አንካራ፤የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ በቱርክ | ዓለም | DW | 16.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

አንካራ፤የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ በቱርክ

የቱርክ ባለሥልጣናት በፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ላይ የተሞከረውን መፈንቅለ-መንግስት ማክሸፋቸውን አስታወቁ። ትናንት ምሽት የቱርክ ጦር ሰራዊት አባላት የራቺብ ጣይብ ኤርዶኻንን መንግስት ከሥልጣን በማስወገድ አገሪቱን መቆጣጠራቸውን ካስታወቁ በኋላ ከ250 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በትናንትናው ምሽት የውጊያ አውሮፕላኖች በኢስታንቡል ከተማ ዝቅ ብለው መብረራቸውን፤ ታንኮች ወደ አደባባይ መውጣታቸውንና ተከታታይ ፍንዳታዎች መከሰታቸው ተዘግቧል። ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ካልታወቀ ስፍራ ኾነው ደጋፊዎቻቸው ወደ አደባባይ በመውጣት መፈንቅለ-መንግስቱን እንዲያከሽፉ በተንቀሳቃሽ ስልክ ያስተላለፉት ጥሪ በቴሌቪዥን አየር ላይ ከዋለ በኋላ በተለያዩ ከተሞች አደባባዮች ኹከት ተቀስቅሶ ነበር። የቱርክ ሰንደቅ አላማን በማውለብለብ ወደ አደባባይ የወጡት የገዢው የልማት እና ፍትሕ ፓርቲ ደጋፊዎች ምሽቱን ከጦር ሰራዊቱ አባላት ጋር ተጋጭተዋል። በአጸፌታው ወታደሮች የመፈንቅለ-መንግስቱ ሙከራን በተቃወሙ ዜጎች ላይ መተኮሳቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። የቱርክ አየር ኃይል የመፈንቅለ-መንግስቱ ደጋፊዎች ከቤተ-መንግስቱ አቅራቢያ ባቆሟቸው ታንኮች ላይ በኤፍ.16 የውጊያ አውሮፕላኖች መተኮሱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የቱርክ ምክር ቤት በከባድ መሣሪያ በመታበት ወቅት በአስቸኳይ ስብሰባ ላይ የነበሩት አባላት በከፊል።

የቱርክ ምክር ቤት በከባድ መሣሪያ በመታበት ወቅት በአስቸኳይ ስብሰባ ላይ የነበሩት አባላት በከፊል።

የቱርክ ባለስልጣናት መፈንቅለ-መንግስቱን የጠነሰሱት በስደት ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት የሃይማኖት መምህር ሼህ ፌቱላህ ጉሌን ናቸው ሲሉ ወንጅለዋል። መፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ ምሽት ላይ የቱርክ ምክር ቤትን በከባድ መሣሪያ በመቱበት ወቅት አባላቱ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ነበሩ። ጉዳት በደረሰበት ምክር ቤቱ ሕንፃ ውስጥ አባላቱ ዛሬ ብሔራዊ መዝሙር አሰምተው አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጋቸው ተዘግቧል። ዩናይትድ ስቴትስ ሰውዬውን አሳልፋ እንድትሰጣት ቱርክ ጠይቃለች። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ጆን ኬሪ በበኩላቸው ጥያቄውን እንደምታጤነው ገልጠዋል፤ ኾኖም ስደተኛው ጉሌን በሴራው እጃቸው ስለመኖሩ ቱርክ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ አለባት ብለዋል። በዛሬው ዕለት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቢናሊ ይልድሪም የመፈንቅለ-መንግስት ሞክረዋል ያሏቸውን የጦር ሰራዊት አባላት በማውገዝ ሁኔታው በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታውቀዋል። 2,839 ወታደሮች እና ከ100 በላይ መኮንኖችን ጨምሮ በመፈንቅለ-መንግስት ሙከራው የተሳተፉ በሙሉ መታሰራቸውን አናዱሉ የዜና አውታር ዘግቧል። የቱርክ መንግሥት ዛሬ ረፋዱ ላይ ከመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ጋር በተያያዘ በሚል 2,745 ዳኞችን ማሰናበቱ ተገልጧል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ