዜ እንዲሰጣቸዉ ጉባኤዉን ጠይቀዉ ነበር። ጥያቄያቸዉ በተለይ በመሪዎች ደረጃ መፈታት አለበት ብለዉ የሚያምኑት አንድ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር። ይህም በብሔራዊ የአንድነት የሽግግር መንግሥቱ መዋቅርን የሚመለከት ነዉ ተፋላሚዎቹ ብቻ ሳይሆኑ በደቡብ ሱዳን የድርድር ሂደት ዉስጥ የሚሳተፉ ወገኖች በሙሉ ዘገባዎቻቸዉን ለኢጋድ ንዑስ ወይም ሙሉ ጉባኤ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢጋድ ሊቀመንበር በፋንታዉ ከኢጋድ አባል ሃገራት መሪዎች ጋር በጉዳዩ ላይ ይመካከርበታል።»ይሁንና የንግግሩ ሂደት የሚፈለገዉ ዉጤት ላይ እንዲደርስ ከደቡብ ሱዳኖች ጥረት በተጨማሪ የአካባቢዉን ሃገራትና የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ዋናዉ አደራዳሪ አምባሳደር ስዩም አያይዘዉ ገልፀዋል።
« በምክክሩ ዉጤት ላይ በመመስረት የአካባቢዉና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ቀጣይ ርምጃ ለሁላችንም ግልፅ ይሆናል። እስከዝያ ግን በደቡብ ሱዳን ህዝብና መሪዎች ብልህነት በአካባቢዉና በዓለም አቀፍ ሙሉ ድጋፍ ላይ ተስፋ እምነታችንን እናድርግ።» አምባሳደር ስዩም መስፍን አክለዉ እንዳሉት የሚመሩት አደራዳሪ ቡድን በደቡብ ሱዳኖች ብልህነትና በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ላይ ትልቅ ተስፋ አለዉ።


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic