አነጋጋሪዉ የዕስረኞች አፈታት ሂደት | ኢትዮጵያ | DW | 25.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

አነጋጋሪዉ የዕስረኞች አፈታት ሂደት

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሀገራዊ መግባባትና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ታሳሪዎችን ለመፍታት ከወሰነ ካለፈዉ ጥር ወዲህ የተፈረደባቸዉና ክሳቸዉ በሂደት ላይ የሚገኙ እስረኞችን እየፈታ ነው። ይሁን እንጅ በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩና በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱ ሰዎች አሁንም ድረስ እስር ላይ መሆናቸዉን የተከሳሽ ጠበቆች ይናገራሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:48

«የሚፈቱበት መንገድ የተዘበራረቀና ለትርጉም የሚያስቸግር ነዉ።»ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ

 እስረኞቹ የሚለቀቁበት መንገድ ግልፅ ባለመሆኑም አንዳንዶቹ  ክሳቸዉ ቀጥሎ እየተፈረደባቸዉ በመሆኑንም ጠበቆቹ አመልክተዋል። መንግሥት ለሀገራዊ መግባባትና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ታሳሪዎችን መልቀቅ ከጀመረ ካለፈዉ ጥር ወዲህ በተለያዩ ክልሎች በሺህ የሚቆጠሩ ታሳሪዎች መለቀቃቸዉ ሲገለፅ ቆይቷል። ከዚህ የምህረት አዋጅ ጋር የተገናኘ ባይሆንም በትናንትናዉ ዕለትም በኦሮሚያ ክልል ከ 7 ሺህ በላይ ለሆኑ የሕግ ታራሚዎች የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ምህረት አድርገው መፍታታቸዉ ተዘግቧል። በትግራይ ክልልም ከ200 በላይ የሕግ ታራሚዎች በተመሳሳይ መንገድ ተለቀዋል። ያም ሆኖ ግን በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረዉ የታሰሩ በርካታ ሰዎች አሁንም ድረስ እስር ላይ መሆናቸዉ ብዙዎችን እያነጋገረ ነዉ። ጉዳዩ በተከሳሾቹ ጠበቆችና ቤተሰቦች ዘንድም ቅሬታ ማሳደሩ ተገልጿል። በሀገሪቱ ተከስቶ ከነበረዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ ጋር ተያይዞ ለታሰሩ 200  ታሳሪዎች አቶ አለልኝ ምህረቱ ጠበቃ ናቸዉ።   አብዛኛወቹ ከአማራና ከኦሮሚያ ክልል ለሆኑ ተጠርጣሪዎች ጥብቅና መቆማቸዉን የሚናገሩት አቶ አለልኝ፤ ከደንበኞቻቸዉ ዉስጥ 130 የሚሆኑት የተፈቱ ቢሆንም  ቀሪዎቹ አሁንም ድረስ እስር ቤት ናቸዉ። የተከሰሱበት ወንጀል ግን ተመሳሳይ ነዉ ይላሉ።


«ሁሉም የክስ ዓይነት አንድ ነዉ።ያዉ አሸባሪ ከተባለ ድርጅት ጋር ተገናኝታችሁ ሽብር ልትፈፅሙ  ስትሉ ተይዛችኋል ወይም ፈፅማችኋል በሚል ነዉ።ከአንድ ክስ እንግዲህ ከአንድ መዝገብ ላይ አብዛኛዎቹ ተለቀዉ ጥቂቶች የቀሩ አሉ።ጥቂቶች ተፈተዉ አብዛኛዎች የቀሩ አሉ። ለኛም በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ደንበኞቻችን በየጊዜዉ አቤቱታ በማቅረብ ላይ ናቸዉ።»ነዉ ያሉት ጠበቃዉ።

በዚህም የተነሳ ታሳሪዎቹና ቤተሰቦቻቸዉ ፍርድ ቤት በቀረቡ ቁጥር ቅሬታ እንደሚያሰሙ ገልፀዋል። የመንግሥትን የይፈታሉ ዉሳኔ ተከትሎ ሁሉም ደንበኞቻቸዉ እንደሚፈቱ ተስፋ ቢያደርጉም ይሄ ነዉ የሚባል የሕግ ምክንያት ሳይቀርብ  ከፊሎቹ ተለቀዉ ከፊሎቹ  እስር ቤት መቅረታቸዉ  ግራ እንዳጋባቸዉ ጠበቃዉ ተናግረዋል። ጉዳዩን በተመለከተ ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቤቱታ አቅርበዉ እንደነበርም የገለጹት ጠበቃዉ ፤ ጉዳዩ የሰዎችን በሕግ ፊት እኩል የመታየት  መብት የሚጋፋ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠዉ ያሳስባሉ።
«አንድ አንቀፅ ተጠቅሶባቸዉ እየተከራከሩ ያሉ ሰዎች ከፊሎቹ ተፈተዉ ከፎሎቹ ሲቀሩ የሰዉን እኩል ሆኖ የመታየት መብት የሚጥስ ስለሆነ፤ጠቅላይ አቃቬ ህግ በአጭር ቀን የመንግስትን ዉሳኔ በአግባቡ አስፈፅሞ የቀሩትን እንዲፈታ ነዉ መልዕክቴ»ብለዋል።
ከቤንሻንጉል ክልል መተከል አካባቢ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዉ ለተያዙ 11 ሰዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ቀንዓ በበኩላቸዉ ከደንበኞቻቸዉ ዉስጥ 7ቱ በመንግሥት የምህረት ዉሳኔ ተፈተዋል። ቀሪዎቹ  4 ታሳሪዎች ግን የክስ ሂደታቸዉ  ቀጥሎ አሁንም ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ይገኛሉ ነዉ ያሉት። ስለ ጉዳዩ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ቢያቀርቡም ግልጽ ምላሽ አለማግኘታቸዉንም አብራርተዋል።።


ሌላው ዶክተር መረራ ጉዲናን፣አቶ በቀለ ገርባን ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና አቶ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ ለ600 ታሳሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ ናቸዉ። ለአብዛኞቹ ታሳሪዎች በነፃ ጥብቅና መቆማቸዉን የሚገልፁት አቶ ወንድሙ አብዛኛዎቹ ከእስር ነፃ ቢሆኑም ወደ 200 የሚጠጉ ደንበኞቻቸው አሁንም እስር ቤት ናቸዉ።

«ከኦሮሚያ ክልል ወደ  120 የኦሮሞ ልጆች ከአማራና ከሌሎች ክልሎች ወደ 80 አካባቢ የሚሆኑት አሁንም እንዳልተፈቱ ነዉ የምረዳዉ።»ካሉ በኋላ ከቄለም ወለጋ  የመጡ የተወሰኑ ታሳሪዎች ክስ መቀጠሉን ለአብነት አንስተዋል።
ከ2 ዓመት በላይ በዝዋይ እስር ቤት ቆይቶ በቅርቡ የተለቀቀዉ የቀድሞዉ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የጠበቆቹን ሀሳብ ያጠናክራል። 
«እኔ እንኳ በዝዋይ እስር ቤት የማዉቃቸዉ በርካታ ሰዎች አሉ።ዝዋይ በነበርኩበት ወቅት።ሌሎቹን በወሬ ደረጃ ነዉ የማዉቃቸዉ።ዝዋይ ግን አሁን በቅርብ ጊዜ ራሱ አንድ ሳምንት በፊት ጓደኞቼን ለመጠየቅ ሄጀ ነበር።ከጅማ አካባቢ የመጡ አሉ።»ብሎ ስማቸዉን ከዘረዘረ በኋላ ያልተፈቱ አብራሪዎችም እንዳሉ ገልጿል።ሌሎች በስም የማያዉቃቸዉ በርካታ ሰዎች በዕስር ላይ መሆናቸዉን ዮናታን ጠቅሷል።
አብረዉት ታስረዉ ከነበሩት ዉስጥም ጠበቃ የሌላቸዉ እንደነበሩ አስታዉሶ ፤ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተገናኘ እሱ ታስሮበት በነበረዉ ዝዋይ እስር ቤት  ክሳቸዉ የተቋረጠላቸዉ ነገር ግን አሁንም ያልተፈቱ  ሰዎች እንዳሉ ገልጾ፤ ስለነዚህ ሰዎች በተገኜዉ አጋጣሚ ድምፃችንን ልናሰማ ይገባልም ብሏል።
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግን  አስተያየት ለማግኜት ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም።

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሰ

 

Audios and videos on the topic