አነጋጋሪዉ የሴቶች መብት ይዞታ | ጤና እና አካባቢ | DW | 10.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

አነጋጋሪዉ የሴቶች መብት ይዞታ

የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከትናንት በስተያ ታስቦ ዉሏል። ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት በመላዉ ዓለም የሴቶችን መሠረታዊ መብቶች ለማስከበር የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም አሁንም እጅግ ረዥም ጉዞ እንደሚቀር የተመድ ዋና ጸሐፊ ያመለከቱት። ዘንድሮ የሴቶች ቀን ሲታሰብም የተመረጠዉ መሪ ቃል «እዉን አድርጉት» የሚል ነዉ።

«በዚህ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ለሴቶች መብት ለሚደረገዉ ትግል የተደረሰዉን መሠረታዊ ስምምነት 20ኛ ዓመትም እናከብራለን። የቤጂንግ ስምምነትና የተግባር ዕቅድ ጠንካራ መመሪያዎችን የያዘ ነዉ። የሴቶች መብት ሰዉ ልጅ መብት ነዉ። ይህም ለፆታ እኩልነትና በተለያዩ ሙያዎችና ማኅበራዊ ዘርፎች ሴቶችና ልጃገረዶች ለአመራር ብቁ እንዲሆኑ ግልፅ አቅጣጫን አመላካች ነዉ። በዚህ ረገድም ትርጉም ያለዉ መሻሻል ታይቷል። በርካታ ልጃገረዶች በፊት ከነበረዉ በተሻለ መልኩ ትምህርት የማግኘት እድል አግኝተዋል፤ በወሊድ ጊዜ የሚሞቱ እናቶች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረዉ በግማሽ ቀንሷል። በርካታ ሴቶች በንግዱ ዓለም፣ በመንግሥት አስተዳደርና በዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ዉስጥ የመሪነት ቦታ ይዘዋል። አሁም ግን ሴቶች ሊደርሱባቸዉ የሚገባ በርካታ ግቦች አሉ፤ እንደየቤት ዉስጥ ጥቃት፣ ግርዛት፤ እንዲሁም የተለያዩ የጥቃት ዓይነቶች። አድሎ አሁንም ጣሪያ እንደነካ ነዉ፤ ይህን ሁሉ ተባብረን ማስቀረት ይኖርብናል።»

በማለት ነዉ ዕለቱን አስመልክተዉ የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ጊ ሙን መልዕክታቸዉን ያስተላለፉት። ባን ጊ ሙን ግልፅ እንዳደረጉትም አሁንም የሴቶችን መብት ከማስከበር አኳያ የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም የሚቀሩት በርካታ ናቸዉ። ከምንም በላይ የሰዎች አመለካከት መሠረታዊ ለዉጥ እንደሚያሻዉም ዋና ፀሐፊዉ ሳያስቡ አላለፉም። ለአሜሪካን ፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት ሂላሪ ክሊንተንም እንዲሁ እሁድ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት በዘመናችን ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችና የተለያዩ የመብት ገፈፋዎች ከዘመኑ ጋ አብረዉ እንደማይሄዱ ነዉ የጠቆሙት።

የዛሬ 20ዓመት ቤጂንግ ላይ ስለሴቶች መብት በተካሄደዉ ጉባኤ በሀገራቸዉ ቀዳማይ እመቤትነት የተገኙት ክሊንተን፤ ያኔ ነበር የሴቶች መብት የሰብዓዊ መብት መሆኑን በመግለፅት አፅንኦት እንዲሰጠዉ ያሳሰቡት። በወቅቱም 189 መንግሥታት የሴቶች መብት እንዲከበር የሚደነግገዉን ሕግ ተስማምተዉበት ተቀብለዋል። ያም ሆኖ ዘንድሮም አሉ ታዲያ ሂላሪ ክሊንተን በ21ኛዉ ክፍለ ዘመንም የሴቶችን መብት ሙሉ በሙሉ አክብሮ የማስከበሩ ጉዳይ ያልተቋጨ ሥራ ነዉ። ለዚህም ዓለም ይህን በይደር ያስቀመጠዉን የቤት ሥራ ትርጉም ባለዉ መልኩ እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል። ዕለቱን አስመልክቶ የወጣ አንድ ጥናት የቤጂንጉን ዉል ከፈረሙት ሃገራት 56ቱ በሕገ መንግሥታቸዉ ማካተታቸዉን ያመለክታል። ሕጉን በሕግነት መቀበሉ ብቻ በቂ አይደለምና አሁንም «እዉን አድርጉት» የሚል ጥሪ ነዉ የቀረበላቸዉ። ሕጉን ከተቀበሉ ሃገራት አንዷ ኢትዮጵያ ለተግባራዊነቱ ምን ያህል ተሳክቶላታል? የኢትዮጵያ ሴት ማኅበራት ጥምረት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድህን ያስረዳሉ። ከድምፅ ዘገባዉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic