1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አንዲት ባለትዳር በ8 ታጣቂዎች ስትደፈር ለማስቆም የሞከረች እናት በጥይት ተገድላለች”

ረቡዕ፣ ሰኔ 12 2016

የካርድ እንዳስታወቀው«የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ስምንት ወታደሮች አንዲትን ባለትዳር ሴት ለስምንት ሲደፍሯት ጠልቃ ገብታ ለማስቆም የሞከረችን እናት በጥይት መተው ገድለዋታል”። “በአንድ የመንግስት ሠራዊት አባል የተደፈረች የ18 ዓመት ታዳጊ የደረሰባትን ድርጊት እንዳትናገር በወታደሩ ተተኩሶባት መገደሏን”የዓይን እማኞችን ጠቅሶ በዘገባው አስቀምጧል፡፡

https://p.dw.com/p/4hGTQ
የኦሮምያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን
የኦሮምያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

«አንዲት ባለትዳር በ8 ታጣቂዎች ስትደፈር ለማስቆም የሞከረች እናት በጥይት ተገድላለች”

የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞኖች ላይ አተኩሮ በሰራው የዳሰሳ ጥናት በግጭት ወቅት ክፉኛ ከሚጎዱ የማህበረሰብ አካላት ዋነኛዎቹ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን አጉልቶ አሳይቷል፡፡ እንደ ሰብዓዊ ተቋሙ ጥናት በግጭቱ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ተፋላሚዎች በሚፈጸመው በተለይም ሴቶች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት እጅግ አስከፊ ሊባሉ የሚችሉ  ተደጋግመው ተከስተዋል፡፡ እንደ ጥናቱ ዝርዝር ከሆነ በአከባቢው በግጭት ውስጥ ባሉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) እና በኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች መጠነ-ሰፊ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ሲፈጸሙ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ 
የካርድ ጥናት ግኝቶቹን ለአብነት ስዘረዝር “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ስምንት ወታደሮች አንዲትን ባለትዳር ሴት ለስምንት ሲደፍሯት ጠልቃ ገብታ ለማስቆም የሞከረችን እናት በጥይት መተው ገድለዋታል” ይላል፡፡ በሌላ በኩልም “በአንድ የመንግሥት ሠራዊት አባል የተደፈረች የ18 ዓመት ታዳጊ የደረሰባትን ድርጊት እንዳትናገር በሚል በወታደሩ ተተኩሶባት መገደሏን” ለጥናቱ ግብዓትነት ከሰበሰበው የአይን እማኞች ማስረጃ መረዳቱን ካርድ በጥናቱ ውጤት አስቀምጧል፡፡ ልጆችና ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በኢትዮጵያ


የጥቃቶቹ መዘዝ፤ ማህበራዊ ህይወትን ማመሳቀላቸው

እንደ ጥናቱ በታጠቁ አካላት የተደፈሩ ሴቶች “ልጃገረዶችም ቢሆኑ ሊወሰድ የሚችለውን አጸፋ ስለሚገነዘቡ የሚደርስባቸውን መሰል ጥቃት የማሳወቅ ሁኔታው አነስተኛ ነው፡፡” አስተያየታቸውን ለጥናቱ ግብዓት የሰጡ የሃይማኖት አባቶችም ጭምር በማህበረሰቡ ውስጥ በነዚህ በታጠቁ ሁሉም ወገኖች ብዙ ጥፋቶች ቢፈጸሙም “ሊከተል የሚችለውን ተጨማሪ መዘዞች በመፍራት ጉዳቱን የሚተነፍስ አካል ባለመኖሩ” ማንም ተጠያቂ ሲሆን አይታይም ይላሉ፡፡ በዚህም ለተለያዩ ጉዳቶች የተዳረገው ማህበረሰብ ከዘላቂ የአዕምሮ ጉዳቶች ጋር እንዲኖር ያስገድደዋል፡፡  
ለካርድ አስተያየታቸውን የሰጡ የጥናቱ ተሳታፊዎች የታጠቁ አካላት ለምን እንዲህ ያለ ድርጊት እንደሚፈጽሙም የሚያውቁት ነገር እንደሌሌ ያስገነዝባሉ፡፡ የካርድ የጥናት ውጤት ግን “አስገድዶ መድፈር ላይ የሚሳተፉ ወንድ ወታደሮች ቡድንን ወይም አከባቢውን የመቅጣት እና የመቆጣጠር ፍላጎት አንግበው ድርጊቱን እንደ ጦር መሳሪያ እንደሚጠቀሙ” ያስረዳል፡፡

ፆታዊ ጥቃት ይቁም የሚለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀን ምልክት
ፆታዊ ጥቃት ይቁም የሚለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀን ምልክት ምስል Colourbox

የወንጀሉ የአሰቃቂነት ደረጃ 

የስነጾታ ባለሙያ እና ተመራማሪ  ናርዶስ ጩታ ይህን ጥናት በጥልቀት መመልከታቸውን ገልጸው በድርጊቱ የተሳተፉትን አካላት በሙሉ ተጠያቂ ማድረጊያ መንገድ መፈለግ እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ “ሪፖርቱ እንዳሳየው ይህ ነገር የተደረገው በሁለቱም ተፋላሚ ሃይላት ነው፡፡አምነስቲ፤ በኢትዮጵያ ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸዉ ፍትህ ሁለቱንም ወገኖች በማወያየት ወደመፍትሄው ቢኬድ የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ” የሚሉት ባለሙያዋ የተፈጸሙ ወንጀሎቹ ደረጃቸው ቢለያይም እጅጉን አሰቃቂ መሆናቸውን በአስተያየታቸው አብራርተዋል፡፡ ወላጆቿ ፊት ከተደፈረችና በዚህም ምክንያት በደረሰባት የዐእምሮና የአካል ጉዳት ትምህርቷን ካቋረጠች የ11 ዓመት ታዳጊ እንደማሳያ በማቅረብም ከስምንት ዓመት ታዳጊ ጀምሮ ሴቶች በግጭቶቹ አከባቢዎች መደፈራቸውን  እጅጉን አሰቃቂ ብለውታልም፡፡


የተጠያቂነት እድል አናሳ መሆን ለወንጀሉ መባባስ መንስኤ

በግጭቶች ሴቶች የተደፈሩበት የጉጂ ዞን
በግጭቶች ሴቶች የተደፈሩበት የጉጂ ዞን ምስል Private

የስነጾታ ባለሙያ እና ተመራማሪዋ ናርዶስ በግጭት ውስጥ የሚፈጸምን የጾታዊ ጥቃት የተጠያቂነት ሁኔታን አጠያያቂ አድርገው ያነሱታል፡፡ “ይህኛው የጾታዊ ጥቃት በሌሎች አውዶች ውስጥ ከሚደረጉ የጻታዊ ጥቃቶች ለየት ያለ ይዘት ያለው ነው፡፡ በመደበኛ ሁኔታ ውስጥ የተጠያቂነት ሁኔታ ስለሚኖር ወደ ፍትህ የመሄዱ አዝማሚ ይኖራል፡፡ በግጭት አውድ ውስጥ ግን የተጠያቂነት ጉዳይ አነስተኛ መሆን ችግሩን ያባብሷል” በማለት አስተያየታቸውን አክለዋልም፡፡ባለሙያዋ ለተጠቁት ሴቶች ዘላቂ ማገገም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ሌላው አንገብጋቢና አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ይጠቁማሉም፡፡ “የተጠቁ ሰዎች አሁን ካሉበት ሁኔታ እንዲያገግሙ ሰብዓዊ እርዳታ ያስፍልጋቸዋል፡፡ ጉዳቱ ከአካልም በላይ በመሆኑ ተጎጂዎች ተከታታይ ምክር የሚያገኙበት ሰብዓዊ ርብርብ ቢደረግም መልካም ነው” ብለዋል፡፡ ፆታዊ ጥቃቶችን በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች መዋጋቱ ምን ያህል ስኬታማ ነው?

ተጠያቂነትን ማስፈን ከባድ ቢሆንም ማድረግ ግን ይቻላል የሚሉት ባለሙያዋ የገለልተኛ አጥኚዎች ተሳትፎ እና የተፋላሚዎች ቀናኢነት በዚህ ውስጥ እጅጉን እንደሚስፈልግም አልሸሸጉም፡፡ ድርጊቱ በፖለቲካ ፍላጎት ውስጥ በመገፋት የተደረገ እንደመሆኑ ከተጠያቂነት የመሸሽ ሁኔታ ስለሚታይ ብዙውን ጊዜ ተጠያቂነት ማስፈን ቀላል አይሆንም የሚሉት ባለሙያዋ፤ ሁለቱንም ወገኖች በማወያየት በትክክል ከተጠና ግን ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ጥቆማቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዛሬ በዓለማቀፍ ደረጃ ታስቦ የዋለው በግጭት ውስጥ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃትን የማጥፋት ቀን ነው፡፡ ከዚሁ ቀን ጋር በማያያዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እጅጉን አስከፊ ባለው 117 ሚሊየን ህዝብ በዓለም በሚካሄዱ ግጭቶች ተፈናቅለው አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ መውደቃቸውን ይገልጻል፡፡ በዚህም ቁጥር አንድ ተጠቂዎች ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን መረጃው ይጠቁማል፡፡ 
ስዩም ጌቱ 
ኂሩት መለሰ 
አዜብ ታደሰ