አንድም ሶስትም ናቸዉ | ዓለም | DW | 05.10.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

አንድም ሶስትም ናቸዉ

ትራምፕ፤ ቦልሶናሮ እና ጆንሰን።የአንድ ዘመኑ መሪዎች ያንድ ዘመኑን መቅሰፍት አደገኛነት ማጣጣላቸዉ አቀራረባቸዉ።ኮቪድ 19ኝን። ያጣጣሉት መቅሰፍት ተራበተራ ሲጥላቸዉ  ደግሞ በርግጥ ሶስትም አድም አደረጋቸዉ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:00

ጆንሰን፣ ትራምፕ፣ ቦልሶናሮና ኮቪድ 19

የሶስት ክፍለ ዓለማት የሶስት የሩቅ ለሩቅ ትላልቅ ሐገራት ግኝቶች ናቸዉ።በዕድሜ፣ የመጀመሪያዉ ከሁለተኛዉ፣ ሁለተኛዉ ከሶስተኛዉ በ10 ዓመታት ይበላለጣሉ። እድገት፣ትምሕርት ልምዳቸዉም ለየቅል ነዉ።መርሕ አስተሳሰባቸዉ ግን ተመሳሳይ፣ ደግሞም እኩል ፖለቲከኛ ናቸዉ።በሁለት ዓመት ልዩነት ተከታትለዉ የሶስቱ ሐገራት ግን ያንድ ዘመን መሪዎች ሆኑ።ትራምፕ፤ ቦልሶናሮ እና ጆንሰን።የአንድ ዘመኑ መሪዎች ያንድ ዘመኑን መቅሰፍት አደገኛነት ማጣጣላቸዉ አቀራረባቸዉ።ኮቪድ 19ኝን። ያጣጣሉት መቅሰፍት ተራበተራ ሲጥላቸዉ  ደግሞ በርግጥ ሶስትም አድም አደረጋቸዉ።የትራምፕ መታመም መነሻ፣ የሶስትም አንድምነታቸዉ መርሕ ማጣቀሻ፣አስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ፤ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

«ድል ወይም ጥሩ ዉጤት ብዙ እናቶች አሏት፣ ሽንፈት ግን እጓለ ሙዉታን ናት እንዲሉ አዉሮጶች» ሆኖ በመጀመሪያዉ ይሁን በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነቶች፣ በቀዝቃዛዉ ይባል በየሐገር ድንበሩ ግጭት-ዉጊያዎች ድል አድራጊዎቹ-ብዙ፣ በቴክኖሎጂ ምጣኔ ሐብት ዕድገቱም  በጎ ዉጤት አስመዝጋቢዎች በርካቶች ናቸዉ።

እነዚያን ብዙዎች ያስተባበሩ፣ የአዋቂዎችን ምክር ገቢር ያደረጉ፣ ከሁሉም በላይ ለየሕዝባቸዉ  ድልና ዉጤትን ያስመዘገቡ መሪዎች-ያዉ መሪዎች ናቸዉና በየድል ዉጤቱ ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸዉ።

የመጀመሪያዉ ዓለም ጦርነት ድል አድርጊዎች ታሪክ ሲወሳ ከብሪታንያ ኤች ኤች አስኩይዝ እና ዴቪድ ሎይድ ጆርጅ፣ ከፈረንሳይ ዦርዥ ክሌሜንሶ፣ ከሩሲያ ቭላድሚር ኤሊይች ሌኒን፤ከዩናይትድ ስቴትስ ዊድሮዉ ዊልሰን፣ እንደሚጠቀሱ ሁሉ በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ከዩናይትድ ስቴትስ ፍራንክሊን ሩዘቬልት፣ ከብሪታንያ ዊንስተን ቸርችልን፣ ከሶቭየት ሕብረት ጆሴፍ ስታሊንን አለመጠቅስ አይቻልም።

ለቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወይም ለካፒታሊስቱ ዓለም ድል ማርጋሬት ታቸርን ከለንደን፣ ሮናልድ ሬጋንን ወይም ጆርጅ ቡሽን ከዋሽግተን፣ ለምጣኔ ሐብት ዕድገት በጣሙን ለኮምፒዉተር ቴክኖሎጂ ምጥቀት ቢል

ክልንተን እንዲሁ በተደጋጋሚ አለማንሳት ሲበዛ ከባድ ነዉ።

የዘንድሮ መሪዎች የመሪነት ብቃት፣የአዋቂ ባለሙያዎችን ምክር ማስጠንቀቂያ የመስማት፣ገቢር የማድረጋቸዉ ብስለት የሚለካዉ፣ ብዙዎች እንደሚስማሙበት የሕዝባቸዉንና የየሐገራቸዉን ምጣኔ ሐብትን ከኮቪድ 19ኝ መቅሰፍት ለመከላከል በተከተሉት መርሕና በወሰዱት እርምጃ ዉጤት ነዉ።

ከአንድም ሶስትሞቹ የዘንድሮ መሪዎች በዕድሜም፣በቀኝ አክራሪነት መርሕም፣ ሥልጣን በመያዝም፣ ከሁሉም በላይ ትልቅ ሐገርን በመምራት ትልቁና ቀዳሚዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ጆን ትራምፕ ናቸዉ።

ጥር 2017 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮያኑ አቆጣጠር) የልዕለ ኃያሊቱን ሐገር የፕሬዝደንነት ሥልጣን ያዙ።ጊዜ አላጠፉም ዋይት ሐዉስ ዉስጥ የነበረዉን የወረርሽኝ መከላከያ ቡድንን በተኑት።ሰንበትበት ብለዉ ደግሞ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከላት (CDC) በተባለዉ ተቋም ሥር የወረርሽኝ መነሻና መከላከያን የሚያጠናዉን ክፍል ዘጉት።ምክንያት ኢትዮጵያዊዉ ሳይንቲስት ዘኪ ሸሪፍ እንደሚሉት ገዘብ እንቆጥብ የሚል ነዉ።

 ትራምፕ ቀዳሚዎቻቸዉ የመሠረቷቸዉን ተቋማት፣የፈረሟቸዉን ስምምነትና ዉሎች ሲመነቃቅሩ የብራዚሉ የቀድሞ የጦር መኮንን ያር ቦልሶናሮ የብራዚሊያን ቤተ መንግሥት ለመቆጣጠር፣ ተቃዋሚዎቻቸዉን ይራገሙ-ይሰድቡ፣ ተከታዮቻቸዉን ያስተባብሩ፣ ብራዚሎችን ይቀሰቅሱ ነበር።ጥር 2019 ተሳካላቸዉ።

ከትራምፕ በ10 ዓመት ግድም የሚያንሱት ቦልሶናሮ ፖርቹጋሊኛ ተናጋሪ ትራምፕን ሆነዉ የደቡብ አሜሪካ የምጣኔ ሐብት ቁንጮዋን ሐገር ፖለቲካዊ-ምጣኔ ሐብታዊ መዋቅሯን ካናቱ  ሲነቀንቁ፣ የብሪታንያዉ ቀኝ ፖለቲከኛ ቦሪስ ጆንሰን የራሳቸዉ ፓርቲ መሪና ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩትን ቴሬሳ ሜይን ዘርጥጠዉ የሚጥሉበትን ሥልት ገቢር እያደረጉ ነበር።

ኃምሌ 2019። ቴንዳዉኒንግ ስትሪትን ተቆጣጠሩ።በለንደን የኤቢሲ ቴሌቪዝን ጣቢያ ወኪል ያኔ እንደዘገበዉ፣ ከትራምፕ በ20፣ ከቦልሶናሮ በ10 ዓመት የሚያንሱት ጆንሰን የትራምፕ ድጋፍ አልተለያቸዉም ነበር።«እኔ ባያጋጥመኝም

ብዙ ሰዎች ጆንሰንን የብሪታንያ ትራምፕ ይሏቸዋል።እዚሕ  ብዙ ሰዎች ሁለቱን መሪዎች እንወዳቸዋል እያሉ ያፌዙባቸዋል።ጆንሰን የመጫዎቻ መፅሐፍ ከሚመስለዉ ከፕሬዝደንቱ መርሕ ወስደዉ ብሪታንያን ዳግም ታላቅ እናድርግ የሚሉ ይመስላሉ።»

ከሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት ይልቅ ሰሞናዊ ጩኸት ጫጫታን፣ ከሐገር ዘላቂ ጥቅም ይበልጥ ወቅታዊ ግብን፣ ከአብሮነት ይብስ ግለኝነትን፣ ከሁሉም አቀፍነት ይበልጥ ዘረኝነትን በማቀንቀናቸዉ ለየአብያተ መንግስቱ የበቁት ሶስቱ ፖለቲከኞች የኮሮና ተሕዋሲን ሥጋት በማጣጥልም ተመሳሳይ ናቸዉ።ፕሬዝደንት ትራምፕ የካቲት ላይ መድሐኒት አልባዉን ገዳይ በሽታ እንደ «ጉፋን» ነዉ ብለዉ ነበር።

ትራምፕ ዋሽግተን ላይ በእንግሊዝኛ ያሉትን መጋቢት ላይ ቦልሶናሮ በፖርቱጋልኛ ደገሙት።እንደ «gripezinha (አ

ነስተኛ ጉንፋን) ነዉ» ብለዉ።በዚያዉ  ወር ብሪታንያ በኮቪድ 19 በሞቱና በተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዓለም አምስተኛ ደረጃን ይዛ ነበር።ሌሎቹ የአዉሮጳ መንግስታት ጥብቅ እርምጃ ሲወስዱ  ጆንሰን በበሽታዉ ተይዘዉ ሆስፒታል የተኙ ሰዎችን ሲጎበኙ እጆቻቸዉን እየጨበጡ እንዳበረታቷቸዉ ባደባባይ ተናገሩ።

ጆንሰን ከብዙ ትችት፣ከተቃዋሚዎች ጫና፣ ከባለሙያዎች ዉትወታ በኋላ የሕዝብ እንቅስዋሴን የሚገታ ደንብ መጋቢት አጋማሽ ላይ ሲያዉጁ እንኳን ሕዝብ ይጠንቀቅ ግን አደባባይ ይዉጣ ነበር ያሉት።

«ትምሕርት ቤቶችን ዘግተናል።በርካት የብሪታንያ ምጣኔ ሐብት መሠረቶችን ዘግተናል።ቡና ቤቶችን፣ምግብ ቤቶችን፣ ቲያትሮችን፣ የስፖርት ቤቶችን ዘግተናል።የዕለት ከዕለት ኑሯችን ባብዛኛዉ ተቀይሯል።ይሁንና የሰዎች አካላዊና መንፈሳዊ ጤና በጣም አስፈላጊ ነዉ።የሚችሉ ከሆነ ዉጪ መዉጣትና ስፖርት መስራት አለባቸዉ።ይሕን ለማድረግ ብዙ ሰዎች የግል መስክ የላቸዉም።ለዚሕም ነዉ ፓርኮችና ክፍት መስኮች ለሕብረተሰባችን በጣም አስፈላጊ የሆኑት።»

ሥለ ጆንሰንን መግለጫ የዘገበዉ የግሪክ ጋዜጣ  ኤታኖስ «ጆንሰን የብሪታንያ ዜጎች ሞትን እንዲቀበሉ ባደባባይ ነገሯቸዉ» ብሎ ተሳለቀ ይላል የዘጋርዲያን ዘገባ።

ብሪታንያዎች ከኮቪድ 19ኝ ጋር እየታገሉ፣ በቤት መዘጋትና ባደባባይ መዉጣት መሐል እየዋለሉ፣ በጠቅላይ ሚንስትራቸዉ መልዕክት ሲከራከሩ ከወደ ብራዚሊያ አዲስ መልዕክት ተሰማ።መጋቢት 26።ቦልሶናሮ።

 (ኮቪድ 19) ምንም አይዝም፣ አያምም።ተመልከቱ ሰዉዬዉ ኩሬ ዉስጥ ዘሎ ሲገባ።ከየቤታችሁ ዉጡ።ዋኙ።እሺ?ምንም አትሆንም።ብራዚል ዉስጥ ከጥቂት ወራትና ሳምንታት በፊት ብዙ ሰዎች ተይዘዋል ብዬ አስባለሁ።የብዙዎቹ  ሰዉነት በሽታዉን የመከላከል አቅም አዳብሯል።»

 በማግስቱ፤ አርብ መጋቢት 27 ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን  በኮቪድ 19ኝ ተያዙ።ለሳምንት ሆስፒታል ሲታከሙ፣ ለሶስት ሳምንት እቤታቸዉ ሲያገግሙ ከርመዉ ወደ ሥራቸዉ ሲመለሱ «ጉዞዉ ወደ ሁለቱም አቅጣጫ ነበር» አሉ።ወደ ሞትም ሽረትም እንደማለት።

ፕሬዝደን ትራምፕ ለጆንሰን የመልካም ምኞት መግለጫ በላኩ ሰሞን መጋቢት ማብቂያ ለሐገራቸዉ ሕዝብ «ሚያዚያ ላይ ፀሐይ ሞቅ ስትል ተሕዋሲዉም ይጠፋል» ይሉ ነበር።ፀሐይ ባገረ,ችበት ኃምሌ ግን የትራምፕዋ ዩናይትድ ስቴትስ በበሽታዉ የሞቱባት ሰዎች ቁጥር ከ120 ሺሕ በልጦ ነበር።ከዓለም እንደኛ ነበረች።አንደኛ እንደሆነች ቀጠለች።

ፕሬዝዝደንት

ትራምፕ ግን የየካቲት አቋማቸዉን መቀየር አለመቀየራቸዉን ጋዜጠኞች ሲጠይቋቸዉ «ፍንክች ያባ ቢላ ልጅ» አሉ።«የለም» መለሱ የትልቂቱ ሐገር ትልቅ መሪ።ቀጠሉም፣ «የለም፣ ሁል ጊዜ ማድረግ ያለብሕ፣ ምናልባት ሰምታችሁ ይሆናል እኔም አደርገዋለሁ፣ ሁል ጊዜ እጆችሕን ታጠብ፣ ንፅሕናሕን ጠብቅ፣ መጨበጥ ያለብሕን ሁሉንም እጆች መጨበት አይኖርብሕ ይሆናል፣ ታዉቃለሕ ጉንፋን ሲይዝሕ የተወሰኑ ነገሮችን ታደርጋለሕ፣ ይሕንንም እንደ ጉንፋን ቁጠሩት።»

ኃምሌ 7። ቦልሶናሮ በኮቪድ 19 ተያዙ።በሳንፖሎ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ኦሌቨር ስፑንካ  ቦልሶናሮ በተሕዋሲዉ በመያዛቸዉ አልተደነቁም። ፕሬዝደንቱ የሚያዙት መቼ እንጂ እንዴት የሚል ጥያቄ አልነበረምና።

«ጥያቄዉ የነበረዉ መቼ ይሆናል ነበር።ምክንያቱም ወረርሽኙ ከተሰራጨበት ጊዜ ጀምሮ ቦልሶናሮ ሥጋቱን አጣጥለዉት ነበር።በቃላት ማጣጣል ብቻ ሳይሆን፣ አካላዊ ርቀትን አያከብሩም ነበር።ብዙ ጊዜ የአፍና አፍንጫ ጭብል አላጠልቅም እንዳሉም ነበር።በተቃዉሞ ሰልፎች ወቅት ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝተዋል።ሰዎችን ሲጨብጡ፣ ሲያቅፉም ነበር።»

የ65 ዓመቱ አዛዉንት ሕመሙ እንደ ብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አልጠናባቸዉም።ቶሎ ድነዋል።ለብዙ ጊዜ የአፍና አፍንጫ ጭብል አላጠልቅም ሲሉ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ማጥለቅ ከጀመሩ በኋላ እንኳን አዘዉትረዉ በሚጠነቀቁ፣ ጭምብል በሚያዘልቁ ሰዎች  ላይ ሲያላግጡ ነበር።

የመጨረሻዉ ከዲሞክራቱ ተፎካካሪያቸዉ ጆ ባይደን ጋር ሲከራከሩ ነበር።ሐሙስ መስከረም 30። ማታ።«ጭብል አለኝ» አሉ ከኪሳቸዉ እያወጡ።«ጭምብሉን የማጠልቀዉ ግን ያስፈልገኛል ብዬ ሳስብ ብቻ ነዉ።ዛሬ ማታ እዚሕ ለምሳሌ ሁሉም ሰዉ ተመርምሯል።አካላዊ ርቀትም ይጠብቃል።ስለዚሕ የማጠልቀዉ ሲያስፈልገኝ ብቻ ነዉ።እንደሱ ጭምብል መልበስ ግን!!እንዲያዉ ባየኸዉ ቁጥር ጭምብል አጥልቆ ነዉ።የሚነጋገረዉ ከሱ ሁለት መቶ ጫማ ርቀት ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ሊሆን ይችላል፣ የሚታየዉ ግን እድሜ ልኬን እይቼዉ የማላዉቀዉ ትልቅ ጭምብል አጥልቆ ነዉ።»

ሹፈት፣ተረብ፣ ንቀታቸዉ በርግጥ እስካሁን የመጨረሻዉ ሆነ።በሳምንቱ ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ ከነባለቤታቸዉና ከ8 ባለስልጣን ወዳጆቻቸዉ ጋር በኮቪድ 19ኝ መታመማቸዉ ተረጋገጠ።ሆስፒታል ገቡም።ቦሪስ ጆንሰን አገግመዉ ሥራ ሲጀመሩ «ከእንግዲሕ በኮሮና ቀልድ የለም» ብለዉ ነበር።ቦልሶናሮ ዝም ነዉ ያሉት፤ ዝም።ትራምፕስ?  ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች