አንድ ቀን ለኢትዮጵያ በፍራንክፈርት | የጋዜጦች አምድ | DW | 11.04.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

አንድ ቀን ለኢትዮጵያ በፍራንክፈርት

በዚሁ በጀርመን በፍራንክፈርትና አካባቢዉ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የተሳተፉበት አንድ ቀን ለኢትዮጵያ Ein Tag Für Äthiopien በሚል ርዕስ የተሰየመ ዝግጅት ባለፈዉ ቅዳሜ ተካሄደ። Höchst በተሰኘችዉ ከተማ የተካሄደዉ ይህ ዝግጅት በጀርመን የተቋቋመዉ አቢሲኒያ የመረዳጃ ማህበር የተባለዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ለተነሳበት ዓላማ ገቢ ለማሰባሰብ ታልሞ የተዘጋጀ ነበር።

ማህበሩ ጀርመን በሚኖሩ ጥቂት ኢትዮጵያዉያን ተነሳሽነት ተቋቁሞ አሁን ወደ 50 የሚደርሱ አባላት አፍርቷል።
ድርጅቱ በዚሁ በጀርመን አገር ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ሆነዉ ከዓላማዉ ጋር የተገናኘ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ግን አልጀመረም።
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ላቀዉ መብራቱ ምክንያቱን እንደገለፁልን ተግባራዊ እንቅስቃሴዉን በኢትዮጵያ ለመጀመር እዛዉ ባንክ ዉስጥ እንዲያስቀምጥ የተጠየቀዉን የገንዘብ መጠን ማሰባሰብ ባለመቻሉ ነዉ።
አንድ ቀን ለኢትዮጵያ በሚል የተሰየመዉ የዚህ ዝግጅት ዋና ዓላማም የታሰበዉን ያህል ባይሆንም መደጎሚያ የሚሆን ገቢ ለማግኘት ነዉ።
በተጨማሪም በዚህ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ዓላማቸዉን ተረድቶ ተባባሪያቸዉ እንዲሆን ለማድረግ መሆኑንም አቶ ላቀዉ ገልፀዋል።
ምንም እንኳን በፍራንክፈርትና አካባቢዉ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ቢኖሩም በዕለቱ ግን ያን ያህል ብዙ የሚባል አልነበረም ታዳሚዉ።
በዕለቱ በዝግጅቱ ላይ ከተገኙት መካከል ግን አብዛኛዎቹ እንደገለፁልን እንዲህ ባለ አጋጣሚ መሰባሰቡ ለእነሱ ታላቅ ነገር ነዉ።
በዚህ ሰዉ እንደልብ በማያገኙበት ቦታ ከወገኖቻቸዉ ጋር መገናኘታቸዉ አንድ ነገር ሆኖ እግረ መንገዳቸዉንም አቅማቸዉ እንደፈቀደ ወገኖቻቸዉን ለመርዳት በመቻላቸዉ ተደስተዋል።
የአቢሲኒያ መረዳጃ ማህበር በጀርመን የተሰኘዉ ይህ ድርጅት የጀርመን መንግስት ህግ በሚፈቅደዉ መሰረት ተቋቁሞ በጀርመን አገር መንቀሳቀስ ጀምሯል።
ከሶስት ወራት በፊት ደግሞ በኢትዮጵያ የአደጋ መከላከልና ዝግጅት ኮሚሽን ስር መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅትነት ተመዝግቦ ህጋዊ ሰዉነት አግኝቷል።
ድርጅቱ የተቋቋመባቸዉ በርካታ አላማዎች ቢኖሩትም በዋናነት በዕድሜ የገፉ ጧሪ የሌላቸዉ አረጋዉያን የምግብና የልብስ እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ፤ ልዩ የህክምና አገልግሎት በሚሰጡ የህክምና ተቋማት ከፍለዉ ለመታከም ለማይችሉ ወገኖች አገልግሎት የሚዉሉ የህክምና መሣሪያዎችንና መድሃኒቶችን በእርዳታ እንዲያገኙ ማስቻል።
በተጨማሪም በህመምና በሰዉ ሰራሽ ምክንያቶች ማየት ለተሳናቸዉ ወገኖች እርዳታ ማፈላለግ እንዲሁም ዉጤት እያላቸዉ የገንዘብ አቅም በማጣት ትምህርታቸዉን በከፍተኛ ተቋማት መከታተል ላልቻሉ ወጣቶች ወጪያቸዉን ሸፍኖ ማስተማር የሚሉት ይገኙበታል።
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዓላማዉን በተረዱ ሰዎች ለጋሽነት የፅህፈት ቤትና አንዳንድ ለፅህፈት ቤቱ የሚያስፈልገዉን ቁሳቁስ በነፃ ለማግኘት ችሏል።
አቶ ላቀዉ እንደሚሉት በዚህ በጀርመንም በርካታ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን ከግለሰቦችም ሆነ ከተለያዩ ድርጅቶች በስጦታ እያገኙ ቢሆንም አጓጉዞ የሚፈለጉበት ቦታ ለማድረስ ለጊዜዉ የድርጅታቸዉ አቅም አልቻለም።
አቅማቸዉን ለማጠናከርም ከዚህ ዝግጅት በተጨማሪ በመጪዉ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. አባላቱንና የማህበሩን ዓላማ የሚደግፉ ወገኖችን ለስብሰባና ለመዋጮ ጋብዟል።
ማህበሩ በልምድና በዕድሜ ከበለፀጉት አባላቱ በተጨማሪ ቁጥራቸዉ የማይናቅ ወጣት አባላትንም በስሩ አሰባስቧል።
በእለቱም ህፃናትን ከማዝናናት ጀምሮ የአገር ባህል ልብስ የፋሽን ትርኢት፤ የስዕል አዉደ ርዕይና ሙዚቃ እንዲሁም የተለያዩ 15 ዕጣዎችን የሚያስገኝ ቶምቦላና ሌሎችም ተጓዳኝ ዝግጅቶች እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ድረስ ተካሂደዋል።
የቶምቦላዉ የመጀመሪያ ዕድልም የሚያስገኘዉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያ ደርሶ መልስ የነፃ ትኬት ነበር።
ይህን ዕድል አየር መንገዱ ለድርጅቱ በእርዳታ የሰጠ ሲሆን የዕጣዉ አሸናፊም በእለቱ ከፍራንክፈርት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ከአቶ የኔነህ ተክለየስ እጅ ትኬቱን ተረክባለች።


ተዛማጅ ዘገባዎች