አንበጣ እና ተምች በክረምት | ጤና እና አካባቢ | DW | 09.07.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

አንበጣ እና ተምች በክረምት

የዓለም የምግብ ድርጅት FAO ከሰሞኑ በመካከለኛው ምሥራቅ እና ከሩቅ ምሥራቅ አካባቢ የአንበጣ መንጋ ቀንሶ ሲታይ፤ በተቃራኒው እድገታቸውን የጨረሱ አንበጣዎች የመን ውስጥ ተስፋፍተው መታየታቸውን አመልክቷል። ከመን ድንበር ተሻግሮ አንበጣ ወደ ሰሜን ሶማሊያ፤ ደቡባዊ ኤርትራ እና ወደ ምሥራቃቂ ኢትዮጵያ ግዛቶች መግባቱንም አሳስቧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:42

«ኢትዮጵያ ላይ አሁን ከአንበጣው ይልቅ አርሚ ዎርም የተባለው ተምች ሁሉንም ቦታ አድርሷል»

የዓለም የምግብ ድርጅት በእንግሊዝኛው ምህጻሩ FAO ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ይፋ ያደረገው ማሳሰቢያ፤ በኢራን፤ በሳውድ አረቢያ እና ፓኪስታን ተንሰራፍቶ የከረመው የአንበጣ መንጋ በዚህ ወር መቀነሱን ያመለክታል። FAO እንደሚለው በተጠቀሱት ሃገራት 300 ሺህ ሄክታር መሬትን አስግቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ሊቀንስ የቻለው በአየር ጠባዩ መድረቅ እና ሙቀት በመጨመሩ እንዲሁም በተደረገው ጠንካራ ቁጥጥር እና ክትትል አማካኝነት ነው። በዚህ አካባቢ ቀነሰ የተባለው የአንበጣ መንጋ የመን ላይ ተጠናክሮ መታየቱን፤ ከዚያም አልፎ ባሕር ተሻግሮ ወደ ሰሜን ሶማሊያ፣ ብሎም ደቡባዊ ኤርትራ እና ምሥራቅ ኢትዮጵያም መዝለቁንም ያሳያል። በእነዚህ ሃገራት በዚህ ወቅት ዝናብ የመኖሩ አጋጣሚ እድገቱን የጨረሰው አንበጣ እንቁላል በመጣል  መስፋፋቱን ለማፋጠን እንደሚሞክር በማመልከትም ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እንዲሁም ሳውድ አረቢያ ከወዲሁ እንዲጠነቀቁም አሳስቧል። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለውን እንዲገልፁን የጠየቅናቸው በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዮስ ሰላቶ፤  በተለያዩ አካባቢዎች የተበታተነ አንበጣ ቢታይም በመንጋ መልኩ እንዳልተከሰተ እና የመቆጣጠሩ ሥራ እየተሠራ ነው ይላሉ።

«መንጋ እኮ አይደለም ይሄ ምንድነው ኖርማሊ ኢትዮጵያ የአንበጣ መራቢያ ወይም ይሄ ብሪዲንግ ሲዝን የሚባል አላት። ያው በዝናብ ወራት ከጎረቤት ሃገራት በተለይ ከየመን ወደ ሶማሌላንድ ሲመጣ ከሶማሌላንድ ወደ ኢትዮጵያ አንበጣ የሚገባባቸው፤ አንዳንዴ ደግሞ የራሳችንም በተናጠል የሚኖር አንበጣ ምቹ የአየር ጠባይ አግኝቶ ቁጥሩ የሚጨምርበት ወራት አሉ። ስለዚህ አሁን ይሄ በጣም ትልቅ ክሰት አይደለም፤ መንጋ የምንለውም አይነት አይደለም።»

የእጸዋት ጠር የሆኑት አንበጣዎች ለመራባት የሚፈልጉት ምቹ የአፈር አይነት እና አካባቢ መኖሩን የሚናገሩት ባለሙያው ይህንንም ኅብረተሰቡ ስለሚያውቅ አስቀድሞ ክትትል ለማድረግ እንደሚረዳም ገልጸዋል።

በFAO አማካኝነት አንበጣ ሊመጣባቸው ያሉ አካባቢዎች ሃገራት ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጣቸው፤ ያንን መሠረት በማድረግም እያንዳንዴ ሀገር የየራሱን ዝግጅት ማለትም አሰሳ እንዲሁም የመከላከል ሥራ እንደሚሠራም አስረድተዋል። ችግሩ ሲሰፋ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሲያስፈልግ ደግሞ፤ አህጉራዊም ዓለም አቀፋዊም ትብብር እንደሚደረግም ዘርዝረዋል። አቶ ዘብዲዎስ እንደገለፁት FAO ባለፈው ሳምንት ማሳሰቢያውን አውጥቷል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያም ተጠቅሳለች። እና በቂ ዝግጅት ተደርጎ ይሆን?

«አዎ በቂ ዝግጅት፤ አሁን ምንድነው ሎጂስቲክ ማዘጋጀት ነው፤ ያው ምንድነው አንበጣ ቁጥሩ እየጨመረ ከመጣ በጸረ ተባይ ነው ሌላ ምርጫ የለም።»

ኢትዮጵያ ያላት የግብርና ኤክስቴንሽን ስርዓት ጠንካራ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዘብዲዮስ ሰላቶ፤ ተገቢው ስልጠና በቀበሌዎች ደረጃ እየተሰጠ ዝግጅቱ መጠናከሩን ገልጸውልናል።  በክረምቱ ከወዲሁ የዝናቡ ሁኔታ ጥሩ መሆኑን  ከብሔራዊ ሜቲሪዎሎጂ የሚደርሳቸው መረጃ እንደሚያስረዳ የሚናገሩት የግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፤ በቆላማ አካባቢዎች ከሚታየው በቀር በቂ ዝናብ እንደሚኖር ያላቸውን ተስፋም አጋርተውናል።

ዝናቡ መኖሩ ለአዝርዕቱም ሆነ ለኅብረተሰቡ ጤና መልካም ቢሆንም አጋጣሚውም ለአንበጣው መራባት ምቹ መሆኑ ይነገራል። ምን ያህል ያሰጋ ይሆን? አሁንም አቶ ዘብዴዎስ፤

«ትክክል ነው አሁን ምንድነው ለአንበጣ መራቢያ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ተብለው ከሚታሰቡ የአየር ጠባይ ሁኔታዎች አንዱ ዝናብ ነው። »

መድኃኒት በሚረጭበት ጊዜም ሰብሎች እንዲሁም ጠቃሚ የሆኑ እንደንብ ያሉት ፍጠረታት ችግር እንዳይደርስባቸው የሚደረግ ጥንቃቄ ይኖር ይሆን? አቶ ዘብዲዎስ ርጭሩ ሰብል ላይ እንደማይደረግ፣ የአንበጣው ማደሪያ እና ማረፊ የታወቀ በመሆኑ ሰዓቱን ጠብቁ በተወሰነ አካባቢ ብቻ እንደሚረጭ ነው ያስረዱት። የንብ ቀፎ በስፍራው ካለም ወደሌላ ቦታ ለተወሰኑ ቀናት እንዲዛወር እንደሚደረግም ዘርዝረዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የታየው አንበጣም ቀድሞ ዝግጅት በመደረጉ ያን ያህል ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት እንደሌለም ተናግረዋል።

አንበጣ በተፈጥሮ የሚከሰት ድንበር የማያግደው ከቦታ ወደቦታ ምቹ ስፍራ እና ወቅትን እየመረጠ የሚገኝ ጸረ ሰብል ፍጥረት ነው። አንበጣን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት

ቢጠናከርም ቁጥሩን በመቀነስ የሚያደርሰውን ጉዳት ለማሳነስ ከሚደረገው በዘለለ ጨርሶ ማጥፋቱ አዳጋች መሆኑን አቶ ዘብዲዎስ ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ ባለሙያው እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ ከአንበጣ በበለጠ በመላው ሀገሪቱ ተስፋፍቶ የሚገኙ ሌላው የእህል ጠር አርሚዎርም የሚባለው የተምች አይነት ነው።

ምንም እንኳን ይህ የተምች አይነት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ቢገኝም ተበራክቶ ከተከሰተ አንበጣ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ነው የገለፁት። ለምን ቢባል የሚመርጠው የእህል ዘር ስለሌለው እንደሆነ ባለሙያው ገልጸዋል። የዓለም የምግብ ድርጅት FAO በዘንድሮው የኢትዮጵያ የክረምት ወቅት የአንበጣዎች መራባት ደረጃ ወትሮ ከነበረው ሊበረክት እንደሚችል፤ ሌሎች ትናንሽ ትሎችም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰሜን ሶማሊያ፤ በሱዳን፤ የመን፤ እንዲሁም በሕንድ እና ፓኪስታን የድንበር አካባቢ ተበራክቶ ሊከሰቱ  እንደሚችሉም አሳስቧል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic